1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ሱዳን ጦርነትና ዲፕሎማሲ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 22 2006

ማቸር ለመደራደር ፍቃደኛ ከመሆናቸዉ ጋር ተኩስ እንደማያቆሙ እንዳስታወቁ ሁሉ ፕሬዝዳት ሳልቫ ኪርም ዉጪ ጉዳይ ሚንስትራቸዉን ለድርድር ወደ አዲስ አበባ ከመላካቸዉ እኩል ሥልጣን እንዲለቁ ወይም አዲስ ምርጫ እንዲደረግ ተቃዋሚዎች ያቀረቡትን ሐሳብ ዉድቅ አድርገዉታል

https://p.dw.com/p/1Ajph
ምስል Reuters

የደቡብ ሱዳን የርስ በርስ ጦርነት፥የተጨማሪ ጦርነት ዛቻ፥ ጦርነት ዛቻዉን ለማስቆም የሚደረገዉም ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ዛሬም እንደቀጠለ ነዉ።የቀድሞዉ ምክትል ፕሬዝዳት የዶክተር ሪክ ማቸር ደጋፊዎች በቅርቡ በመንግሥት ጦር የተቀሟትን ከተማ ቦርን ዛሬ መልሰዉ መቆጣጠራቸዉን አስታዉቀዋል።የአማፂያኑ ቃል አቀባይ ሞሰስ ሩአይ ዛሬ እንዳስታወቁት ቦር ሠፍሮ የነበረዉ የመንግሥት ጦር ከአማፂያኑ የተሰነዘረበትን መጠነ-ሰፊ ጥቃት መቋቋም አቅቶት ሸሽቷል።የመንግሥት ጦር ቃል አቀባይ ኮሎኔል ፊሊፕ አጉዋር ግን ቦርን ለመያዝ እና ላለመስያዝ የሚደረገዉ ዉጊያ እስከ ቀትር ድረስ እንደቀጠለ ነዉ ባይ ናቸዉ።ቦር ከዕሠ-ከተማ ጁባ ሁለት መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።አዲሲቱ ሐገር ለተጨማሪ ዉጊያ አዳዲስ ፉከራና ዛቻ እየተሰማባትም ነዉ። ማቸር ዛሬ እንዳስታወቁት ደጋፊዎቻቸዉ ርዕሠ-ከተማ ጁባን ለማጥቃት ወደ ከተማይቱ እየገሰገሱ ነዉ።በዚሕም ምክንያት ማቸር እንዳሉት፥ ተኩስ እንዲያቆሙ የቀረበላቸዉን ጥያቄ አይቀበሉትም።ሰወስተኛ ሳምንቱን በያዘዉ ዉጊያ በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፤ ወደ ሁለት መቶ ሺሕ ተሰደዋል

በተያያዘ ዜና የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) አባል ሐገራት ባቀረቡት የድርድር ጥያቄ መሠረት ሁለቱም ወገኖች ተደራዳሪዎችን ወደ አዲስ አበባ መላካቸዉን አስታዉቀዋል።ማቸር ለመደራደር ፍቃደኛ ከመሆናቸዉ ጋር ተኩስ እንደማያቆሙ እንዳስታወቁ ሁሉ ፕሬዝዳት ሳልቫ ኪርም ዉጪ ጉዳይ ሚንስትራቸዉን ለድርድር ወደ አዲስ አበባ ከመላካቸዉ እኩል ሥልጣን እንዲለቁ ወይም አዲስ ምርጫ እንዲደረግ ተቃዋሚዎች ያቀረቡትን ሐሳብ ዉድቅ አድርገዉታል።በዉጊያ፥ዛቻዉ፥ በእንቢተኝነቱ መሐል ይደረጋል የተባለዉ ድርድር ይዘትና ዉጤት ታዛቢን ግራ እንዳጋባ ነዉ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሠላም አስከባሪ ጉዳይ ረዳት ዋና ፀሐፊ ሔርቨ ላድሱስ በፋንታቸዉ ድርጅታቸዉ ወደ ደቡብ ሱዳን ሠላም አስከባሪ ለማዝመት እየተዘጋጀ መሆኑን አስታዉቀዋል።የደቡብ ሱዳን መንግሥት ከድርጅቱ ጋር እንዲተባበርም ጠይቀዋል።

«ባለፈዉ ሳምንት በፀደቀዉ ዉሳኔ ቁጥር 2132 መሠረት፥ ለዘመቻዉ የሠራዊት፥ የትጥቅና የቁሳቁስ መዋጮን ለማስተባበር ሌት-ከቀን እየሠራን ነዉ።ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ሙሉ ትብብርን እንደምንጠብቅ በአፅንኦት መናገር አፈልጋለሁ።ከምክር ቤቱ ፊት እንደተናገርኩት፥ ቤት እየተቃጠለ የእሳት ተከላካይ ባለሙያዎችን ዜግነትና ማንነት ሊያስጨንቀን አይገባም።የሚያስፈልገዉ ሠራተኞቹ ቃጠሎዉን እንዲያጠፉ ማድረግ ብቻ ነዉ።»

የላድሰን ዲፕሎማሲያዊ ወቀሳ የተሰነዘረዉ የደቡብ ሱዳን መንግሥት ሠራዊት የሚያዘምቱ ሐገራትን ማንነትን በመጠየቁ ነዉ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት፥ ተፋላሚ ሐይላትን ለመሸምገል ኢጋድ የጀመረዉን ጥረት እንደሚደግፍ አስታዉቋል።ተፋላሚዎች ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ እንዲደራደሩ አሳስቧልም።

Südsudan Kämpfe 30.12.2013
ምስል Reuters

ነጋሽ መሀመድ

ተክሌ የኋላ