1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የይርጋዓለም አግሮ-ኢንዱስትሪ መንደር

ረቡዕ፣ ጥቅምት 26 2012

በ294 ሄክታር  መሬት በመገንባት  ላይ የሚገኘው የአግሮ ኢንዱስትሪ ፖርክ   ዘርፈ ብዙ አገራዊ ጠቀሜታዎችን መሠረት አድርጎ የተነሳ ስለመሆኑ ይነገርለታል፡፡ በተለይም የወጪ ንግድ ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ጨምሮ  ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የፖርኩ የሥራ ሃላፊዎች ይናገራሉ፡፡

https://p.dw.com/p/3SaHW
Avocado-Anbau in Tigray
ምስል DW/S. Wegayehu

የይርጋዓለም አግሮ-ኢንዱስትሪ መንደር

የኢትዮጵያ መንግሥት በሁለተኛው የእድገትና የምጣኔ  ሀብት እድገት ሽግግር እቅዱ አራት ግዙፍ የተቀናጀ የግብርና አንዱስትሪ መንደሮችን (ፓርኮችን) በመገንባት ላይ ነዉ። በደቡብ ፣ በአማራ ፣በኦሮሚያና በትግራይ ክልሎች በመገንባት ላይ የሚገኙት መንደሮች የአርሻና የአንዱስትሪ ዘርፉን በማስተሳሰር ለአገሪቱ የምጣኔ  ሀብት እድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ይኖራቸዋል ተብሎ ታምኖባቸዋል

በሲዳማ ዞን ዳሌ ወረዳ የዳጊያ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት የሃምሣ አምስት ዓመቱ አዛውንት መንግሥቱ አሊቶ የዕድሜ ዘመናቸውን ያሳለፉት በግብርና ሥራ እንደሆነ ይናገራሉ። አቶ መንግሥቱ ለዓመታት አፈር ገፍተው የደከሙበት ጥረታቸው ግን እንዳሰቡት ኑራቸውን ብዙም ፈቅ ያደረገላቸው አይመስልም። አሁን ላይ እሳቸውን ጨምሮ ሌሎች የአካባቢው አርሶ አደሮች በአቅራቢያቸው በመገንባት ላይ  የሚገኘውን የይርጋዓለም የተቀናጀ  የግብርና አግሮ ኢንዱስትሪ ፖርክ ተስፋ ማድረጋቸው አልቀረም።

በአሁኑ ወቅት ለፖርኩ ኢንዱስትሪዎች  በምርት ግብዓትነት ሊውሉ የሚችሉ የቡናና አቮካዶ ዛፎችን በማልማት ላይ እንደሚኙ የሚጠቅሱት አቶ መንግሥቱ  በተለይ ተፈላጊ ዝርያዎችን በማዳቀልና በማባዛት የገቢ ምንጭ መፍጠራቸውን ይናገራሉ። አቶ መንግሥቱን  ጨምሮ በበርካታ አርሶ አደሮች ተስፋ የተጣለበት የይርጋዓለም የተቀናጀ የግብርና አግሮ ኢንዱስትሪ ፖርክ  ከሀዋሣ ከተማ  በ47 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ሥፍራ ግንባታው እየተከናወነ ይገኛል። በ294 ሄክታር  መሬት ላይ በመገንባት  ላይ የሚገኘው ይኸው የአግሮ ኢንዱስትሪ ፖርክ  ከመነሻው ዘርፈ ብዙ አገራዊ ጠቀሜታዎችን መሠረት አድርጎ የተነሳ ስለመሆኑ ይነገርለታል። 

በተለይም የወጪ ንግድ ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ጨምሮ  ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የፖርኩ የሥራ ሃላፊዎች ይናገራሉ። የይርጋዓለም የተቀናጀ የግብርና አግሮ ኢንዱስትሪ ፖርክ የኦኘሬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ኤኬቲ  የፖርኩ የግንባታ አፈጻጸም የሚገኝበትን ደረጃ እንዲህ ይገልጻሉ።
በእርግጥ በተንጣለለው የኢንዱስትሪ ፖርክ ቅጥር ግቢ አሁንም በርካታ ሼዶች ገና በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ ቢሆንም  በከፊል የተጠናቀቁ ጥቂት ሼዶች ግን ከወዲሁ የምርት ተግባር ሲያከናውኑ ይስተዋላሉ።

Avocado-Anbau in Tigray
ምስል DW/S. Wegayehu

በአሁኑ ወቅት በፖርኩ የምርት አገልግሎት በጀመሩ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ  ባገኙት የሥራ ዕድል ተቀጥረው በመሥራት ላይ ከሚገኙት ወጣቶች መካከል አንዷ የሆነችው  ትዕግሥት ፋንታ  ወደ ፖርኩ የተቀላቀለችበትን አጋጣሚ እንዲህ ትገልጻለች።

የይርጋዓለም የተቀናጀ የግብርና አግሮ ኢንዱስትሪ ፖርክ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 152 ሼዶች ይኖሩታል የሚሉት የፖርኩ የኦኘሬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ በእነኚሁ ሼዶች ውስጥ የሚቋቋሙ ኢንዲስትሪዎች ከ393 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች አዳዲስ የሥራ ዕድል ያስገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አቶ ብርሃኑ ገልፀዋል።

የፓርኩ መገንባት ከሥራ ዕድል ጠቀሜታው በተጨማሪ  የሲዳማና የጌዲኦ ዞኖችን ጨምሮ በዙሪያው በሚገኙ አምራቾችና ኢንዱስትሪዎች መካከል  የገበያ ሠንሠለት ለመፍጠር እንደሚያስችልም ነው አቶ ብረሃኑ የሚናገሩት። ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ወደ እዚሁ የገበያ ሠንሠለት ይቀላቀላሉ ተብለው ከሚጠበቁ አርሶ አደሮች መካከል  የዳጊያ ቀበሌ ነዋሪው አቶ መንግሥቱ አሊቶም ይገኙበታል።

በአሁኑ ወቅት በማሳቸው ላይ የሚኘውን የቡናና የአቮካዶ ምርት በመሰብሰብ  ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ በዩኒየን አማካኝነት ለኢንዱስትሪዎች ለማቅረብ በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ የሚናገሩት አቶ መንግሥቱ በዚህም እንደበፊቱ የምርታቸው የዋጋ ተመን በደላላዎች ይወሰንብኛው የሚል ሥጋት አይኖርብኝም ይላሉ። በእርግጥ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፖርክ በቀጥታ ከውጭ ንግድ ጋር የተሳሰረ በመሆኑ ጥራቱንና ደረጀውን የጠበቀ የአመራረት ሂደት መከተል ለድርድር የማይቀርብ ስለመሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። 

ወደ ምርት አገልግሎት እየገባ የሚገኘው የይርጋዓለም የተቀናጀ የግብርና አግሮ ኢንዱስትሪ ፖርክ  በቀጣይ ሊያጋጥሙት ከሚችሉት ተግዳሮቶች መካከል የዓለም ገበያ የሚፈልገውን ጥራትና ደረጃ  አሟልቶ የመገኘት ጉዳይ ሊጠቀስ ይችላል። የፖርኩ የኦኘሬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ኤኬቴ ግን  ከሼድ ግንባታ እስከ ምርት አቅርቦት ድረስ ያለውን ሂደት ደረጀውን በጠበቀ መንገድ ለማከናወን በቅንጅት እየተሠራ እንደሚገኝ ይናገራሉ። 

ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ

ነጋሽ መሐመድ