1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ሱዳን ቀውስ እና የናይሮቢው ውይይት

ሐሙስ፣ የካቲት 13 2006

የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖች ከአንድ ወር በፊት በአዲስ አበባ የተፈረመውን የተኩስ አቁም ደንብ በመጣስ ወሳኝ የነዳጅ ዘይት አምራች በሆነው የ«አፐር ናይል» ግዛት ዋና ከተማ፣ ማላካል ላይ ካካሄዱት ግዙፍ የጥቃት ዘመቻ በኋላ

https://p.dw.com/p/1BCEZ
Südsudan Rebellen 10.02.2014
ምስል Reuters

የከተማይቱ ቁጥጥር በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች መካከል መዋሉን የዜና ምንጮች አስታወቁ። ይህ በዚህ እንዳለ፣ ለውዝግቦች የመፍትሄ ሀሳብ የሚያቀርበው « ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ» ትናንት በናይሮቢ፣ ኬንያ ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ የፖለቲካ ተንታኞች እና ጠበብት ስለ ውዝግቡ ተወያይተዋል።

በደቡብ ሱዳን ሰሜን ምሥራቃዊቱን የማላካልን ከተማ ለመያዝ በተካሄደው ውጊያ ዓማፅያኑ ከፊል ከተማይቱን እና አየር ማረፊያውን እንደያዙ የዜና ምንጮች ቢዘግቡም ፣ በዚያ ያለው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ በወቅቱ ከተማይቱን ይኸኛው ወይም ያኛው ወገን ተቆጣጥሯታል ብሎ ማረጋገጥ እንደማይችሉ ቃል አቀባይ ጆ ኮትሬራስ አስታውቀዋል። አሁንም ገና ባላበቃው ውጊያ በማላካል የተመድ ቅጥር ግቢ ከተጠለሉት 20,000 ሰዎች መካከል 10 እንደተገደሉ ጆ ኮትሬራስ አክለው ገልጸዋል። የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖች ከአንድ ወር በፊትበአዲስ አበባ የተፈረመውን የተኩስ አቁም ደንብ በመጣስ የተካሄደውን ውጊያ መነሻ በማድረግ « ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ» የጠራው ስብሰባ የደቡብ ሱዳንን ውዝግብ ለማብቃት ዓለም አቀፉ ማህበረ ሰብ ባስቸኳይ ርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አስተላልፎዋል። የስብሰባው ተሳታፊዎች በጠቅላላ የደቡብ ሱዳን ውዝግብ በዚችው ሀገር ያለውን ሥር የሰደደ መንሥዔ ያጎላ መሆኑን ተስማምተዋል። የደቡብ ሱዳን ሰላም አፈላላጊ ጥምረት ምክትል ሊቀመንበር ላም ቱንግዋ ግዌይን ጎንግ ስለ ሀገራቸው ወቅታዊ ሁኔታ እንዳስረዱት፣ የተፋላሚዎቹ ወገኖች ዓላማ የሚቆጠጠሩትን ቦታ ለማስፋቱ ተግባር ትኩረት ሰጥተዋል።

Südsudan Rebellen 10.02.2014
ምስል Reuters

« የኃይሉ ተግባር አሁንም እንደቀጠለ ነው። የሰላሙ ጥረት እየተካሄደ ባለበት በዚሁ ወቅት ተፋላሚዎቹ ወገኖች ተጨማሪ ቦታዎችን ለመቆጣጠር የሚቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ ነው። እያንዳንዱ ቡድን ትልቅ ትኩረት የሰጠው በሰላሙ ድርድር ወቅት የበላዩን እጅ ይዞ ለመቅረብ የተቆጣጠረውን ቦታ ማስፋት ለሚለው ዓላማ ነው። »

መነሻው ባለፈው ታህሳስ ወር በፕሬዚደንቱ ተቀናቃኝ እና የቀድሞ ምክትል ፕሬዚደንት ሪክ ማኸርና ደጋፊዎቻቸው ተካሄደ የተባለው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የሆነው ደም አፋሳሹን ውዝግብ ለማብቃት በአዲስ አበባ የቀጠለው አዳጋቹ የሰላም ድርድር አካሄድ ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች በሚወስዱት ምርጫ ላይ ጥገኛ እንደሚሆን በናይሮቢ ያሉት የዓለም አቀፉ የፀጥታ ጥናት ተቋም ተመራማሪ፣ ኤማኑዌል ኪሳንጋኒ አስረድተዋል።

Flüchtlingslager Südsudan
ምስል Reuters

« ሁሉን የሀገሪቱን ህብረተሰብ የሚያጠቃልለውን ገላጋይ ሀሳብ ላይ መድረስ እና ተሀድሶ ማነቃቃት የሚቻልበትን መንገድ ከመረጡ ደቡብ ሱዳን አሁን ከምትገኝበት ቀውስ ልትወጣ ትችላለች። ባካባቢውም ተሰሚነትዋ ከፍ ሊል ይችላል። በሀገሪቱ ላይ ለተደቀኑት ችግሮች መፍትሔ ካላፈላለጉ ግን ፍጥጫው ወደፊትም ሊቀጥል ይችላል። »

ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ የቀጠለው ውዝግብ እልባት የማያገኝበት ሁኔታ ምናልባት የደቡብ ሱዳንን መከፋፈል እንዳያስከትል አንዳንድ በአፍሪቃ የሚገኙ የፖለቲካ ተንታኞች ስጋታቸውን እየገለጹ ነው። ይሁንና፣ ይህንኑ አባባል በፕሪቶርያ የዓለም አቀፉ የፀጥታ ጥናት ተቋም ተንታኝ ዶክተር ፖል ሳይመን ይህን ሀሰብ ይጻረራሉ።

« ሀገሪቱ ትፈራርሳለች ብየ አላስብም። የዚችኑ ሀገር አመሠራረት መርሳት የለብንም። ገና ሁለት ዓመቷ ነው። አሁን የሚታየው ችግር በአዲስ ሀገር ውስጥ የሚጠበቅ ችግር ነው። እና ማወቅ ያለብን በጥቂት ወራት የሚያበቃ ቀውስ እንደሌለ ነው። እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፣ የአፍሪቃ ህብረት እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አጋሮች ሁሉ ቀውሱ ብዙ ጊዜ ሊቆይ እንደሚችል መገንዘብ ይኖርባቸዋል። »

Karte Horn of Africa

ሁኔታው አሁን እንዳለው ከቀጠለ የደቡብ ሱዳን ውዝግብ በሦስት አካባቢዎች፣ ማለትም፣ በምሥራቅ እና በማዕከላይ አፍሪቃ፣ እንዲሁም፣ በአፍሪቃው ቀንድ ፀጥታ ላይ ስጋት መደቀኑ እንዳልቀረ ዶክተር ሳይመን ሄንዲ አስታውቀዋል።

« የደቡብ ሱዳን ውዝግብ የደቀነው የፀጥታ ስጋት ጎረቤት ሀገሮችን እንዳሳሰባቸው በውዝግቡ ጣልቃ የገቡበት ድርጊት አመላካች ነው። ሱዳን፣ ዩጋንዳ፣ ኬንያ እና ኢትዮጵያ ውዝግቡ ተፅዕኖ እንዳሳረፈባቸው ይሰማቸዋል። እና የእነዚህ ሁሉ ሀገራት ጣልቃ ገብነት ውዝግቡ ላካባቢው የያዘውን የፀጥታ ትርጓሜ ያሳያል። »

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ