1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ሱዳንና የተመድ ዉዝግብ

ረቡዕ፣ መጋቢት 3 2006

ፕሬዝዳንት ኪር ባለፈዉ ታሕሳስ በደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሐላፊዎችን ከመንግሥት እኩል ሐገር ለመምራት ይሞክራሉ በማለት ወንጅለዋቸዉ ነበር።በቀደም ጁባ ዉስጥ ለተሰለፉት ወጣቶች ንግግር ያደረጉት ምክትል ፕሬዝዳንት ጄምስ ዋኒ ኢጋ የአለቃቸዉን አባባል ደገሙት

https://p.dw.com/p/1BOhm
ምስል UNMISS/Handout via Reuters

ደቡብ ሱዳን የሠፈረዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠላም አስከባሪ ሠራዊትUNMISSካሚዮኖች የጦር መሳሪያ ጭነዉ መያዛቸዉ የጁባ መንግሥትንና የዓለም አቀፉን ድርጅት ዉዝግብ አባብሶታል።የፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር መንግሥት የጦር መሳሪያዉ የመንግሥትን ጦር ለሚወጉት አማፂያን የተላከ ነበር በማለት የሠላም አስከባሪዉን ሰራዊት ሐላፊዎች ወንጅሏል።የድርጅቱ ባለሥልጣናት መሳሪያዉ የተጫነዉ በስሕተት መሆኑን ቢያስታዉቁም የተቀብላቸዉ የለም።ባለፈዉ ሰኞ ጁባ አደባባይ የተሠለፉ ወጣቶችም በደቡብ ሱዳን የድርጅቱን ተወካይ በግልፅ አዉግዘዋል።ሒልከ ፊሸር የዘገበቺዉን ነጋሽ መሐመድ እንደሚከተለዉ አጠናቅሮታል።

«ሒልዳ ጆንሰን ይዉድሙ፤ ሒልዳ ጆንሰን ሒዱልን» ነዉ የሚለዉ ሠልፈኛዉ።ወይዘሮ ሒልዳ ጆንሰን ደቡብ ሱዳን የሠፈረዉ የተባበሩት መንግሥታት ሠላም አስከባሪ ሠራዊት (UNMISS) ኃላፊ ናቸዉ።ጆንሰንን የሚያወግዙት ሰልፈኞች ደግሞ የሳልቫ ኪር መንግሥት ነዉ ያደራጃቸዉ የጁባ ወጣቶች ናቸዉ።

የኪር መንግሥትና የዓለም አቀፉ ሠራዊት ሐላፊዎች ጠብ የተጀመረዉ የደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች መንግስት እና አማፂ በሚል ለሁለት ተከፍለዉ ያቺን ደሐ-አዲስ ሐገራቸዉን የሚወድመዉን ጦርነት ባቀጣጠሉ ማግሥት ነበር።የጎሳ መልክና ባሕሪ የተላበሰዉን ጦርነት የሸሹ ከ80ሺሕ የሚበልጡ ሰላማዊ ሰዎች እሳካሁን ድረስ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቅጥር ግቢዎች ዉስጥ እንደተሸሸጉ ነዉ።ዉጊያዉ እንደተጀመረ ዲንካዎች የሚያዙት የመንግሥት ጦር ጁባ የሚገኘዉን የዓለም አቀፉን ድርጅት ቅጥር ግቢ ለመዉረር ሲሞክር ባአብዛኛዉ የኙዌር ጎሳ አባላት ቅጥር-ግቢዉ መሸሸጋቸዉን የሚያዉቁት የድርጅቱ ሐላፊዎች ጦሩ እንዳይገባ ይከለክላሉ።

Hilde Johnson Leiterin UNMISS-Friedensmission Südsudan OVERLAY
ምስል Charles Atiki/AFP/Getty Images

የኪር መንግሥት የዓለም አቀፉን ድርጅት ባለሥልጣናትን ካማፂያኑ ጋር ይተባበራሉ በማለት መወንጀሉን ያኔ ጀመረ።ባለፈዉ አርብ ደግሞ ቤንቱዊ በባለችዉ ከተማ ለሰፈረዉ ለጋና ሠራዊት ሥንቅ ያጓጉዛሉ የተባሉ ካሚዮኖች የጦር መሳሪያ ጭነዉ ሲጓዙ መያዛቸዉ ዉግዘት-ወቀሳዉን አናረዉ።

«ታሕሳስ 15 2013 ጁባ ዉስጥ የተደረገዉን መፈንቅለ መንግሥት ዩኒሚስ ለማቀነባበሩ እና ሙከራዉን ለማሳካት ከሪክ ማቸር ጎን ለመቆሙ ምንም ጥርጥር የለዉም።»

ሠልፍኛ ወጣቶቹን ካስተባበሩት አንዱ።የጁባ መንግሥት እንደሚለዉ የመንግስት ጦር ባልደረቦች መኪኖቹን ሲፈትሹ በርካታ የጦር መሳሪዎችና የሚቀበሩ ፈንጂዎች አግኝተዋል።የጦር መሳሪዎቹ ለአማፂያኑ የተላኩ መሆናቸዉን የመንግሥት ባለሥልጣናት በግልፅ ነዉ የሚናገሩት።

ፕሬዝዳንት ኪር ባለፈዉ ታሕሳስ በደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሐላፊዎችን ከመንግሥት እኩል ሐገር ለመምራት ይሞክራሉ በማለት ወንጅለዋቸዉ ነበር።በቀደም ጁባ ዉስጥ ለተሰለፉት ወጣቶች ንግግር ያደረጉት ምክትል ፕሬዝዳንት ጄምስ ዋኒ ኢጋ የአለቃቸዉን አባባል ደገሙት።«የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቅኝ ተገዢዎች ሊያደርገን ነዉ የሚፈልገዉ።ቅኝ የሚገዙን ከሆነ እንደምታዩኝ ሽማግሌ ብሆንም ቅኝ አገዛዝን አልቀበልም።ጫካ ገብቼ እተዋጋሁ እሞታለሁ።»

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣናት እንደሚሉት ባለፈዉ ከተያዙት የጦር መሳሪዎች ተቀባሪ ፈንጂ የተባሉት ፈንጂ ሳይሆኑ የኦክሲጂን ጋኖች ናቸዉ።ሌላዉ ግን ጦር መሳሪያ መሆኑን የድርጅቱ ባለሥልጣናት አልካዱም።መሳሪዎቹ ግን ለጋና ወታደሮች የተላኩ ናቸዉ ባይ ናቸዉ።ይሁንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከዚሕ ቀደም ከደቡብ ሱዳን ጋር ባደረገዉ ዉል መስረት ለሠላም አስከባሪዉ ሠራዊት የሚላኩ ጦር መሳሪያዎች መጓጓዝ ያለባቸዉ በአዉሮፕላን ብቻ ነዉ።

Konflikt im Südsudan Ankunft bengalische UN-Soldaten 31.12.2013
ምስል Reuters

አሁን ለምን በመኪና ተላከ ነዉ ጥያቄዉ።የድርጅቱ ቃል አቀባይ አርየነ ኩዋንቲየር ሥሕተት ይሉታል።«ሥሕተት ስርተናል።ይሕን ተናግረናልም።ምንድነዉ የሆነዉ የጋና ጦርን ሥንቅና ትጥቅ በመጫኑና በማጓጓዙ ሒደት ሥሕተት ተፈፅሟል።»

በጀርመኑ ፖለቲካ ጥናት ተቋም SWAየደቡብ ሱዳን አጥኚ አኔተ ቬበር እንደሚሉት ግን ተሳሳትን ማለት ብቻዉን በቂ አይደለም «መሳሪያዉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መኪኖች መጫኑ ድርጅቱን መጉዳቱ አይቀርም።ግን ሀ,ይሕ እንዴት ሊሆን ቻለ።ለ,መሳሪዎችን ከድርጅቱ ሠራተኞች መሐል አንዱ ቢጭናቸዉ እንኳን ከድርጅቱ ሐላፊዎች ቁጥጥርና ክትትል እንዴት ሊያመልጥ ቻለ?»ላሁኑ መልስ የለም።

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ