1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ሱዳን ነጻነትና ፋይዳው

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 3 2013

ፕሬዝዳንት ኪር ዳግም ወደ ጦርነት እንደማይገቡ ቢናገሩም ምክትላቸው ማቻርም የሰላምን አስፈላጊነት ቢያጎሉም ሁለቱም ያሉትን ተግባራዊ ማድረጋቸውን የሚጠራጠሩ አልጠፉም።በአሁኑ ጊዜ ጦርነትም ሰላምም በሌለበት ሁኔታ ላይ የምትገኘው የደቡብ ሱዳን እጣፈንታ ማነጋገሩ ቀጥሏል። የደቡብ ሱዳን መሪዎች የመሰረቱት የአንድነት መንግሥትም ደካማ በመባል ይተቻል።

https://p.dw.com/p/3wJJ1
Südsudan Salva Kiir (C) und Riek Machar (R)
ምስል AFP/P. Louis

የደቡብ ሱዳን ነጻነትና ፋይዳው

ደቡብ ሱዳን ነጻ የወጣችበት አስረኛ ዓመት ትናንት ተከብሯል። ነጻነትዋን ሳታጣጥም ድንገት የገባችበት የርስ በርስ ጦርነት ግን በእጅጉ አሽመድምዷታል፣አለመረጋጋቱም ስር ሰዷል በከፋ ረሃብም እየተሰቃየች ነው።ጦርነቱ በርካታ ህዝቧን ገድሏል ያቆሰለው ከቤት ንብረቱ የተፈናቀለው እጅግ ብዙ ህዝብ ነው።ትንሽቷ ሃገር ደቡብ ሱዳን እንደ ጎርጎሮሳዊው ሐምሌ ዘጠኝ 2011 ዓም እኩለ ለሊት ነበር ነጻነትዋን ያወጀችው። ይህ የሆነውም የ99 በመቶ ህዝቧን ድጋፍ ካገኘው ከሱዳን ተነጥሉ ነጻ መንግሥት ለመመስረት ከተካሄደ ህዝበ- ውሳኔ በኋላ ነበር። ከዚያ በፊት ደቡብ ሱዳናውያንና  በካርቱም መንግሥት መካከል በተካሄዱ የርስ በርስ ጦርነቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት አልፏል እንደ ፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገባ ።ከህዝበ-ውሳኔው አስቀድሞ በጎርጎሮሳውያኑ 2005 ዓም የሱዳን መንግሥትና የደቡብ ሱዳን አማጽያን የሰላም ውል ፈረሙ። በውሉ መሠረት ደቡብ ሱዳን በሸሪአ ሕግ መተዳደርዋ ቀርቶ ለ6 ዓመታት ራስዋን በራስዋ ስታስተዳድር ነበር።ጦርነቱም ቆሞ ሃገሪቱ ነጻ ስትወጣ ሰላም ርቆት የቆየው ህዝብ፣ ለሃገሩ ልማትና ብልጽግናን ሰንቆ የወደፊቷን ደቡብ ሱዳን በምናቡ እየሳለ እጅግ ቢፈነጥዝም ደስታው ግን አልዘለቀም።ለነጻነት በአንድ ላይ የታገሉት የሃገሪቱ የመጀመሪያ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርና ምክትላቸው ርየክ ማቻር በጎሳና ፖለቲካ ፀብ ተለያዩ።ደቡብ ሱዳን ነጻ በወጣች በሁለት ዓመቱ የርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ተዘፈቀች። ሃገር ግንባታው ተረስቶ ነጻ አውጭዎቿ ሃገሪቱን ሲቀራመቱ፣ከነጻነት በኋላ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውን የሰላምና የብልጽግና ተስፋ ጨለመ።አምባሳደር ተፈራ ሻውል የደቡብ ሱዳንን ጉዳይ በቅርብ ከሚያውቁት ዲፕሎማቶች አንዱ ናቸው።የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን ኢጋድ አቋቁሞት የነበረው የደቡብ ሱዳን አደራዳሪ ቡድን ዋና ፀሀፊም ነበሩ።ወደ ኃላ መለስ ብለው የደቡብ ሱዳንን የነጻነት ትግል ያስታወሱት አምባሳደር ተፈራ ደቡብ ሱዳን ነጻ ከወጣች በኋላ ወደ አስከፊ ጦርነት ብትገባም ከነጻነቱ ያተረፈችውም አለ ይላሉ።
ከኑዌር ጎሳ የወጡት ሪየክ ማቻር በጎሮሳዊው 2013 ዓም ከስልጣን ሲባረሩ ነበር ውጥረቱ የተባባሰው።የዲንካ ጎሳው ሳልቫ ኪር ማቻርን በከሸፈ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ከሰሱ። በዚያው ዓመት ሃገሪቱ የርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ገባች። ዘርን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ፣መጠነ ሰፊ አስገድዶ መድፈር ህጻናትን በወታደርነት ማሰለፍና ሌሎችም ጭካኔ የተሞላባቸው እርምጃዎች ተስፋፉ።ከዚያም በ2015 ዓም የሰላም ውል ተፈርሞ ማቻር በምክትል ፕሬዝዳንትነት ቢቀጥሉም ውጊያው እንደ አዲስ አገረሸና ማቻርም ኅይሎቻቸውም ሸሹ። አምባሳደር ተፈራ ሻውል እንደሚሉት ለደቡብ ሱዳን ነጻነትና በኋላም በሃገሪቱ ሰላም እንዲወርድ ኢትዮጵያ ብዙ ጥረት አድርጋለች።ይሁንና የሌሎች ሃገራት ፍላጎቶች የሰላም ጥረቱ እንዳይሰምር እንቅፋት መሆናቸው አልቀረም። ተግዳሮቶቹም እነዚህ ብቻ አይደሉም።
ሁለቱ ባላንጣዎች ኪርና ማቻር ከሦስት ዓመት በኋላ በሰኔ 2018 ፣ነበር  የብሔራዊ አንድነት መንግሥት የመመስረት ዓላማ ያለው አዲስ የሰላም ስምምነት ላይ የደረሱት። በመስከረም 2018 መንግሥት ለመመስረት ቢስማሙም ምሥረታው ሁለት ጊዜ ተራዝሞ ባለፈው ዓመት አጋማሽ ነው የተሳካው። ዋና ከተማይቱ ጁባ ውስጥ ትናንት በደቡብ ሱዳን ነጻነት አስረኛ ዓመት መታሰቢያ ክብረ በዓል ላይ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሪየክ ማቻር  ባሰሙት ንግግር ብዙዎች ተግባራዊ ሆኖ ማየት የሚፈልጉትን ቃል ገብተዋል።
«በበኩሌ እንደገና ወደ ጦርነት እንደማልመለሳችሁ አረጋግጥላችኃለሁ።ካጣናቸው አሥርት ዓመታት መልሰን ለማገገምና ሃገራችንን በወደፊቱ አሥር ዓመት ወደ ልማት ጎዳና  ለመውሰድ በአንድነት እንስራ።»
ምክትል ፕሬዝዳንት ሪየክ ማቻርም በስነ ስርዓት ላይ ሰላም የሁሉም መሠረት ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
«እኛ በዓላትን ማክበር እንድንቀጥል ሰላምን ህያው ማድረግ አለብን። ምክንያቱም የስፖርት እንቅስቃሴዎችንም ይሁን የኤኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችንም ጭምር ማካሄድ የሚቻለው ሰላም ሲኖር ብቻ ነው። በሰላም አማካይነት ነው ልናደርገው የምንችለው።
ፕሬዝዳንት ኪር ዳግም ወደ ጦርነት እንደማይገቡ ቢናገሩም ምክትላቸው ማቻርም የሰላምን አስፈላጊነት ቢያጎሉም ሁለቱም ያሉትን ተግባራዊ ማድረጋቸውን  የሚጠራጠሩ አልጠፉም።ብሪታንያ ኖርዌይና ዩናይትድ ስቴትስ በጋራ ባወጡት መገለጫ የተሻለ መጻኤ እድል  ለመገንባት ብዙዎች አብረው ለመስራት ያሳዩትን ቁርጠንነት አድንቀው ሆኖም ቃል  የተገባላቸው ሰላምና ብልጽግና አሁንም አለመሟላታቸው በእጅጉ አሳዛኝ መሆኑን ሳይጠቅሱ አላለፉም።በአሁኑ ጊዜ ጦርነትም ሰላምም በሌለበት ሁኔታ ላይ የምትገኘው የደቡብ ሱዳን እጣፈንታ ማነጋገሩ ቀጥሏል። አምባሳደር ተፈራ ሻውል
ሃገሪቱን ነጻ ያወጡት የቀድሞዎቹ አማጽያን፤በኃላም ሁለት ጊዜ የርስ በርስ ጦርነት ያካሄዱት የአሁኖቹ የደቡብ ሱዳን መሪዎች አሁንም ሥልጣን ላይ ናቸው።በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከፍተኛ ጫና ፣ባለፈው ዓመት በየካቲት ወር ከታቀደበት ጊዜ ዘግይተው የመሰረቱት የአንድነት መንግሥትም ደካማ በመባል ይተቻል።ሃገሪቱ ሌላ ጦርነት ውስጥ እንዳትገባ ለማድረግ ወሳኝ የሚባሉ እርምጃዎች አለመሟላታቸውም ነው የሚነገረው።ታዲያ እነዚህ መሰረታዊ የተባሉ ጉዳዮች ተጓድለው የሃገሪቱ የወደፊት ተስፋ ምን ሊሆን ይችላል።
የኃለኛው የደቡብ ሱዳን ጦርነት ከ380 ሺህ በላይ ሰዎችን ሕይወት አጥፍቷል።ከፊሉ በህመምና የጤና አገልግሎት ባለማግኘት ነው የሞተው። ቁጥራቸው አራት ሚሊዮን የሚጠጋ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።የተመድ፣ የመንግስት ኃይሎችንና ሌሎች ታጣቂዎችን ሆነ ብለው ለሰላማዊ ሰዎች እርዳታ እንዳይደርስ በመከልከልና ሰዎችን በማፈናቀል ሲከስ ቆይቷል።የፖለቲካው ዝግመት ፣ቃል በተግባር አለመተርጎሙ ፣የኤኮኖሚው ቀውስ እንዲሁም ሃገሪቱ ከነጻነት ወዲህ የከፋ ለሚባል ረሃብ መጋለጧ የድሃይቱን ሃገር ጫና አክብዷል።ምንም እንኳን በደቡብ ሱዳን የደረሰውን የሰላም እጦት ሊያስቀሩ የሚችሉ ብዙ እድሎች ባክነዋል ቢባልም የሰላሙን ሂደት እንደገና ለማንቀሳቀስ አሁን ጊዜው አልረፈደም የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም። 

Südsudan Verhandlungen zwischen Regierung und Opposition
ምስል Reuters/J. Solomun
Uganda Flüchtlingslager Palorinya Südsudan
ምስል DW/L. Emmanuel
Südsudan Juba Unterzeichnung Friedensvertrag mit Rebellen
ምስል Reuters/S. Bol


ሒሩት መለሰ

ታምራት ዲንሳ