1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደመራ በዓል አከባበር በጀርመን

ሐሙስ፣ መስከረም 20 2008

በፍራንክ ፈርት ጀርመን ደብረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ-ክርስትያን የደመራ በዓል በደማቅ ተከብሮአል ። የደመራ በዓል ሲከበር ከተለያዩ የጀርመን ከተሞች የተሰባሰቡ ኢትዮጵያዉያን እና ኤርትራዉያን ምዕመናን እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶችና የከተማዋ ነዋሪዎች በሥነ- ስርዓቱ ላይ ተገኝተዉ ነበር።

https://p.dw.com/p/1GgmK
Meskel Fest in Frankfurt
ምስል DW/A. Tadesse

የደመራ በዓል አከባበር በጀርመን

እንደ ብዙዎች ግምት በዚህ ክብረ በዓል ከ1000 በላይ ሰዉ ነበር የተገኘዉ። በዚህ ዝግጅታችን በፍራንክፈርት እጅግ በርካታ ኢትዮጵያዉያን የተገኙበትን የደመራ በዓል ቃኝተን በአሁኑ ወቅት በአዉሮጳ ብሎም በጀርመን ስላለዉ የስደተኝነት ቀዉስ እናያለን። ምዕመኑ የኢትዮጵያ ባህላዊ ልብሱን ለብሶ ደመራዉ ወደተመረበት ፍራንክፈርት ከተማ ዉስጥ ወደ ሚገኘዉ ደብረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ-ክርስትያን መትመም የጀመረዉ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ ነዉ። በኢትዮጵያና በጀርመን ሰንደቅ ዓላማ መሃል የቆመዉ በግምት ወደ ስምንት ሜትር ቁመት ያለዉ አደይ አበባን በመሰለ ቢጫ አበባ የተንቆጠቆጠዉ ደመራ፤ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ለብሶ፤ ዙርያዉን በርከት ያለ ችቦ ተደርድሮበታል። በፍራንክፈርት መሃል ከተማ በሚገኘዉ ይህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስትያን ደመራን በዓል ሲያከብር ሁለት አስርተ ዓመታት ያስቆጠረ በመሆኑ ለከተማዉ ነዋሪ የኢትዮጵያዉያኑ የደመራ በዓል እንዲሁም አከባበር ባህላዊዉ የአበሻ ልብስ አዲስ አይደለም። በየዓመቱም የከተማዉ ከንቲባ አልያም ሌሎች ከፍተኛ የጀርመን ባለስልጣናት በክብር እንግድነት ይጋበዙበታል። ዘንድሮ የፍራንክፈርቱ ደመራ በዓል ላይ በክብር እንግድነት የተጋበዙት አዲስ ተሾመዉ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጀነራል ምህረትዓብ ሙሉጌታም ነበሩ። ከቀኑ አስር ተኩል ሲሆን ምዕመናኑ ትልቁን ደመራ ከበዉ ዘማሪዎች ልብሳቸዉን ለብሰዉ ደመራዉ በተደመረበት ሰፊ ሜዳ ላይ ተሰበሰቡ። ክብረ በዓሉም በፍራንክፈርት ደብረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ-ክርስትያን አስተዳዳሪ በአባ ኃይለመለኮት ተስፋ ማርያም በይፋ ተጀመረ።የደመራን በዓል የኢትዮጵያ ቀን ብለን ስናከብረዉ ዓመታት ተቆጥረዋል፤ ሲሉ በመቀጠል ንግግር ያደረጉት በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን ዋና ተጠሪ ሊቀነ ካህናት ዶክተር መራዊ ተበጀ የመስቀል በዓልና የደመራ በዓል

Deutschland, Meskel-Fest in Frankfurt
ምስል A. Tadesse

ምስጢርን አስተምረዋል። የመዘምራኑ ወረብና ዝማሬ ምዕመናኑ ብቻ ሳይሆን ባህል ትዉፊቱን ለማየት የመጣዉን ጀርመናዊም ሆነ በአካባቢዉ ያልፍ ያገድም የነበረዉን መንገደኛ ወደ ክብረ በዓሉ ጋብዞ ነበር ያመሸዉ። ፊልም የሚቀርፅ ፎቶግራፍ የሚያነሳ ጀርመናዊ ቁጥርም ቀላል አልነበረም።ደመራዉ ተለኩሶ ዘማሪያን በከበሮ በጽናጽል እና በእልልታ አካባቢዉን ሲያደምቁ በፍራንክፈርት ደብረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ-ክርስትያን አስተዳዳሪ በአባ ኃይለመለኮት ተስፋ ማርያም ኢትዮጵያዉያን ስለ መስቀል በዓል ልዩ ፍቅር አለን ሲሉ ተናግረዋል።

« የመስቀል በዓል ደመራ የመታሰብያ በዓል ነዉ። በፍራንክፈርት ደግሞ በየዓመቱ እንደዚሁ ከ 18 ዓመት ጀምሮ በታላቅ ነዉ የሚከበረዉ። በመጀመርያዎቹ ዓመታት የጀርመን ከፍተኛ ባለስልጣናት፤ የፍራንክፈርት ከተማ ምክት ከንቲባ እየመጣ አብሮን አክብሮአል። በክብረ በዓሉ ላይ የሚገኘዉም ሕዝብ እጅግ ብዙ ነዉ። የደመራዉም አከባበር ልክ እንደ ሀገራችን ነዉ ደስ ይላል፤ ሕዝቡም ደስተኛ ነዉ። »

በአባ ኃይለ መለኮት በጀርመን ብሎም በአዉሮጳ የወቅቱ ያለዉን የስደት ቀዉስ በተመለከተ ቤተ-ክርስትያኒቱ ምዕመኑ ሁሉ ስለ ችግሩ እንደሚያስብ እንደሚፀልይ ተናግረዋል።

Meskel Fest in Frankfurt
ምስል DW/A. Tadesse

« በእዉነቱ የስደተኛ ችግር በጣም የሚያሳዝን ነዉ። ሁላችንም አይተናል፤ ሰምተናል፤ በተለይ በመካከለኛዉ ምሥራቅ ያለዉ ችግር ፤በሶርያ ፤ በአፍጋኒስታን፤ በኤርትራ እንደዚሁ ከባድ የስደት መከራ ነዉ ያለዉ። ጀርመኖችም ሁኔታዉ የሁለተኛዉን ዓለም ጦርነት ያስታዉሳል ነዉ የሚሉት፤ በቤተ-ክርስትያናችን እንፀልያለን። በሊቢያ ለሞቱት ወገኖቻችንም ፀሎት አድርገናል። አሁንም ፀሎት እናደርጋለን። የሶርያ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ቤተ-ክርስትያናቸዉ ተቃጥሎ እምነት መፀለያ አተዉ፤ እኛ ደግሞ እዚህ እንዲህ ተከብረን ሲታይ ታላቅ እድል ታላቅ በረከት ነዉና ፤ እነሱን በዚህ እለት እናስባቸዋለን። በአሁኑ ጊዜም ከአዉሮጳ ሀገራት በበለጠ ስደተኞችን የምትቀበለዉ ጀርመን ናት። እኛም እዚህ መብታችን ተከብሮ የምንኖርበት ሀገር ነዉ። ቤተ-ክርስትያናችንን አዉደ ምህረቱን የሰጡንም ጀርመኖች ናቸዉ፤ እናመሰግናቸዋለን፤ ጀርመንን ይባርክልን»

በበዓሉ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት በፍራንክፈርት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጀነራል ምህረትዓብ ሙሉጌታን እንኳን አደረሶት ይህን ክብረ በዓል በጀርመን ደምቆ ሲያዩ ምን አሉ ስል ነበር የጠየቅናቸዉ።

« እንኳን አብሮ አደረሰን! ይሄ እንግዲህ በሀገራችን በመላዉ ኢትዮጵያ በድምቀት የሚከበር አንዱ በዓል ነዉ። ይሄ የሁሉም የክርስትና ኃይማኖት ተከታዮች በዓል ስለሆነ በጣም ደስ የሚል ነዉ። በዚህ በተለይ በዉጭ ፤ በጀርመን ሃገር ሁሉ ተሰብስቦ እንዲህ ሲያከብር ሳይ በጣም ነዉ ደስታ የተሰማኝ። ለኔ ደግሞ በተለይ በጀርመን ሳከብር የመጀመርያዬም ስለሆነ በጣም ተደስቻለሁ። ዘንድሮ 2008 ዓ,ም ትልቅ ዓመት ነዉ፤ ይህ እዚህ የሚታየዉ ደስታና ሕብረት ወደ ሀገራችንም እንደዚሁ በሕብረት በአንድነት የሚሳተፉበት ፤ ሕብረቱን ይዘዉ ለሀገራቸዉ አስተዋዖ የሚያደርጉበት ዓመት እንደሚሆን ተስፋ አለኝ። » ቆንስላ ጀነራል ምህረትዓብ ሙሉጌታ፤ በጀርመን ብሎም በአዉሮጳ ስለሚታየዉ የስደተኝነት ቀዉስ በተመለከተ፤ ጀርመኖች ከሌላዉ የአዉሮጳ ሀገራት ቀደም ብለዉ ለስደተኞች በራቸዉን ከፍተዋል፤ ይህ በጣም የሚያስመሰግናቸዉ ነዉ። በዓለም ላይ ሀገራት የሚሰደዱ ሰዎችን ተቀብሎ ማስተናገድ ዓለማቀፍ ሕግ ነዉ። »

Meskel Fest in Frankfurt
ምስል DW/A. Tadesse

ደብረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ-ክርስትያን ዘማሪ አስካለ ማርያም ደመራን በፍራንክፈርት ስታከንር ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ነዉ።

« በዓሉ ቆንጆ ነዉ። በድምቀት አክብረናል፤ የተለያዩ ኃይማኖታዊ ክንዉኖችን በማድረግ አሳለፍን የከርሞ ሰዉ ይበለን።»

በጀርመን ሀገር ሲኖር 15 ዓመት የሆነዉ ሌላዉ የበዓሉ ታዳሚ የፍራንክፈርት ነዋሪ ዮሃንስ አማን ነዉ ዮኃንስ በስደት ሀገር ሆኖ ባህልን እንዲህ ማየቱ አስደሳች ነዉ ሲል ይገልጻል።

«በጣም የሚያስደስት ነዉ። በርካታ ኢትዮጵያዉያን ነዉ የተገኙት። በስደት ሀገር ላይ ሆነን እንደዚህ በዝማሪ በተለያዩ ባህላዊ ክንዉኖች ታጅበዉ ህዝቡም፤ የሀገር ባህል ልብሱን ለብሶ ተዉቦ ነዉ የተገኘዉ። እዚህ የተወለዱትንም ልጆቻችንን ባህላቸዉንና ወጋቸዉን እንዲያዉቁ የባህል ልብስን አድርገዉ ነዉ የመጡት፤ በጣም ደስ ይል ነበር።»

ጀርመናዉያን ይህን በዓል እንዴት ነዉ የተከታተሉት? « በጣም ደስ ይላቸዋል። ግማሾቹ በመንገድ ሲያልፉ ይህን በዓል አይተዉ የገቡ አሉ። ባቡር ዉስጥ ሆነዉ ፎቶ ሲያነሱም አይቻለሁ»

Meskel Fest in Frankfurt
ምስል DW/A. Tadesse

ጀርመናዊዉ ዮሴፍ ዩስት መስቀል በዓልን በፍራንክፈርት ሲያከብሩ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነዉ። ክብረ በዓሉ እጅግ ማራኪ ነዉ ባይ ናቸዉ። ኢትዮጵያዉያንን ይወዳሉም።

«እጅግ ግሩም ነዉ። ደመራን ሳከብር ይህ የመጀመርያዬ አይደለም። ባለፈዉ ዓመት እዚህ ከጓደኛዬ ጋር ሆኜ አክብሪአለሁ። ባህሉ እጅግ አስደስቶኛል። የዉጭ ሀገር ባህልን እወዳለሁ። በተለይ የኢትዮጵያዉያን ባህል ሥነ-ምግባርን በጣም እወዳለሁ። ከኢትዮጵያዉያን ጋር መሆን እጅግ ያስደስተኛል።»

በጀርመን ካልስሩወ ከተማ ምዕራፈ ቅዱሳን አቡነ ተክለ ኃይማኖት ቤተ-ክርስትያን አገልጋይ መላከ ስብሃት ተክሌ ሲራክ ክብረ በዓሉ ኢትዮጵያ እንዳሉ ያህል እንደተሰማቸዉ ነዉ የገለጹት።

« በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ነዉ ያከበርነዉ። ኢትዮጵያዉያን ከሀገራቸዉ የወጡ አይመስልም። በጣም በደስታ ነዉ ያከበሩት ። በዚህ በባዕድ ሀገር ይህን ያህል ሰዉ ይገኛል ብዬ አልገምትም። ነገር ግን ሁሉም ቦታ ለሁሉም ሀገሩ ነዉ። ክርስትናን ሀገር ድንበር አይገድበዉም። በየትም ቦታ እግዚአብሄር አለ ፤ በየትም ቦታ ይመለካል። ምዕመናኑ ስላሉ ነዉ አባቶች ወደዚህ የመጡት ፤ ምዕመናኑ ስላሉ ነዉ ቤተ-ክርስትያንዋ ወደዚህ የመጣችዉ። በዚህ መልኩ በድምቀት ተከብሮአል። ይህ በዓል ብዙ እሴት ያለዉ ነዉ፤ ለዚህ ሀገርም ቢሆን ጀርመን የክርስትያኖች ሀገር ነች ፤ እና ነዋሪዉ ይህን ሲያይ ይደሰታል።»

መላከ ስብሃት ተክሌ ሲራክ፤ ጀርመን በርካታ የዉጭ ዜጋ መኖሩን ሀገሪትዋ ለስደተኞች በርዋን መክፈትዋ በተመለከተ፤ የጀርመን ታላቅነት ያሳያል ሲሉ ነዉ የገለፁት።

«ይህ ታላቅነታቸዉን ያሳያል። አንደኛ ሰብዓዊ ርህራሄአቸዉን ነዉ የሚያሳየዉ። ማንም የተቸገረዉን ሁሉ እንዲረዳ በእግዚአብሄር የታዘዘ ነዉ። ስለዚህ ጀርመናዉያን ከክርስትናዉም አልፎ ሰብዓዊነታቸዉን ነዉ ያሳዩት። ይህ ጉዳይ የነሱ ጉዳይ ሆኖ የሚያስፈልገዉን ነገር አሟልተዉ ተቀብለዉ አስተናግደዉ ማስቀመጣቸዉ በጣም የሚደነቁ ህዝቦች ናቸዉ። ይህን በዓላችንን እንኳ ስናይ ቀላል ነገር አይደለም፤ ቤተ-ክርስትያናቸዉን ሰጥተዉ አደባባያቸዉን ፈቅደዉ፤ በምንፈልገዉ፤ መልኩ፤ ደመራዉ ተደምሮ፤ ተለኩሶ፤ ዙርያዉን ሆነን ጮክ ብለን እየዘመርን፤ ሁሉ ነገር ሳይጓደል እንድናከብር በማድረጋቸዉ፤ እጅግ በጣም ሊደነቁ የሚገባቸዉ ናቸዉ። ከነሱ ብዙ ነገርን መማር እንችላለን። አርዓያችን ናቸዉ ማለት ይቻላል። »

Meskel Fest in Frankfurt
ምስል DW/A. Tadesse

ወ/ሮ መብራት በፍራንክፈርት ደብረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ-ክርስትያን ስትመሰረት ጀምሮ ወደዚች ቤተ ክርስትያን እንደሚሄዱ ነዉ የነገሩን። «ይህች ቤተ-ክርስትያን ስትመሰረት ጀምሮ ወደዚህ ቤተ- ክርስትያን እመጣለሁ። ለ 22 ዓመት ማለት ነዉ። በጣም ደማቅ በዓልን ነዉ ያከበርነዉ»

ከሃይድል በርግ ከተማ ደመራን ለማክበር ወደ ፍራንክፈርት የመጡት ወ/ሮ መሰርት በበኩላቸዉ ደመራን ሲያከብሩ ሀገራቸዉ እንዳሉ ያህል ባህላቸዉን ወጋቸዉን እንዳስታወሳቸዉ እንዲሁ ተናግረዋል። እዚሁ በጀርመን በቩልስ ቡርግ ከተማ ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስትያን አስተዳዳሪ መላከ ጽዮን አባ አብረሃም ገብረ ሚካኤል በበዓሉ ድምቀት ተደስተዋል፤ ዶቼ ቬለን ደግሞ የዘወትር አድማጭ መሆናቸዉን ነግረዉናል።

በተለያዩ የጀርመን ከተሞች የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያዉያን በፍራንክፈርት ደብረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ-ክርስትያን የደመራ በዓል አከባበር ሥነ-ስርዓት ሙሉ ዝግጅት የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ያድምጡ!

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ