1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ሱዳን ፖለቲካዊ ይዞታ

ረቡዕ፣ የካቲት 5 2006

ለደቡብ ሱዳን ነፃነት በጋራ የታገሉት የሐገሪቱ ፖለቲከኞች ካለፈዉ ታሕሳስ ጀምሮ የለየለት ዉጊያ ገጥመዋል።ጦርነቱን ለማስቆም የሚደረገዉ ሁለተኛ ዙር ድርድር ከታቀደለት ቀን ተሸጋሽጎ ቢጀመርም ተፋላሚ ወገኖች መካሰሳቸዉ መቀጠሉ ነዉ የተሰማዉ።

https://p.dw.com/p/1B7Za
ምስል Charles Lomodong/AFP/Getty Images

በፕሬዝደንት ሳል ቫኪር ታማኞችና በቀድሞ ምክትላቸዉ ሪክ ማቻር ደጋፊዎች መካከል ሲካሔድ የነበረዉ ድርድርም አሁን ሶስተኛ ተደራዳሪ ሊታከልበት እንደሆነ ነዉ ከአደራዳሪዉ ወገን ተሰምቷል።

አዲሷ ነፃ ሀገር የነፃነት ዘመኗን እንኳ በወጉ ሳታጣጥም ከዉጭ የገጠማት ሳንክ ሳያንስ በዉስጥ የፖለቲካ ጉዳይ መታመስ መጀመሯ የወደፊት ርምጃዋን መስቀለኛ መንገድ ላይ አሳርፎታል። ባለፈዉ ታህሳስ ወር ለፕሬዝደንቱ ታማኞች እና በምክትላቸዉ ተከታዮች መካከል የተለኮሰዉ ግጭት በሺ የሚቆጠሩትን ህይወት አሳጥቶ፤ በብዙ ሺዎች የሚገመቱት ከቤት ንብረት በማፈናቀል ብቻ አልተገታም። በመፈንቅለ መንግስት የተጠረጠሩትም ዘብጥያ አዉርዷል። ታስረዉ ከነበረዉ ከ11ዱ ተጠርጣሪዎች ሰባቱ ተለቀዉ ኬንያ ገብተዋል። ውዝግቡ ሲጀመር የደቡብ ሱዳን የአማፅያን መሪ የሪክ ማቻር ተባባሪዎች ታሳሪዎቹ ካልተለቀቁ ለድርድር አንቀርብም ሲሉም ቆይተዋል። አሁን ኬንያ የሚገኙት ከእስር የወጡት ወገኖች ግን አሁን ከማቻር ጎን ሳይሆን ለብቻቸዉ እንደሶስተኛ ወገን ሆነዉ በድርድር ለመሳተፍ እንደሚሹ ነዉ የተሰማዉ። ይህ በግጭትና በፖለቲካ ቀዉስ ዉስጥ ለገባቸዉ አዲስ ሀገር ሰላምና መረጋጋት ምን ማለት ይሆን? በደቡብ አፍሪቃ ጆሃንስበርግ የሚገኘዉ የዓለም ዓቀፉ የፀጥታ ጥናት ተቋም ባልደረባ አንድሩ አታ አሳሞሃ፤ በተቀናቃኞቹ ወገኖች መካከል የሚካሄደዉ ድርድር ራሱ ቀላል እንደማይሆን ነዉ የሚጠቁሙት፤
«በመጀመሪያ እዉነቱን ለመናገር የጉዳዩ ተዋናዮች በዚህ ደረጃ ያለዉ ድርድር ቀላል መስሎ ታይቷቸዋል። እኔ ግን በተለያየ አቅጣጫ ያለዉ የኃይል እንቅስቃሴ እንዲገታ ከዓለም ዓቀፍ ተዋናዮች የሚደረገዉ ጫና በመኖሩ በመጠኑም ቢሆን አዳጋች ይሆናል ብዬ አስባለሁ። ተጨማሪ መከፋፈሎችንም ይኖራሉ። ምክንያቱም በዚህ ደረጃ ላይ ድርድር እንዲካሄድባቸዉ የተለያዩ ፍላጎቶችና አጀንዳ ወደጠረጴዛዉ የሚቀርቡት።»
እሳቸዉ እንደሚሉትም በተለይ አማፅያኑ የሚያቀርቧቸዉን ሃሳቦች በቅርበት መመርመት የሚገባዉም በዚህ ደረጃ ላይ ነዉ። በዚህ ሁኔታም ሪክ ማቻር የሁሉንም ጥያቄዎች አንሰተዉ ይናገሩ እንደሆነዉ መረዳት የሚቻለዉ። በፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር መንግስት ለመገልበጥ በማሴር ከታሰሩበት የተለቀቁት እና አሁን ኬንያ የሚገኙት ሰባቱ ደቡብ ሱዳናዊያን ከማቻር ጎን አለመቆማቸዉም የዉስጣዊ ክፍፍላቸዉ ነፀብራቅ ነዉ እንደአሳሞሃ፤
«እንደሚመስለኝ ይህ ደቡብ ሱዳን አሁን ወደምትገኝበት ደረጃ ወዳደረሳት የዉስጥ መከፋፈል ይመራናል። በመሠረቱ አብዛኞቹ ራሳቸዉን ከሪክ ማቻር ጎን ያሰባሰቡ ወይም ያሰለፉ ወገኖች የግድ ሪክ ማቻርን የሚደግፉ ሰዎች ናቸዉ ማለት አይቻልም። አንድ የሚያደርጋቸዉ እንደሚመስለኝ ሁሉም የፕሬዝደንቱ ተቃዋሚዎች መሆናቸዉ ነዉ። እናም ፕሬዝደንቱ ፖሊሲያቸዉን እና በአንድ ሰዉ የመመራት አካሄዳቸዉን ስለተቃወሙ ብቻ ሁሉንም በአንድ ላይ በማጎር ስህተት የሠሩ ይመስለኛል። እንደሚመስለኛ የተሳሳተ መስመር አለ። እነዚህ ሰባት ሰዎች ተለቀዉ ከኬንያ የሰጡትን መግለጫ ካየሽ ፕሬዝደንቱ ወዳጃቸዉ እንደሆኑ እና ከእሳቸዉ የሚፃረር ነገር እንደሌላቸዉ ነዉ የገለፁት። ይህም ወዲያዉ ልዩነቱን አሳየ። እናም እኔ ሶስተኛ ወገን በመፈጠሩ አልገረምም፤ ያም ማለት ሪክ ማቻር የግድ የሁሉም ድጋፍ አላቸዉ ማለት አይደለም። ሃቁ የፕሬዝደንቱን አስተዳደር በመቃወም የሚጋሩት ነገር አለ። እናም እዚህ ጋ ነዉ መስመሩን ማድረግ የሚኖርብን።»
እንደሚታወቀዉ የደቡብ ሱዳን የዛሬ መሪዎችና አማፂያን፤ በአንድ ወቅት የትግል ጓዶች የነበሩና ለነፃነቱም ከፍተኛ መስዋዕትነት በጋራ የከፈሉ ወገኖች ናቸዉ። የሀገሪቱ ልማት እንደታሰበዉ ሳይንቀሳቀስ፤ ከሰሜን ሱዳምን ጋ የሚያነታርካቸዉ የነዳጅ ዘይት ሀብት አጠቃቀም ጉዳይ ፈር ሳይዝ፤ በዉስጥ በፖለቲካ በመታመሰል ለመከፋፈል ብሎም ነፍጥ አንስቶ ለመታኮስ መብቃታቸዉ እየታየ ነዉ። በተለያዩ አንጃዎች የተከፋፈለዉ የሀገሪቱ ለወደፊት ይዞታን አስመልክቶ አንድሩ አታ አሳሞሃ፤ የደቡብ ሱዳን ነፃ አዉጪ ጦርም፤ ሆነ የሱዳን ህዝቦች የነፃነት ንቅናቄን ታሪክ ለተመለከተ ከዚህ የተለየ እንዳልሆነ ነዉ የሚያረዱት፤
«ወደፊት የመራመዱ ነገር ሲታሰብ እንደሀገር የሚገጥማቸዉን አስቸጋሪ ሁኔታ ያመላክታል። ታሪካቸዉን ብንመለከት በተለይም የSPLA፤ የSPLMን እና እንደገና የSPLAን ታሪክ ስናይ ይህ ፍፁም አዲስ ነገር አይደለም። ምክንያቱም SPLA ብቻዉን የወጣ ቡድን አልነበረም በዉስጡ የተለያዩ ቡድኖችና የተለያዩ ተዋጊ ኃይላት ያሏቸዉ ግለሰቦች ናቸዉ የተለያየ ሃሳብ ይዘዉ በSPLA ጥላ ሥር የተሰባሰቡት። እናም ላለፉት ዓመታት የየራሳቸዉን አጀንዳ ይዘዉ በአንድ መሪ ሥር ለአንድ ዓላማ የተለያዩ ቡድኖች ሲታገሉ አይተናል። አሁን ደቡብ ሱዳን የሚኖራት ፈተና በዓመታት ሂደት በጋራ ለአንድነት የመሥራት እድሉ ይኖራታል ወይ የሚለዉ ነዉ።»
እሳቸዉ እንደሚሉት ከሆነም ለሀገሪቱና ለህዝቧ የሚበጀዉ ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር መንግስቴን ሊገለብጡ ነበር በሚል የከሰሷቸዉ የትግል አጋሮቻቸዉን ይቅር ቢሉ ነዉ።

Südsudan Rebellen 10.02.2014
ምስል Reuters
Unterzeichnung Waffenstillstandabkommen für Südsudan in Addis Abeba Äthiopien 23.01.2014
ምስል picture-alliance/dpa

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ