1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት የ«አይ ሲ ሲ» አባልነት ጥያቄ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 20 2007

የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት በቅርቡ በሀገሩ በተካሄደው የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ የተካፈሉትን እና በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ተመልካች ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ የተላለፈባቸውን የሱዳን ፕሬዝደንት ኦማር ሀሰን አል በሽርን ባለማሰሩ የሚሰነዘርበት ወቀሳ አሁንም እንደቀጠለ ነው።

https://p.dw.com/p/1Fo6Y
Sudafrika Pretoria Union Buildings, Sitz der Regierung
በፕሪቶርያ የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት መንበርምስል imago/blickwinkel

[No title]

ወቀሳው እና ንትርኩ በቀጠለበት ባሁኑ ጊዜ የሀገሪቱ መንግሥት የዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ተመልካች ፍርድ ቤት፣ በምህፃሩ የ «አይሲሲ»ን አባልነቱን ይዞ መቆየት አለመቆየቱን በጥሞና እንደሚያጤነው አስታወቀ።የኃያላኑ መንግሥታት እና የመብት ተሟጋቾች የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት አንድ የሀገሩ ፍርድ ቤት በሺር እንዲታሰሩ ያሳለፈውን ትዕዛዝ ችላ በማለት ወደ ሀገራቸዉ በተመለሱበት ድርጊት የተነሳ ባለፈው እአአ ሀምሌ 15፣ 2015 ዓም የተጀመረው ዲፕሎማቲክ ንትርክ በአፍሪቃ እና በበለፀጉት ሀገራት መካከል ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ተመልካች ፍርድ ቤት በያዘው ሚና ላይ የተፈጠረው ልዩነት እየሰፋ መሄዱን አሳይቷል። እንደ አፍሪቃ ህብረት ተንታኝ እና አማካሪ ሊዝል ሎቭ አስተያየት፣ የደቡብ አፍሪቃ ገዢው የአፍሪቃውያን ብሔረተኞች እንቅስቃሴ «ኤ ኤን ሲ» በፍርድ ቤቱ አኳያ ያለውን ጥርጣሬ የፓርቲው ዋና ጸሐፊ ግዌዴ ማንታሼ ፍርድ ቤቱን አደገኛ ሲሉ ነው የገለጹበት አነጋገራቸው አንፀባርቋል።

Südafrika Omar al-Baschir in Johannesburg
ፕሬዚደንት ኦማር ሀሰን ኤል በሺርምስል Reuters/S. Sibeko

« አል በሺር ይታሰራሉ አይታሰሩም በሚል መላ ምት በተሰማበት የአፍሪቃ ህብረት ጉባዔ በተካሄደበት ጊዜ እንኳን አንዳንድ ለ«ኤ ኤን ሲ » ቅርበት ያላቸው ሀያስያን ፍርድ ቤቱ እስካሁን ያሰረው አፍሪቃውያንን መሆኑን ጠቁመዋል፣ ፍርድ ቤቱ ያነጣጠረው በተለይ በአፍሪቃውያን ላይ ነው በሚል የአፍሪቃ ህብረት ያሰማው ቅሬታም በ«ኤ ኤን ሲ » እና ባንዳንድ የደቡብ አፍሪቃ ህብረተሰብም ዘንድ ሲሰነዘር ይሰማል። »

ይህ አቋሙም ውሎ አድሮ ከ« አይ ሲ ሲ » ለቆ ወደመውጣቱ ሊያመራ እንደሚችል ጠቋሚ ሊሆን ይችል እንደሆን ከዶይቸ ቬለ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሊዝ ሎቭ ሲመልሱ፣

Parteitag des ANC Südafrika
ግዌዴ ማንታሼ(በስተቀኝ)ምስል picture-alliance/dpa

« ወደዚያ የሚያመራ ይመስላል፣ እንደሚታወቀው የ« ኤ ኤን ሲ » ዋና ጸሐፊ ግዌዴ ማንታሼ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳረፉ ፖለቲከኛ ናቸው። ይሁንና፣ የህግ ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ ፍርድ ቤቱን ለቆ መውጣቱ ለደቡብ አፍሪቃ ቀላል አይሆንም፣ የተወሳሰበ ነው ምክንያቱም ፍርድ ቤቱ የተቋቋመበት የሮሙ ሰነድ በሀገሪቱ ሕግ ውስጥ ተካቶዋል። የፍርድ ቤቱን አባልነት ብትሰርዝም በሰነዱ የሰፈሩትን ውሳኔዎች ማክበር ይኖርባታል። ማለትም አባልነቷን ከሰረዘችም በኋላ እንበል የሱዳኑ መሪ አል በሺር ደቡብ አፍሪቃን ቢጎበኙ አስራ ለፍርድ ቤቱ ማስረከብ አለባት። እና ከ« አይ ሲ ሲ » መውጣት የምትችልበት ሂደቱ ለምክር ቤት መቅረብ ስለሚኖርበት ረጅም ነው የሚሆነው። »

እንደ ሊዝ ሎቭ ግምት ደቡብ አፍሪቃ ከ ከ« አይ ሲ ሲ » የምትወጣበት ድርጊት ከአንዳንድ የህብረተሰብ ክፍል እና ኦማር ሀሰን አል በሺር ከተከሰሱ ወዲህ ከፍርድ ቤቱ አባልነት የመውጣትን ሀሳብ ካራመደው ከአፍሪቃ ህብረት ድጋፍ ቢያስገኝለትም በዓለም አቀፍ አጋሮቹ ዘንድ ተዓማኒነቱን ያጣል።

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ