1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ሱዳን ቀውስ መባባስ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 4 2007

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዩኒቲ ከተባለዉ የደቡብ ሱዳን ግዛትን ለቅቆ ለመውጣት በመገደዱ ከ300,00 በላይ ሰዎች ለችግር መጋለጣቸውን አስታወቀ። ባለፈው ሣምንትም ድንበር የለሽ ሐኪሞች የተሰኘው ግብረ-ሠናይ ድርጅት ግዛቲቱን ለቅቆ መውጣቱ ተዘግቧል።

https://p.dw.com/p/1FOlt
Zeltlager Rückkehrer Juba Südsudan
ምስል Jared Ferrie

በደቡብ ሱዳን የዩኒቲ ግዛት ከሚያዝያ አጋማሽ ጀምሮ የተቀሰቀሰው ግጭት ባለፉት አስራ ሰባት ወራት በአገሪቱ ከታየው ቀውስ ሁሉ የከፋ እንደ ሆነ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል። የደቡብ ሱዳን መንግስት ወታደሮች ከግዛቲቱ ዋና ከተማ ቤንቱ በነዳጅ ሐብት ወደ በለጸገችው እና ተቃዋሚዎች ወደ ሚቆጣጠሯት ሊር ከተማ በሚያደርጉት ዘመቻ ለአካባቢው ሕዝብ ሰብዓዊ እርዳታ የመስጠቱ ስራ ተቋርጧል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰራተኞች በአካባቢው ስራቸውን ለመከወን በመቸገራቸው 300, 000 የሚበልጥ ሕዝብ እርዳታ ማግኘት አይችልም። በደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተልዕኮ ቃል አቀባይ አሪያን ኩዊንቴር ቢሯቸው በመንግስት ወታደሮች ከእንቅስቃሴ መታገዱን ይናገራሉ።

Südsudan Bentiu Rebell Massaker Leiche GEPIXELT
ምስል Reuters

«በርካታ መንደሮች ተቃጥለዋል።ግድያ እየተፈጸመ ነው። እድሚያቸው እስከ የ10 አመት የሚደርስ ወንዶች ልጆች፤ሴቶችና ህጻናት እየታገቱ ነው። አስገድዶ መድፈር እየተፈጸመ ነው። ሰዎችም የመኖሪያ ቀያቸውን ጥለው ለመሰደድ ተገደዋል። ሰዎችን በማነጋገር እና ወደ ቦታው በመሄድ ምን እንደተፈጸመ ለማጣራት እየሞከርን ነው።ከግንቦት 30 ጀምሮ አካባቢውን ጥለን እንድንወጣ ታዘናል።በፍተሻ ኬላዎች የሚገኙ የመንግስት ወታደሮች በአካባቢው እንዳንቀሳቀስ አግደውናል። ይህ ደግሞ ግጭት ወደ ተቀሰቀሰበትና ሰብዓዊ እርዳታ ወደሚያስፈልግበት አካባቢ መድረስ ለሚፈልገው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በጣም አሳሳቢ ነው።»

ድንበር የለሽ የሐኪሞች (Doctors Without Borders) የተሰኘዉ የርዳታ ድርጅትምየመንግስት ወታደሮች በሊር ከተማ ላይ የሚሰነዝሩትን ጥቃት በመስጋት የህክምና አገልግሎቱን አቋርጦ መዉጣቱን ባለፈው ሳምንት አስታዉቆ ነበር። አለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴም በፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና በሪየክ ማቻር ደጋፊዎች መካከል የሚካሄደው የተኩስ ልውውጥ በሺ የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ለስደት ይዳርጋል በማለት ስጋቱን አስታውቋል። አሪያን ኩዊንቴር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሊር ከተማና አካባቢው ጠቅሎ በመውጣት ላይ መሆኑን ይናገራሉ።

«የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአማጽያኑ ይዞታ ከሆነችውና ከመንግስት ጥቃት የሚሰነዘርባት የሊር ከተማ የጸጥታ ሁኔታ ለሰራተኞቻችን ደህንነት አስተማማኝ ባለመሆኗ ሰዎቻችንን በማስወጣት ላይ እንገኛለን። ይህ ውሳኔ ከ300,000 በላይ ሰዎች ሰብዓዊ እርዳት በሚፈልጉበት ጊዜ የሚፈጸም በመሆኑ ስጋት ገብቶናል። የአካባቢው ነዋሪዎች ለሚቀጥለው ጊዜ ምግብ ለማምረት የእርሻ ስራ የሚሰሩበት ጊዜ ቢሆንም ሁኔታው ግን አልፈቀደም።»

የአማጺ ቡድን መሪው ሪየክ ማቻር የትውልድ ስፍራ የሆነችው የሊር ከተማ በመንግስት ጥቃት ዒላማ ውስጥ የወደቀችው ካለፈዉ ዓመት ጥር ጀምሮ ነው። ታጣቂዎች በአካባቢው ብቸኛ የሆነውን እና በድንበር የለሽ የሐኪሞች የግብረ-ሰናይ ድርጅት የተገነባን ሆስፒታል ማፈራረሳቸውንና አልጋ የያዙ ህመምተኞች መግደላቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የደቡብ ሱዳን ተልዕኮ ቃል አቀባይ አሪያን ኩዊንቴር በደቡብ ሱዳናውያን ላይ የበረታውን መፍትሄ ለማበጀት የአገሪቱ ፖለቲከኞች በጎርጎሮሳዊው 2013 ዓ.ም. የፈረሙትን ውል እንዲያከብሩ ይወተውታሉ።

Bildkombo Südsudan Riek Machar und Salva Kiir
ምስል Getty Images/Zacharias Abubeker/Ashraf Shazly/Montage

«ይህች አገር ሰላም እንደምትፈልግ ሁሉም ሰው ይስማማል። የዚህች አገር እና የተቃውሞ መሪዎች በአንድነት ተቀምጠው እንደ ጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር በ2013 ዓ.ም. የተፈረመውን ስምምነት ማክበር እና ተግባራዊ ማድረግ ይኖርባቸዋል።ሰላም የሚፈጠርበትን፤እርቅ የሚወርድበትን በሰላም የሽግግር መንግስት የሚመሰረትበትን እቅድ በማምጣት የዚህች አገር ሰዎች የነጻነትን እንዲያጣጥሙ ማድረግ ይኖርባቸዋል።»

የተፋላሚ ሐይላት ተወካዮች አዲስ አበባ ዉስጥ ለረጅም ጊዜ ባደረጉት ድርድር ተኩስ ለማቆም በተደጋጋሚ ቢስማሙም እስካሁን ገቢራዊ አላደረጉትም።ድርድሩም እንደተቋረጠ ነዉ።

ተንታኞች እንደሚሉት 17 ወራት ያስቆጠረዉ የደቡብ ሱዳን ጦርነት በርካታ ታጣቂ ቡድኖችን እየሚሳተፉበት የጎሳ ጦርነት ባሕሪ ይዟል።በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ መሰረት በአስር ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል። 12 ሚሊዮን የአገሪቱ ዜጎች የእርዳታ ጥገኛ ሲሆኑ 2.5 ሚሊዮን ያህሉ ደግሞ ከፍተኛ የምግብ እጥረት ገጥሟቸዋል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ