1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ አፍሪቃ ኤኮኖሚ ድክመት

ረቡዕ፣ ሰኔ 20 2004

ደቡብ አፍሪቃ በተፈጥሮ ሃብት እጅግ የታደለችና ከሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት ይልቅ የተራመደች ብትሆንም በወቅቱ በክፍለ-ዓለሚቱ ከሚታየው ዓመታዊ የኤኮኖሚ ዕድገት መጠን አንጻር በዝቅተኛው ደረጃ ላይ ነው የምትገኘው።

https://p.dw.com/p/15LfI
A view of one of the largest steel producing companies in South Africa's industrial site close to the industrial port of Saldanha bay, South Africa, Saturday, March 8, 2008. As world economy have been under sever pressure with falling American house and stock prices, South Africa is facing an added energy crisis.(ddp images/AP Photo/Schalk van Zuydam)
የደቡብ አፍሪቃ ኤኮኖሚምስል AP

ደቡብ አፍሪቃ በተፈጥሮ ሃብት እጅግ የታደለችና ከሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት ይልቅ የተራመደች ብትሆንም በወቅቱ በክፍለ-ዓለሚቱ ከሚታየው ዓመታዊ የኤኮኖሚ ዕድገት መጠን አንጻር በዝቅተኛው ደረጃ ላይ ነው የምትገኘው። አገሪቱ ያላት የተፈጥሮ ሃብት በ 2,5 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል። በማዕድን ከሰል፣ ወርቅ። ፕላቲን፣ አቶም ቦምብ መሥራት በሚያስችለው ንጥረ-ነገር ዩራኒየም፣ አልማዝና ሌላም ጸጋ የታደለች አገር ናት። ሆኖም ግን ጥሬው ሃብት በገበያ ላይ እጅግ ይፈለግ በነበረባቸው ባለፉት ዓመታት የተጠቀመችው በጣሙን ጥቂት ነው። የኤኮኖሚ ጠበብት የተገኘውን ጥቅም ከአማካይ መጠን በታች ነበር ይሉታል።

አሁን በወቅቱ ደግሞ የጥሬ ሃብት ፍላጎት በገበዮች በማቆልቆል ላይ ሲሆን የወርቅ ዋጋ ለዝቧል፤ በአገሪቱ የመጀመሪያዎቹ የፕላቲን ማዕድኖችም በመዘጋት ላይ ናቸው። የተቀረው የአፍሪቃ ክፍል ከአምሥት እስከ ሰባት በመቶ የኤኮኖሚ ዕድገት እያሳየ ሳለ የደቡብ አፍሪቃ ዕርምጃ በአንጻሩ በ 2,7 ከመቶ የተወሰነ ሆኖ ይገኛል። ሃቁ ይህ በመሆኑም ደቡብ አፍሪቃ አስቸኳይ ውሣኔን ከሚጠይቅ መንታ መንገድ ላይ መድረሷን ነው ለምሳሌ የአገሪቱ ቀደምት የኤኮኖሚ ባለሙያ ማይክ ሹስለር የሚናገሩት።

«በ 2001 ዓመተ-ምሕረት 5,2 ሚሊዮን ስራ የሌላቸው ስራ ፈላጊዎች ነበሩን። ታዲያ በዚያን ወቅት መንግሥት ይህንኑ የስራ አጡን አሃዝ በግማሽ እንደሚቀንስ አስታውቆ ነበር። ግን ከዚያን ወዲህ የስራ አጡ ቁጥር 50 በመቶ መቀነስ ሣይሆን 50 በመቶ ነው የጨመረው። ዛሬ የአገሪቱ ስራ አጦች ቁጥር 7,7 ሚሊዮን ሲደርስ እነዚህም የግድ አንድ ነገር ማግኘት ይፈልጋሉ»

እንግዲህ በወቅቱ 7,7 ሚሊዮን ስራ አጦች በ 7,3 ሚሊዮን ቋሚ ተቀጣሪዎች አንጻር ቆመው ነው የሚገኙት። ታዲያ ከሚሰራው የማይሰራው መብዛቱ ደግሞ ለቀውስና ለዓመጽ አመቺ ሁኔታን ሊፈጥር የሚችል ነው። ይህን አገሪቱን የሚያስተዳድረው የአፍሪቃው ብሄራዊ እንቅስቃሴ ANC-ም ሳይገነዘበው አልቀረም። ሆኖም ግን ጎልድፊልድስ በመባል የሚታወቀው የአገሪቱ የወርቅ ኩባንያ አፈ-ቀላጤ ስቬን ሉንሸ እንደሚሉት ችግሩ መንግሥት የተሳሳተ ውሣኔ ላይ መድረሱ ነው።

«መንግሥት የያዘው የኤኮኖሚ መርህ ከስራ አጦች ይልቅ ስራ ላላቸው ሰዎች ይበልጡን ትኩረት የሚሰጥ ነው። የአገሪቱ የሙያ ማሕበራትም እርግጥ ጠንካራና በኤኮኖሚ ረገድ እጅግ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማድረግ የሚችሉ ናቸው። እና ጥሩ ደሞዝ ባያስከፍልም እንኳ የበለጠ ስራ እንዲገኝ ምናልባት ሥልጣናቸውን በመጠኑም ቢሆን መቀነሱ ግድ ነው»

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ከ 2010 የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር በኋላ ያብባል ተብሎ የተጠበቀው የመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦት እንደታሰበው አገሪቱን አላጥለቀለቀም። እርግጥ ቻይና ገብታለች፤ የአሜሪካው የንግድ ግዙፍ ዎልማርትም እንዲሁ! የጀርመን የአውቶሞቢል ኩባንያዎች BMW ዳይምለርና ፎልክስዋገንም የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት እንደ መለያ ሰሌዳው አድርጎ በጥሩ ሁኔታ ስለሚያስተናግዳቸው በአገሪቱ ሕያው ናቸው።

አንዱ የደቡብ አፍሪቃ ችግር በመንግሥቱ ካቢኔ ውስጥ በአንድ ወገን ሶሻሊስቶችና በሌላ በኩልም ለዘብተኛ የገበያ ኤኮኖሚ መሠረተ-ዓላማ ደጋፊዎች ፊት ለፊት ተቀምጠው የሚገኙ መሆናቸው ነው። አንዱ ወገን ንብረት በመንግስት እንዲወረስና ልዩ ግብር እንዲከፈል ሲጠይቅ ሌላው በፊናው የመንግሥት ተጽዕኖ የሌለበት ልዩ የኤኮኖሚ ክልል እንዲኖር ይጠይቃል። እንደ አገሪቱ ታዋቂ የኤኮኖሚ መጽሄት ፋይናንሺያል ሜይል ምክትል ዋና አዘጋጅ እንደ ማክስ ጌብሃርድት ከሆነ ሁኔታው በጣሙን የተቃወሰ ነው።

«እያንዳንዱ ጋሪውን ወደ ሌላ አቅጣጫ ይጎትታል። መንገዱን የሚወስን ግን ማንም የለም»

ደቡብ አፍሪቃ እንግዲህ በክፍለ-ዓለሚቱ ያላትን ግንባር-ቀደም ሚና ልታጣ ወዲያ ወዲህ እየተንገዳገደች ነው። ናይጄሪያና ግብጽ እስከፊታችን 2020 ድረስ ታላላቆቹ ባላ ኤኮኖሚዎች በመሆን ሊደርቧት እንደሚችሉ ያታመናል። ቀደምቱ የኤኮኖሚ ባለሙያ ማይክ ሹስለር አፍሪቃ ከደቡብ አፍሪቃ ሣይሆን በተቃራኒው ደቡብ አፍሪቃ ከአፍሪቃ መማር አለባት ባይ ናቸው። ለዚህም የሚሰጡት ምክንያት በሌሎች የክፍለ-ዓለሚቱ አካባቢዎች መዋዕለ-ነዋይን በስኬት መሳብ ሲቻል በደቡብ አፍሪቃ ይህ ሊከሰት አለመቻሉን ነው። የኤኮኖሚው ጋዜጠኛ ማክስ ጌብሃርትም ቢሆን ከዚህ የተለየ አስተሳሰብ የላቸውም።

«የሚያስፈልገን ኩባንያዎችን የሚያቀርብ ሁኔታን የሚፈጥር መንግሥት ነው። ምክንያቱም የሥራ መስኮችን የሚከፍተው መንግሥት ሣይሆን የኤኮኖሚው ዘርፍ መሆኑን እናውቃለን»

ያም ሆነ ይህ የደቡብ አፍሪቃ የወደፊት የስኬት ተሥፋ የራሷ ክፍለ-ዓለም ለመሆኑ ጥርጥር አይኖርም። በዚህ ብዙዎች የኤኮኖሚ ባለሙያዎች ይስማማሉ። ደቡብ አፍሪቃ ጠንካራ የፊናንስ ዘርፍና አገልግሎት ስጭ መስክ፤ እንዲሁም ኢንጂነሮችና ዕውቀት ሲኖራት አፍሪቃ ውስጥ መዋዕለ-ነዋይ ለማድረግም የሌላውን የዓለም ክፍል ያህል የሚከብዳት ወይም የሚያስፈራት አይሆንም። ደቡብ አፍሪቃ ታዲያ ለተቀረው አዳጊ ክፍለ-ዓለም በር ከፋት ልትሆን ትችልም ይሆናል። ግን ማይክ ሹስለር እንደሚሉት እርግጥ በመጀመሪያ ትክክለኛውን መንገድ ለመምረጥ መወሰኗ ግድ ነው።

«ደቡብ አፍሪቃ ይህን እንደምታደርግ ተሥፋ አለኝ። ነገር ግን የሚቀጥሉት አምሥትና አሥር ዓመታት ምናልባት ከባድ የሚሆኑ ይመስለኛል። በበኩሌ አሁን ገንዘቤን ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ስራ ላይ ለማዋል አልፈልግም»

ደቡብ አፍሪቃ እንደ ሶሥተኛ ዓለም ሃገር ከባሕር ማዶ ጋር ስትነግድ መኖሯን ስትኮራበት ነበር የቆየችው። አሁን ግን ጊዜው እየተለወጠ መሄዱን መገንዘቧም አልቀረም። በፊናንስ ቀውስ ሳቢያ በተለመደ የአውሮፓ ገበያዋ የውጭ ንግዷ ማቆልቆልና ሌሎች ምክንያቶችም አሁን ዓይኗን ድሃ ጎረቤቶቿ ላይ እንድታሳርፍ አድርገዋል። ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ በምዕራባውያን ግፊት ከኢራን የሚያስገቡትን ነዳይ ዘይት እንዲቆርጡ ከተደረጉ በኋላ አሁን በቅርቡ እንደተናገሩት አገራቸው ናይጄሪያን በመሳሰሉ ሃገራት ላይ እያተኮረች ነው።

በኑክሌያር ፖሊሲዋ የተነሣ ማዕቀብ የተጣለባት ኢራን ለደቡብ አፍሪቃ ዋነኛዋ ነዳጅ ዘይት አቅራቢ ሆና ቆይታለች። ደቡብ አፍሪቃ ባለፈው ሚያዚያ ከኢራን ያስገባችው ጥሬ ዘይት ቀደም ካለው ወር ሲነጻጸው በ 3 ከመቶ ወደ 286 ሺህ ቶን ነበር የቀነሰው። በአንጻሩ ከናይጄሪያ የሚገባው በተመሳሳይ ጊዜ በአምሥት ዕጅ በመጨመር ከ 615 ሺህ ቶን በላይ ሆኗል።

እርግጥ የደቡብ አፍሪቃ ንግድ ባለፈው አሠርተ-ዓመት ቀስ በቀስ እያደገ መምጣቱ ባይቀርም በአፍሪቃ በማዕድን፣ በግንቢያና በአልባሳት መስክ በሚገባ ከተቆናጠጡት ከቻይናና ከሕንድ ሲነጻጸር ግን ገና ብዙ ኋላ የቀረ ነው። ይህ እርግጥ የአፓርታይዱ ዘመን የወለደው ቅርስ ነው። የኬፕታውኑ ውሁድ የነጮች መንግሥት ከአፍሪቃ ይልቅ ከአውሮፓ ጋር ነው የንግድ ትስስር አድርጎ የኖረው። በዚህ ደግሞ አገሪቱን ትልቅ ዕድል ነው ያመለጣት።

ደቡብ አፍሪቃ ፈጣን እድገት ባለባቸው አካባቢዎች ላይ እንድታተኩር ከትልቁ የንግድ ሸሪኳ ከአውሮፓ የፊናንስ ቀውስ ሁኔታ ጠቃሚ ትምሕርት ነው የቀሰመችው። የ 2008-2009 ዓለምአቀፍ የፊናንስ ቀውስ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥም በ18 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የኤኮኖሚ ችግርን ማስከተሉ አይዘነጋም።

በዚህ ዓመትም የኤውሮ ቀውስ ተጽዕኖ በአገሪቱ የፊናንስ ገበዮች ላይ እየተንጸባረቀ ነው። የአገሪቱ ምንዛሪ ራንድ ገንዘባቸው አስተማማኛ ካልሆነው ሌሎቹ አዳጊ ሃገራት ምንዛሪ አንዱ ሆኖ ቆይቷል። በቅርቡ በዶላር 8,71 በመሆን በሶሥት ዓመታት ያልታየ ማቆልቆል ደርሶበት ነበር። እርግጥ ጉዳቱ በፊናንሱ ዘርፍ ብቻ ተወስኖ አልቀረም። ተጽዕኖው ወደ አምራቹ ኤኮኖሚም እየተሻገረ ነው የመጣው። ወደ አውሮፓ የሚደረገው የውጭ ንግድ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ 28 ወደ 23 ከመቶ ወርዷል።

ችግሩን ለመወጣት ወይም የጎደለውን ለመሙላት ቁልፉ ያለው አምሥት በመቶና ከዚያም በላይ ዕድገት ከሚያደርጉት የአፍሪቃ ሃገራት ጋር መነገዱ ላይ ነው። ደቡብ አፍሪቃ በአካባቢው የምታደርገው የውጭ ንግድ የአካባቢው ንግድ ደረጃ በደረጃ በማደግ ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ 15 ወደ 17 በመቶ አድጓል። ሆኖም ደቡብ አፍሪቃ ከክፍለ-ዓለሙ ጋር የምታካሂደው ንግድ ከ 2001 ወዲህ ሶሥት ዕጅ ቢጨምርም በሌላ በኩል ከቻይና ብዙ ያነሰ ሆኖ ነው የሚገኘው።

የቻይና የአፍሪቃ ንግድ በተመሳሳይ ጊዜ 16 ዕጅ ነው ያደገው። ደቡብ አፍሪቃ 150 ሚሊዮን ሕዝብ ወዳላት ግዙፍ የአፍሪቃ አገር ወደ ናይጄሪያ ወይም ወደ ግብጽ የምታደርገው የውጭ ንግድም ከአቅሟ ሲነጻጸር እጅግ ዝቅተኛ ሆኖ ነው የሚገኘው። ባለፈው 2011 ደቡብ አፍሪቃ ወደ አፍሪቃ ባደረገችው የውጭ ንግድ ወደ ግብጽ የሄደው ከጠቅላላው 0,5 በመቶ፤ ወደ ናይጄሪያም 4 በመቶው ነበር። በንጽጽር የቻይና ድርሻ 16 እና 13 በመቶ ደርሷል።

እርግጥ ደቡብ አፍሪቃ በአካባቢዋ በደቡባዊው አፍሪቃ የኤኮኖሚ ማሕበረሰብ ውስጥ ጥሩ እንቅስቃሴና ድርሻ ነው ያላት። ከዚያ ውጭ ግን ለዓመታት ብዙ እንዳመለጣት አሁን ከመቼውም ይበልጥ ጎልቶ በመታየት ላይ ነው። ምርጫው እንግዲህ እስካሁን የጎደለውን በፍጥነት ማሟላት ብቻ ይሆናል።

መስፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ