1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ሱዳን ግጭትና የታቀደው ምርጫ

Melesse Hirutዓርብ፣ ታኅሣሥ 24 2007

የርስ በርስ ግጭት በየጊዜው በሚያገረሽባት በደቡብ ሱዳን ከጥቂት ወራት በኋላ አጠቃላይ ምርጫ እንደሚካሄድ የደቡብ ሱዳን መንግሥት ትናንት አስታውቋል። መንግስት በዚሁ ምርጫ ብዙዎች እንዲሳተፉ ለአማፅያን ምህረት እንደሚያደርግም ተናግሯል።

https://p.dw.com/p/1EEIE
ምስል Ashraf Shalzy/AFP/Getty Images

ይሁንና ግጭቱ ሳይቆም በደቡብ ሱዳን ሊካሄድ ታቅዷል የተባለው ምርጫ ተግባራዊነት እያነጋገረ ነው። በኢትዮጵያ የሰላምና የልማት ዓለም ዓቀፍ ተቋም የምሥራቅ አፍሪቃ ጉዳዮች የፖለቲካ ተንታኝ አቶ አቤል አባተ ለዶቼቬለ በሰጡት አስተያየት እቅዱ ጋሪውን ከፈረሱ ያስቀደመ ይመስላል ብለዋል። የሱዳን መንግሥት ቃል አቀባይን ጠቅሶ አሶስየትድ ፕሬስ እንደዘገበው በሱዳን አጠቃላይ ምርጫ ለማካሄድ የታቀደው በመጪው ግንቦትና ሐምሌ መካከል ነው። ለምርጫውም ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል። የደቡብ ሱዳን መንግሥት ፕሬዝዳንት የፕሬስ ፀሃፊ አቴኒ ዌክ አቴኒ እንዳሉት በጀት ተመድቧል፤ ብዙዎችን በምርጫው ለማሳተፍ ና ለማበረታታትም ለአማፅያን ምሕረት ለማድረግ ታስቧል።

Symbolbild - Soldaten Südsudan
ምስል Getty Images

ይሁንና መንግሥትና አማፅያን ከአንድ ዓመት በላይ ከወሰደ የሰላም ድርድር በኋላ አንድም መፍትሄ ላይ ሳይደርሱ ምርጫ ይካሄዳል መባሉ አነጋጋሪ ሆኗል። በኢትዮጵያ የሰላምና የልማት ዓለም ዓቀፍ ጥናት ተቋም የምሥራቅ አፍሪቃ ጉዳዮች የፖለቲካ ተንታኝ አቶ አቤል አባተ በአዲስ አበባው የሰላም ድርድር የተጀመሩ ጥረቶች ፍጻሜ ሳያገኙ ና የተኩስ አቁሙም ሳይፀና ምርጫ ለማካሄድ ማሰብ አስቸጋሪ እንደሚሆን ነው የሚናገሩት።የደቡብ ሱዳን መንግሥት ምርጫው ግልፅና የህዝቡንም ፍላጎት የሚያንፀባርቅ እንደሚሆን ነው የሚናገረው። መንግሥትን የሚወጉት አማፅያን ግን የተቃደውን ምርጫ እንደማይቀበሉና ነፃና ፍትሃዊ ይሆናል ብለው እንደማያምኑም አስታውቀዋል። ምንም እንኳን መንግሥት ለአማፅያን ምህረት አደርጋለሁ ቢልም አማጽያኑ በምርጫው እንደማይሳተፉም ነው የተናገሩት።

Flüchtlingslager Tomping in Juba Südsudan
ምስል DW/Scholz/Kriesch

መንግስት እንዳለው በምርጫ እቅድ የሚገፋ ከሆነ የረባ ውጤት ያመጣል ብሎ መገመት ያዳግታል ይላሉ አቶ አቤል፤አቶ አቤል እንደሚሉት ከምርጫው በፊት ፍጻሜ ሊያገኙ የሚገባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል። በርሳቸው አስተያየት በተለይ የእርስ በእርስ ግጭቱን ለማስቆም የተጀመሩት ጥረቶች ከዳር መድረስ ይኖርባቸዋል። ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረው የደቡብ ሱዳን የርስ በርስ ግጭት ከ10 ሺህዎች በላይ የሚገመቱ ሰዎችን ሕይወት አጥፍቷል፤ ከ 1.9 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑትን ደግሞ አፈናቅሏል ።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ