1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ሱዳን ውዝግብ እና ድርድሩ

ቅዳሜ፣ ጥር 3 2006

በደቡብ ሱዳን ካለፈው ታህሣሥስድስት ወዲህ የቀጠለውን እና ከአንድ ሺ በላይ ህዝብ ያጠፋውን፤ ከ 200,000 በላይ ህዝብ ውጊያ ለማስቆም በተፋላሚ ዎቹ ወገኖች ተወካዮችመካከል በኢጋድ ሸምጋይነት በአዲስ አበባ

https://p.dw.com/p/1Ap9p
Äthiopien Südsudan Gespräche in Addis Abeba Verhandlungsdelegation
ምስል Reuters

የተጀመረው የፊት ለፊት የሰላም ድርድር የፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር ተቃዋሚዎች ባቀረቡት በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ወንጀለዉ የያሰሩዋቸው ባለሥልጣናት የይፈቱ ጥያቄ ችግር እንዳጋጠመው ይገኛል። ምንም እንኳን ከፕሬዝዳት ሳልቫ ኪርንና ኪር ያሰሯቸዉን ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ተነጋግረው የተመለሱት አደራዳሪዎች አበረታቺ ሂደት ማየታቸውን ቢገልጹም አሁንም ድርድሩ ችግር ገጥሞታል። ይህ በዚህ እንዳለ፣ የደቡብ ሱዳን ጦር ተቃዋሚው ይዟት የነበረችውን ግዙፍ የየነዳጅ ዘይት ንጣፍ የሚገኝባትን በዩኒቲ ግዛት የምተገኘዋን ዋነኛ ከተማ ቤኒቱን መልሶ መያዙን አስታውቋል። የደቡብ ሱዳን ጦር ጥቃቱን አጠናክሮ የጆንግሌይን ዋና ከተማ ቦርንም መልሶ እንደሚይዝም አክሎ አስታውቋል።

Konflikt im Südsudan Armeechef James Hoth Mai 02.01.2014
ምስል Reuters

የኢጋድ አደራዳሪዎች ሽምግልና በቀጠሉበታ በዚሁ ወቅት የሱዳን ፕሬዚደንት ኦማር ሀሰን ኤል በሺር ስለቀውሱ ከደቡብ ሱዳን አቻቸው ሳልቫ ኪር ጋ ለመምከር ባለፈው ሰኞ ወደ ጎረቤት ሀገር መዲና ጁባ ተጉዘው ነበር። ሁለቱ መሪዎች ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን በደቡብ ሱዳን ያሉትን ግዙፍ የነዳጅ ዘይት ንጣፍ ከዓማፅያን ጥቃት የሚከላከል አንድ የጋራ ኃይል ማሠማራት ስለሚቻልበት ጉዳይ በጥሞና ለማሰላሰል ተስማምተው መለያየታቸው ታውቋል። የሱዳን ፕሬዚደንት የደቡብ ሱዳንን ቀውስ ለማብቃት በሚደረገው ጥረት ላይ ገንቢ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ በበርሊን የጀርመናውያኑ የፖለቲካ ጥናት ተቋም ተንታኝ ይገመታሉ።

« ፕሬዚደንት በሺር ደቡብ ሱዳን እንድትረጋጋ ነው የሚፈልጉት። ባሁኑ ጊዜ ለርሳቸው ትልቅ ትርጉም የያዘው የነዳጅ ዘይቱ ሀብት እና እስከዛሬ ድረስ ተግባራዊ ያልሆኑት የአጠቃላዩ የሰላም ስምምነት ነጥቦች ናቸው። ድንበሩ ገና አልተሰመረም። የአቢየ ጉዳይ አለ፣ በሰሜን ሱዳንም በደቡብ ኮርዶፋን እና በብሉ ናይል ግዛቶች በሺር በደቡብ ሱዳን ይርዳሉ የሚሉዋቸው ዓማፅያን የቀጠሉት ግጭትም አለ። እና በሺር የተረጋጋች ደቡብ ሱዳን እንድትኖር ይፈልጋሉ። »

Südsudan Sudan Omar al-Bashir bei Salva Kiir in Juba
ምስል Reuters

በሺር እልባታ ላለገኘው የድንበር ጥያቄ መፍትሔ ይገኝለት እና በተለይ የደቡብ ሱዳን የነዳጅ ዘይት ዘርፍ እንደገና ሙሉ ለሙሉ ስራውን ይጀምር ዘንድ ሸሪክ ያስፈልጋቸዋል። ደቡብ ሱዳን የምታመርተው ነዳጅ ዘይት በሱዳን በተዘረጉት ቧምቧዎች የሚተላለፍበት ድርጊት ለሱዳን መንግሥት ዋነኛ የገቢ ምንጭ ነው።

ሁለቱ ጎረቤት ሀገራት የብዙ ዓመታት ደም አፋሳሽ ታሪክ ቢኖራቸውም፣ በሺር ከሁለቱም ተቀናቃኞቹ የደቡብ ሱዳን ቡድኖች ጋ ማለፊያ ግንኙነት አላቸው። የቀድሞው ምክትል ፕሬዚደንት ሪክ ማቸር እና በሺር በ «ኤስ ፒ ኤል ኤም» ውስጥ ልዩነት ተፈጥሮ ማቸር አአአ በ1990ኛዎቹ ዓመታት ከቡድኑ በመገንጠል በሳልቫ ኪር አንፃር ደም አፋሳሽ ውጊያ ባካሄዱበት ጊዜ የጠበቀ ግንኙነት መሥርተው ነበር። ከሳልቫ ኪርም ጋ ቢሆን በሺር ጥሩ ግንኙነት አላቸው።

ከሱዳን እና ከብዙዎቹ የደቡብ ሱዳን ጎረቤት ሀገራት አንፃር በፕሬዚደንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ የሚመሩት የዩጋንዳ መንግሥት በደቡብ ሱዳን ውዝግብ ውስጥ በግልጽ ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪርን ይደግፋል። የዩጋንዳ ጦር እአአa ከ1986 ወዲህ «ኤስ ፒ ኤል ኤም» ይረዳሉ፣ ከደቡብ ሱዳን ነፃነትም ወዲህ የሁለቱ ሀገራት ጦር በቅርብ ፣ በተለይ የሎርድ ሬዚዝተንስ አርሚን በመዋጋቱ ረገድ ተባብረው ይሰራሉ። ዩጋንዳም ለደቡብ ሱዳን ጦር ከባድ የጦር መሣሪያ ርዳታ ይሰጣል። የዩጋንዳ ፀጥታ ጥበቃ ኃይላትም ጁባ የሚገኘውን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ይጠብቃሉ።።

Südsudans Präsident Kiir und Ugandas Präsident Museveni
ምስል Tony Karumba/AFP/Getty Images

የደቡብ ሱዳን መንግሥት ያሰራቸውን ባለሥልጣናት እስካልፈታ ድረስ ከሦስት ሳምንት በላይ ያስቆጠረውን ጦርነት ማስቆም የሚያስችል ተኩስ አቁም እንደማይደረስ በአዲስ አበባ ከደቡብ ሱዳን ተወካዮች ጋ የፊት ለፊት ድርድር የሚያካሂዱት የቀድሞዉምክትልፕሬዚደንትየሪክማቸርደጋፊዎችተወካዮች አስጠንቅቀዋል። ድርድሩ በደቡብ ሱዳን ለቀጠለው ውዝግብ ዘላቂ መፍትሔ ያስገኝ ዘንድ ጆንስ በቅድሚያ ሊወገዱ የሚገቡ አንዳንድ እንቅፋቶች መኖራቸውን በብሪታንያ ኦክስፈርድ የሚገኙት የሱዳን ጉዳይ አጥኚ ዳግላስ አስረድተዋል።

« በኤስ ፒ ኤል ኤም፣ ማለትም በሱዳን ሕዝብ ነፃ አውጪ ንቅናቄ ውስጥ ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር በሚከተሉት ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ አንፃር ያለው ተቃውሞ ለምሳሌ ትልቅ እንቅፋት ደቅኖዋል። እነዚህ ተቃዋሚዎች ግን ሪክ ማቸር የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ለመሆን ያላቸውን ፍላጎት ይደግፋሉ ማለት ግን አይደለም። ሪክ ማቸር አንድ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ አንድ ብሔራዊ ኃይል ማቋቋም አለባቸው። እስካሁን ለጦርነቱ ያሰባሰቡዋቸው ተዋጊዎች ከተለያዪ የኑዌር ጎሣ ቡድኖች የተውጣጡ ናቸው። በመንግሥቱ ጦር አንፃር የሚዋጋ ኃይል ስለሌላቸው አሁን ውጊያው ይበልጡን ወደ ጎሣ ግጭት እየተቀረ ሄዶዋል። »

ይህ ሂደት ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት ነፃነቱን በተጎናፀፈው ሕዝብ መካከል የጎሣ ፍጅት እንዳያስከትል ሥጋት በመደቀኑ ቀውሱ ባስቸኳይ ሊወገድ እና፣ ለምሳሌ፣ የጋራ መንግሥት ምሥረታ ምናልባት መፍትሔ ሊሆን እንደሚችል አንዳንዶች ሲጠቁሙ ተሰምቶዋል። እርግጥ፣ የአዲስ አበባው ድርድር በተለይ የፕሬዚደንት ሳልቫ ኪርን መንግሥት እና የተቀናቃኛቸውን ሪክ ማቸርን ደጋፊዎች ሊያቀራርብ ይችል ይሆናል የሚሉት ዳግላስ ጆንስ የተቀናቃኞቹ የዲንካ የኑዌር ጎሣዎች ተወካዮችን በሀገር አመራሩ ተግባር ላይ ማሳተፉ ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ።

« ሥልጣን መጋራት ዘላቂ መፍትሔ ማለት አይደለም፣ እንደ ጊዚያዊ መፍትሔም ቢሆን መረጋጋትን አያስገኝም። የሽግግር መንግሥት ይመሥረት ከተባለም ደቡብ ሱዳን አሁን ካላት የተለየ እና ሁሉን የሚወክል መንግሥት ማዋቀር ይቻል ዘንድ አንድ፣ ከተቀናቃኝ ወገኖች የሥልጣን ሽኩቻ ጋ ያልተያያዘ እና የሲቭሉን ሕዝብ ተወካዮች ያካተተ አዲስ ሕገ መንግሥታዊ ጉባዔ መቋቋም ይኖርበታል። »

Südsudan Kämpfe Flüchtlinge in Bor
ምስል Reuters

ጦርነቱ እንዳይባባስ ማድረጉ ቀላል ይሆናል ተብሎ እንደማይገመትም የገለጹት ዳግላስ ጆን በዚሁ ረገድ የአፍሪቃ ህብረት የሚያደርገው ጥረት እና የሚወስደው ሰላም ጠባቂ ጓድ ማሠማራትን የመሰለ ርምጃ ወሳኝ እንደሚሆን ይገምታሉ። ይሁንና፣ በውዝግቡ ላይ የደቡብ ሱዳን አቻቸውን ሳልቫ ኪርን በግልጽ የሚደግፉት የዩጋንዳ ፕሬዚደንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ጦራቸውን በደቡብ ሱዳን በማሠማራት ጣልቃ የገቡበት ድርጊት ይህን የህብረቱን ርምጃ አዳጋች ሊያደርገው እንደሚችል ገልጸዋል።

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ