1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ሱዳን ህዝበ ውሳኔና የአቢዬ ዕጣ ፈንታ

ሐሙስ፣ ኅዳር 2 2003

አሜሪካ ከትላንት በስቲያ ይዛ ብቅ ያለችው የመፍትሄ ሀሳብ ዋንኛዋን አጨቃጫቂ ቦታ የሚመለከት ነው--አቢዬን። በደቡብ ሱዳን ጥር 9/2010 ህዝበ ውሳኔ ይካሄዳል ተብሎ በመጠበቅ ላይ ቢሆንም በነዳጅ ዘይት በከበረችው አውራጃ አቢዬ ፤ ምርጫው የጊዜ ሰሌዳውን ተከትሎ የሚከናወን አይመስልም።

https://p.dw.com/p/Q6NG
ምስል DW/AP

የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት 2011 በገባ በ11ኛው ቀን ላይ ሊካሄድ ቀጠሮ በተያዘለት የደቡብ ሱዳን ህዝበ ውሳኔ ላይ ከሚያስማሙት ይልቅ ልዩነቶች ፈጠው ወጥተዋል። ቀኑ እየተቃረበ በመጣ ቁጥር ደቡብንናሰሜን ሱዳኖችን የሚለያዩት ጉዳዮች መበርከት ይዘዋል። አንዷም አቢዬ ናት። አሜሪካ ባለፈው ማክሰኞ ያሰማችው የመፍትሄ ሀሳብ በመጪው ጥር የሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ አቢዬን ሳያካትት እንዲሄካሄድና ሁለቱ ወገኖች ውይይታቸውን እንዲቀጥሉ የሚል አማራጭ ነበር። በዓለም ዓቀፉ የግጭት አጥኚ ቡድን የሱዳን ጉዳይ ተንታኝ ፉአድ ሂክማት ከአሜሪካ የተሰማውን አማራጭ መፍትሄን ይጋሩታል።

ድምጽ

«የአቢዬ ጉዳይ ችግር እየሆነ መጥቷል። ሁሉም ወገን በአቢዬ ህዝበ ውሳኔው እንዲካሄድ ዝግጅት እያደረገ ያለ ይመስለኛል። የአቢዬ ህዝበ ውሳኔ ከደቡብ ሱዳን ጋር ጎን ለጎን አንድ ላይ የሚካሄድ እንደሆነ ነው ሁኔታዎች የሚያሳዩት። ይህ ነገር አሁን ፈጽሞ የሚሆን አይመስለኝም። ይህን ለማድረግ ከሁለቱም ወገኖች መጠነ ሰፊ የሆነ ፖለቲካዊ ፍቃደኝነትን የሚፈልግ ጉዳይ ነው።»

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ፊሊፕ ክሮውሌይ ገና የተጠናከረ ውይይትና ድርድር ያስፈልጋል፤ የአቢዬ ጉዳይ ትንሽ ይቆይ ሲሉ ነበር ማክሰኞ መግለጪያ የሰጡት። አወዛጋቢዋ አቢዬ ላይ ሁለቱም ወገኖች ደቡቡና ሰሜኑ፤ የየራሳቸውን የመፍትሄ ሀሳቦች አቅርበዋል። ከሰሜኑ የሚያደሉት ዘላኖቹ እጣፈንታቸው አንዱ አወዛጋቢ ጉዳይ ሆኗል። የደቡብ ሱዳን አስተዳደር ለሰሜኑ ካሳ መክፈልና አቢዬን ወደርሱ መጠቅለል ይፈልጋል። በእርግጥ በሁለቱ ወገኖች የቀረቡት የመፍትሄ ሀሳቦች ተቀባይነትን አላገኙም። የሱዳን ጉዳይ ተንታኝ የሆኑት ፉአድ ሂክማት አቢዬ ከህዝበ ውሳኔው ውጪ መሆን አለባት ይላሉ።

ድምጽ

«በሁለቱም ወገኖች የቀረቡት የመፍትሄ ሀሳቦች ተቀባይነትን ካላገኙ በማህበረሰቡም ዘንድ ተቀባይነትን አያገኙም። በተለይም በዘላኑ የሜሴሪያ ማህበረሰብ ዘንድ። በእርግጥ ፖለቲካዊ መፍትሄዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ከመፍትሄዎቹ አንዱ የአቢዬን ጉዳይ በአጠቃላይ ከህዝበ ውሳኔው ውጪ ማድረግና ለብቻው መፍትሄ መፈለግ ነው። አቢዬ በህዝበ ውሳኔው መካተት አለባት ካሉ፤ ይህ ወደ ገደል የሚወስድ እርምጃ ነው። በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። ምክንያቱም በአቢዬ በሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ ላይ ድምጹን መስጠት የሚችለው ማን ነው በሚለው ላይ ሁለቱም ወገኖች ከስምምነት አልደረሱም። ዘላኑ የሜሴሪያ ማህበረሰብ በህዝበ ውሳኔው ካልተካተተ የአጠቃላዩ የሰላም ስምምነት ጉዳይ አደጋ ውስጥ መግባቱ አይቀርም።»

በእርግጥ አሜሪካ የደቡብ ሱዳኑ ህዝበ ውሳኔ መካሄድ አለበት የሚለው አቋሟ የጠራና ግልጽ ነው። የጣለችውን ማዕቀብ እያራዘመች ያለችበትም ምክንያት አንድም ህዝበ ውሳኔው ላይ ችግር እንዳይፈጠር እንደሆነ ትናገራለች። በየጊዜው የመፍትሄ ሀሳብም ትሰነዝራለች። የባለፈው ማክሰኞ በእርግጥ የመጀመሪዋ አይደለም።

ድምጽ

«አሜሪካኖቹ ይዘው ከመጡት ሀሳቦች አንዱ አቢዬን ለሁለት በመክፈል ሰሜን አቢዬን ወደ ሰሜን ሱዳን፤ ደቡቡን ደግሞ ወደ ደቡብ ሱዳን እንዲካለሉ የሚል ነበር። ይህ ተቀባይነትን አላገኘም። እናም አሁን መፍትሄው እንዴት ይገኛል የሚለው ነው መሰረታዊው ነጥብ። ዋናው ነገር የሚመስለኝ ሁለቱ ወገኖች ህዝበ ውሳኔው ከተካሄደ በኋላ ቀጣዩ እርምጃ ምን መሆን እንዳለበት ቁጭ ብለው እንዲነጋገሩ ጫና ሊደረግባቸው ይገባል። ምክንያቱም ከህዝበ ውሳኔው መካሄድ በኋላ የዜግነት ጥያቄንና የነዳጅን ጉዳይ በተመለከተ፤ በአጠቃላይም የኢኮኖሚውንና ሌሎች በጋራ ሊጠቀሟቸው በሚችሏቸው ነገሮች አንጻር መነጋገርና የአቢዬን ጉዳይ በተመለከተ ሌሎች መንገዶችንም ሊያዩ የሚችሉበት ዕድል ይኖራልና ነው።»

አቢዬ አሁንም እንዳወዛገበች አለች። ህዝበ ውሳኔው የሚካሄድበት ቀን እየተቃረበ ነው። ብዙዎች አቢዬን የሱዳኗ ካሽሚር ይሏታል። መፍትሄ ሳይሰጠው የዘለቀው የሷ ጉዳይ መጨረሻው ጦርነትን ያቀጣጥል ይሆን? የብዙዎች ስጋት ነው።

መሳይ መኮንን

ሂሩት መለሰ