1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ አፍሪቃ «ነፃው ትውልድ»

ዓርብ፣ ሚያዝያ 17 2006

የደቡብ አፍሪቃ ህዝብ ነፃነቱን ካገኘ ከ20 ዓመት በኋላ የሀገሪቱ ወጣቶች ለመሆኑ ምን ያህል ተዋህደው እየኖሩ ነው? ብዙዎችእንደሚሉትግን ከሆነ አሁንም በሀብታም እና ደሀ ፣ በጥቁር እና ነጭ መካከል ልዩነቱ በሰፊው ይስተዋላል።

https://p.dw.com/p/1Bo4Q
Südafrika Born Free Generation Variante
ምስል picture-alliance/Yadid Levy/Robert Harding

ሁሉም የደቡብ አፍሪቃ ነፃ ትውልድ ወይም « ቦርን ፍሪ ጀነሬሽን» ናቸው። አንጋፋው የአፓርታይድ ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ከእስር ከተፈቱ በኋላ የተወለዱ ልጆች። ለነገሩ ሁሉም እኩል እድልና መብት አላቸው ሊባል ይችላል፤ ይሁንና በተግባር የተለያየ ህይወት ነው የሚመሩት። ቲፋኒ ከነዚህ የደቡብ አፍሪቃ «ነፃ ትውልድ» አንዷ ናት፤«መልካም፤ አዎ በነፃነት የተወለድን እና በነፃነት የምንፈልገውን የመወሰን አቅም ያለን ነን። ምን መሆን እንደምንፈልግ እራሳችን መወሰን እንችላለን። በተመሳሳይ ደግሞ በኢኮኖሚ እና ከሌሎች ጋር አብሮ መኖርን በተመለከተ ብዙ መቀየር ያለብን ነገሮች አሉ። አሁን ድረስ ሰዎች በቆዳቸዉ ቀለም፣ በመጡበት መንደር ወይም በሚናገሩት ቋንቋ ምክንያት ይጨቆናሉ።»

ቲፋኒ በጆሃንስበርግ ከተማ የዮንቨርስቲ ተማሪ ናት። የአካባቢ አጠባበቅ እና የስነምድር ምርምር ጂኦሎጂ ተማሪ ናት። ጥቁር ደቡብ አፍሪቃዊቷ በምትማርበት ከፍተኛ ተቋም፣ ከዘወትር አለባበሶች ሌላ፤ ቡርቃ፣ እንዲሁም የአይሁድ መለያ የሆነዉን ኮፍያ የሚያደርጉ ከተለያየ ቦታ የመጡ ተማሪዎች ይማራሉ። ይህ ለቲፋኒ የቀድሞው ዘረኝነት ቀስ በቀስ እየተመናመነ እንደሆነ የሚገልፅ ጥሩ ተስፋ ነው። ይሁንና ልዩነቱ የሚታይባቸዉ መንገዶች ዛሬም አሉ።

Südafrika Born Free
ነፃው ትውልድምስል Kerstin Welter

«ለምሳሌ አንዲት ጥቁር ልጅ ነጭ ፍቅረኛ ከያዘች በቃ የመጨረሻ የተሳካላት ይመስላታል። ለምን? ይህን በእውነት አላስፈላጊ እና ያለማወቅ ነው የምለው። እሷ ከሱ ትንሽ ከፍ ያለ ለቆዳ ቀለም የሚሰጥ የተፈጥሮ ንጥረ ነገር ስላላት? ቢሆንስ? የምንማረዉ በአንድ ትምህርት ቤት፣ የምንናገረው አንድ አይነት ቋንቋ፣ የምንማረው አንዳይነት ትምህርት። ለምን ይሆን ዛሬም ቢሆን አንዳንድ ሰዎች ከነጮች ጋር ስለሆኑ ብቻ የተለዩ መስሎ የሚሰማቸዉ? ከዚህ መላቀቅ ይኖርብናል። ዮንቨርስቲዉ ብዙ ረድቶኛል። እዚህ ሁሉም ተዋህዶ ነገር ግን ማንነታቸው ሳይቀይር እና ሳይረሳ ነው የሚኖረዉ።»

ቲፋኒ ከጆሀንስበርግ ወጣ ብላ ከምትገኝ ነጮች በብዛት ከሚኖሩበት አካባቢ ነው የመጣችው። የቲፋኒ እናት ከቤት ሠራተኝነት ተነስተዉ እስከ ሥራ አስኪያጅነት ደርሰዋል። ቲፋኒ እናቷ አርአያ እንደሆኗት እና ሁሌም እድሏን ተጠቅማ እንድትማር እና ጥሩ ደረጃ ላይ እንድትደርስ እንደሚመክሯት ትናገራለች። ለትምህርት ቤቷ አራት ታላላቅ ወንድሞቿ ይከፍሉላታል። ከቲፋኒ አጠገብ የትምህርት ቤት ጓደኛዋ አማንዳ ተቀምጣለች። አማንዳ ነፃ የትምህርት እድል አግኝታ ነው የምትማረው። ምንም እንኳን ወላጆቿ የተማሩ ቢሆኑም ለትምህርት ቤት ሊከፍሉላት አይችሉም ነበር። ሀብት አሁንም የደቡብ አፍሪቃ ወጣቶችን መለየቱን እንደቀጠለ ነው።

«የተወሰኑ ሀብታምና ሞልቃቃ ሴት ተማሪዎች አሉ። እና እኔ እንደሱ የተሞላቀኩ አይደለሁም እንድትይ ያደርግሻል። አባቴን ደውዬ፤ «አባዬዬዬ አዲስ የእጅ ስልክ እፈልጋለሁ ልለዉ አልችልም።» አንድ የምፈልገዉን ነገር ለማገኝነት በቂ ምክንያት ያስፈልገኛል። ሌላ ሰው ስላለው ብቻ እኔም ያስፈልገኛል ማለት አልችልም። እና አንዳንዴ ሆ! እናንተ ከኔ በጣም የተለየ ህይወት ነው ያላችሁ እንድል ያደርገኛል። እና ይህ ትንሽ አስገራሚ ነው።»

Bildergalerie Johannesburg Stadt zwischen Verfall und Wiederauferstehung
የጆሀንስበርግ ከተማምስል DW/T. Hasel

አማንዳ ብቻ ሳትሆን አሌክስ እና ሜጋንም ትምህርታቸዉን በጀመሩበት ወቅት ይህን ሁኔታ ታዝበዋል። ልዩነቱ ትዝብታቸው ከሌላኛው አቅጣጫ መሆኑ ብቻ ነው። ወጣቶቹ ሳንድቶን የሚገኝ የሀብታሞች የገበያ አዳራሽ ተቀምጠዋል። ሜጋን ኬፕታውን ውስጥ ጋዜጠኝነት ትማራለች። አሌክስ ደግሞ ስኮትላንድ ውስጥ ህክምና ታጠናለች። የእረፍታቸዉ ወቅት እንደመሆኑ ቤተሰቦቻቸዉን ለመጎብኘት መጥተዋል። የሚጠጡትን መጠጥ ካዘዙ በኋላ፣ ስለተማሩበት የግል ትምህርት ቤት፣ ስላላቸው ትልቅ ግቢ እና ወደ አውሮፓ ለዕረፍት ስለሚሄዱበት ቦታዎች ማውራት ጀመሩ። አስተዳደጋቸው ከነጭ ወላጆቻቸው ብዙም የተለየ አልነበረም።

«በተማርንበት ትምህርት ቤት ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የተዉጣጡ ነበሩ። ከስዌቶ የመጡ የፃ የትምህርት እድል ያገኙ ሴት ተማሪዎች አብረዉን ተምረዋል። ይሁንና ለእነሱ ቀላል አልነበረም። እኛ በመኪና ስንመላለስ እነሱ በአውቶቡስ መጓጓዝ ነበረባቸው። መጀመሪያ አካባቢ ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክም አልነበራቸውም። ያንን ሁሉ ሃብት ከጎናቸው ሲመለከቱ ለእነሱ ከባድ የነበረ ይመስለኛል። አንዳንዴ ጥሩ ስሜት አይሰማኝም ነበር። በእርግጥ አብዛኞቹ ጎደኞቼም ከደህና ቤተሰብ የመጡ ናቸው። እንዲያም ሆኖ ማንም ቢሆን የሚናገረዉን በጥንቃቄ መምረጥ ይጠበቅበታል።»

ያለፈዉን ሁኔታ በማስተዋል አሌክስ እና ሜጋን ልዩነቱ እንዲስተካከል የበኩላቸዉን ለማድረግ በነፃነት ይነጋገራሉ። ስለፖለቲካዉ፤ እንዲሁምድህነቱ እንዲወገድና በደቡብ አፍሪቃ የተሻለ ነገር እንዲኖር ከጓደኞቻቸዉ ጋ ይወያያሉ። ይህም ሆኖ ግን በስብስቡ ዉስጥ የሰዎች ስብጥር እንደሌለ ነው ሜጋን የምትገልፀው።

«ለምን እንደሆን እንጃ፤ ሁል ጊዜ ተመሳሳይ የሆኑ አይነት ሰዎች ናቸው አንድ ላይ የሚሰበሰቡት። ጥቁር ጓደኞቼም ይሁኑ ሌሎች አብረውኝ ያሉ ጓደኞቼ፣ አብሬያቸው ለመዝናናት የምሄደው እና አብሬያቸው አንዳንድ ነገሮችን የማደርግ በሙሉ ተመሳሳይ ተሞክሮ ነው ያላቸው። እንደ ወላጆቻችን ማለት ለምሳሌ፤ ጥቁር ጓደኞች አሉሽ? ልዩነት አለው? ብለው እንደሚጠይቁት አይሁን እንጂ፤ በጋራ ተዋህዶ የመኖሩ ነገር የተሳካ ይመስላል። ያም ቢሆን ግን የሚቀር ነገር አለ። »

Bildergalerie Johannesburg Stadt zwischen Verfall und Wiederauferstehung
በማንሰራራት ላይ ያለችው የጆሀንስበርግ ከተማ

ጄፍሪ ከሀብታሞቹ ከተማ ሳንድቶን፤ ጥቂት ኪሎ ሜትር ርቆ ጥቁር እና ደሀው ማህበረሰብ በሚገኝበት አሌክሳንድራ ነው የሚኖረው። በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች በተጨናነቀ ሁኔታ ይኖራሉ። ከእያንዳንዱ ቤት ጀርባ በቆርቆሮ የተመቱ ቤቶች እና በጨርቅ የተወጠሩ ጎዶዎች ይታያሉ። አካባቢው ጥሩ ጠረን የለውም፤ ቁሻሻ በየቦታው ተጥሏል። በዚህ አካባቢ ሰባት የነጭ ቤተሰቦች ብቻ ናቸው የሚኖሩት። በዚህ የተነሳ የጄፍሪ ጎደኞች እንብዛም የተዋሐዱ አይደሉም። ይሁንና ጄፍሪ ይህ በቅርቡ እንደሚቀየር ባለሙሉ ተስፋ ነው።

« አዎ! ብዙ ልዩነቶች አሉ ፤ ይህ አሁን ያበቃል ብዬም አላስብም። የጊዜ ጉዳይ ነው። የሀገራችን ዴሞክራሲ ገና እኮ 20 ዓመት ብቻ ነው። ገና ለጋ ነዉ። ሁልጊዜ ከሁሉም ነገር መጥፎ ገፅታ አይጠፋም። ዋናው ነገር ይህንን መጥፎ ገፅታ እንዴት እንደምትለዉጪው ነው። የፈለኩበት ቦታ መሄድ እችላለሁ። አንዳንዴም ሰዎች በቆዳዬ ቀለም የተነሳ በተለየ መልኩ ይቀበሉኛል። ይሁን! እኔ ምንም አይመስለኝም። መቆጣት ምንም ለዉጥ አያመጣም። እንደዉም ነገሮች እንዲባባሱ ያደርጋል።»

እንደ ጄፍሪ ሁሉ አብዛኞቹ አፓርታይድ በኋላ ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ የተወለዱ ወጣቶች አዎንታዊ አመለካከት ያላቸዉ እዉነታዉን ያዉቁታል። ሁለት ሶስተኛው የነሱ ትውልድ ሥራ እና የትምህርት እድል አለማግኘቱ የዮንቨርስቲ ተማሪ የሆኑት ቲፋኒ እና አማንዳንም ያሳስባቸዋል። አማንዳ ደቡብ አፍሪቃ አፓርታይድን ወደኋላዋ ትታ ወደፊት እስክትራመድ አሁንም ጊዜ ይፈጃል ትላለች።

Picture-Teaser Südafrika 20 Jahre nach der Apartheid
ምስል DW/T. Hasel

« አብዛኞቹ የኔ ጓደኞች እዚህ ጆሀንስበርግ ውስጥ አፓርታይድን ረስተን ወደፊት ብንመለከት ጥሩ ነበር ይላሉ። ነገር ግን ወደቤት ስንመለስ የደቡብ አፍሪቃ «ነፃ ትውልድ» ነን ልንል የቻልነው እነሱ ለነፃነታቸው ስለተዋጉ በመሆኑና ይህንን መርሳት እንደሌለብን ይነግሩናል። እኔ የደቡብ አፍሪቃን ያለፈ ጊዜ ማንፀባረቅ አልፈልግም። አዎ! በቀል የሰው ልጅ ተፈጥሮ ነው። ግን መበቀልን አልፈልግም። ባለው ሁኔታ መደሰት ነው የምፈልገው። ነገር ግን መድረስ ያለብን ቦታ አሁንም አልደረስንም። »

የአፓርታይድ ማክተም ለአዲሱ ትውልድ ጥሩ እድል እንደከፈተለት ኬርስቲን ያነጋገረቻቸው ወጣቶች በሙሉ ይናገራሉ። ማንኛቸውም የትኛውም የቆዳ ቀለም ይኑራቸው፣ ሀብታምም ይሁኑ ደሀ ፤ ሁሉም እንደ አርዓያ የሚያነሱት የኔልሰን ማንዴላን ሁሉም በነፃነት ያለመድሎ የሚኖርበትን ራዕይ ነው።

የዶይቸ ቬለዋ ኬርስቲን ቬልተ በደቡብ አፍሪቃ እየተዘዋወረች ከደቡብ አፍሪቃ «ቦርን ፍሪ ጀነሬሽን» ወይም ነፃ ትውልዶች ጋር የነበራትን ቆይታ በተጨማሪ በድምፅ ዘገባ ያገኙታል።

ኬርስቲን ቬልተ

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሠ