1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ደቡቡ ንግድ መስፋፋት

ረቡዕ፣ መስከረም 20 2002

በአፍሪቃና በሌሎች አዳጊ የዓለም አካባቢዎች መካከል የሚካሄደው የደቡብ ደቡቡ ንግድ ባለፈው አሠርተ-ዓመት ስኬታማ እየሆነ ነው የሚጣው። በነዚሁ በታዳጊ አገሮች መካከል የሚካሄደው የምርት ንግድ በያመቱ በአማካይ የ 12,5 ከመቶ ዕድገት ይታይበታል።

https://p.dw.com/p/JutZ
ምስል AP

በበለጸገው ሰሜንና በደቡቡ ዓለም መካከል የሚካሄደው ንግድ ዕድገት በአንጻሩ ሰባት በመቶ ገደማ ቢሆን ነው። የደቡብ ደቡቡ ንግድ ዓለም በኤኮኖሚ ቀውስ በተወጠረበት በአሁኑ ወቅት እንኳ የዓለም ንግድን ሰድሥት በመቶ ድርሻ ይይዛል። ከዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስ ለማላቀቅ መውጫ መንገድ አድርገው የሚመለከቱት ጥቂቶች አይደሉም።

ታዳጊ አገሮች የደቡብ ደቡቡን ንግድ በማስፋፋት ዕርምጃቸውን ለማጠናከር ቆርጠው እንደተነሱ ባለፉት ዓመታት በያጋጣሚው ታይቷል። የአፍሪቃና የእሢያ፣ የደቡብ አሜሪካና የአረብ አገሮች፤ እንዲሁም ባለፈው ሣምንት ቬኔዙዌላ ላይ የተካሄደው የአፍሪቃና የደቡብ አሜሪካ መሪዎች ጉባዔ፤ ይሄው ፍላጎት የተንጸባረቀባቸው ነበሩ። በተለይ በአፍሪቃና በአሕጽሮት ብሪክ በመባል በሚጠሩት ራመድ ያሉ አገሮች ብራዚል፣ ሩሢያ፣ ሕንድና ቻይና መካከል የሚደረገው የንግድ ልውውጥ እጎ.አ. ከ 1985 እስከ 2007 ዓ.ም. ድረስ ከአሥር ዕጅ በላይ ነው የጨመረው።
በ 2007 ይሄው ንግድ ከ 256 ሚሊያርድ ዶላር በልጦ ነበር። ከጠቅላላው የአፍሪቃ ንግድ ቢነጻጸር 33 ከመቶውን ያህል ድርሻ የሚይዝ ነው። እርግጥ የአፍሪቃ ውስጣዊ ንግድ ዕድገት በጥቅሉ ከደቡብ ደቡቡ ሲነጻጸር ዝግታ ይታይበታል። በተመሳሳይ ጊዜ ሰባት በመቶ ብቻ ነው ያደገው። በሌላ በኩል በምሥራቅና ደቡብ ምሥራቅ እሢያ የአካባቢው ውስጣዊ ንግድ ከጠቅላላው ከአርባ በመቶ የበለጠውን ድርሻ ይይዛል። የተጣጣመ ሚዛን ለጊዜው ጎልቶ አይታይም። ይህም የአፍሪቃን ተጠቃሚነት ለጊዜውም ቢሆን አጠያያቂ የሚያደርግ ነው።

በደቡብ አሜሪካ ላይ እናተኩርና በአካባቢው ለደቡብ ደቡቡ ንግድ መስፋፋት በተቀዳሚነት ግፊት ሲያደርጉ የቆዩት የብራዚሉ ፕሬዚደንት ሉዊስ-ኢናሢዮ-ዳ-ሢልቫ ናቸው። የቀድሞ የሙያ ማሕበር መሪ ብራዚልን ከሌሎች ታዳጊና ራመድ ያሉ አገሮች ጋር በተሻለ የንግድ መረብ ማስተሳሰሩን ግብ አድርገው ከያዙት ቆየት ብለዋል። ቀደም ብለው በ 2004 የሣኦ-ፓውሎ የተባበሩት መንግሥታት የንግድ ጉባዔ ላይ ያነሱት ጉዳይ ነበር።

“ይህ አዲስ መልክዓ-ምድር የሰሜን ደቡቡን ንግድ የሚተካ መሆን የለበትም። የበለጸገው ሰሜን ወደፊትም ክብደት ያለውና የማይተው ሸሪክ ሆኖ ይቀጥላል። የውጭ ንግዳችን ዒላማ፣ የመዋዕለ ነዋይና የከፍተኛ ቴክኖሎጂ ምንጫችን እንደሆነ ግልጽ ነው። ሆኖም ግን የደቡቡ ዓለም ብሄራዊ ኤኮኖሚዎች በተሻለ ሁኔታ ሊጣጣሙ የሚችሉባቸውን አዳዲስ ጥርጊያዎች ለመክፈትና ትብብርን ለማራመድ እንፈልጋለን”

የብራዚል ውጥን ከጊዜ በኋላ የታሰበውን ፍሬ መስጠቱ አልቀረም። ብራዚል አሁን ከሰሜኑ ዓለም ይልቅ ለታዲዎቹና በመራመድ ላይ ላሉት አገሮች የበለጠ ምርት ትሸጣለች። ከዩ.ኤስ.አሜሪካና ከጎረቤቲቱ አርጄንቲና ቀጥላ ሶሥተኛዋ ዋነኛ የንግድ ሽሪኳ ቻይና ናት። የብራዚል ኩባንያዎች ከቻይና ቀጥሎም በተለይ በአፍሪቃ ላይ አተኩረዋል። ፕሬዚደንት ሉዊስ-ኢናሢዮ-ዳ-ሢልቫ በሥልጣን ጊዜያቸው አፍሪቃን 11 ጊዜ መጎብኘታቸው ፍላጎቱ ምን ያህል የጠነከረ እንደሆነ የሚያመለክት ነው። የአገሪቱ የውጭ ንግድና የመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦት አራማጅ ተቋም አፔክስም ንግዱን ለማስፋፋት የሚያደርገውን ጥረት ሲያጠናክር ነው የሚታየው። አንድ የብራዚል ኩባንያዎች ልዑካን ቡድንም ከሶሥት ሣምንታት ገደማ በፊት ደቡብ አፍሪቃን ጎብኝቶ ነበር። የጉዞው ዓላማ የአፔክስ ፕሮዤ ሃላፊ ማውሪሢዮ ማንፍሬ እንዳስረዱት፤

“ሃሣባችን ግንኙነቱን ማስፋፋትና ማጠናከር ነው። እኛ እዚህ የምንወክለው የብራዚልን ኩባንያዎች ጥቅም ብቻ አይደለም። ወደ አገር የሚገቡ ምርቶችንም እንፈልጋለን። በዚህ ዓለምአቀፍ ቀውስ በሰፈነበት ሰዓት አዲስ የንግድ መንገዶችን ለመክፈት ነው የምንሻው”
ብራዚል ከሣሃራ በስተደቡብ ወደሚገኙት የአፍሪቃ አገሮች የምታስገባው ምርት ባለፉት አሥር ዓመታት በስምንት ዕጅ ገደማ ከፍ ብሏል። ባለፈው ዓመት ከአሥር ሚሊያርድ ዶላር ሲበልጥ ይህም ከብራዚል አጠቃላይ የውጭ ንግድ አምሥት በመቶው መሆኑ ነበር። እርግጥ ከአምሥት ሚሊያርድ የሚበልጠው የውጭ ንግድ የተካሄደው ከሶሥት አገሮች ከአንጎላ፣ ከደቡብ አፍሪቃና ከናይጄሪያ ጋር ነው። ሆኖም በዚሁ ተወስኖ የሚቀር አይመስልም። በተለይ በዓለምአቀፉ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ የተነሣ በአፍሪቃ አዳዲስ ገበዮች መገኘታቸው የሚማርክ እንደሚሆን የደቡብ ምሥራቅ ብራዚል ፌደራል ክፍለ-ሐገር የሚናስ-ጌራይሽ የውጭ ንግድ ተቋም አስተዳዳሪ የሆርሄ-ዱዋርቴ-ዴ-ኦሊቪየራ ዕምነት ነው።

“ራመድ ያሉት አገሮች በዓለምአቀፉ ቀውስ ከሌላው ሲነጻጸር ጥቂት ነው የተጎዱት። እናም በዚህ በብራዚል ለመለስተኛው መካከለኛና ዝቅተኛ የሕብረተሰብ ክፍሎች የፍጆት ዕቃ ለሚያመርቱት ትናንሽ ፋብሪካዎች ተስማሚ ገበዮች አሉ። እነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎችና ፈጂዎች ደግሞ በአፍሪቃና በመካከለኛ ምሥራቅም የምናገኛቸው ናቸው”

ቻይና ለምሳሌ ሁለት ሶሥተኛውን ጥሬ ዕቃ ባቄላና ጥሬ ብረትን የመሳሰለውን ከብራዚል ስትገዛ ተሰርተው ያለቁ ምርቶችን ግን አትወስድም። በአንጻሩ ብራዚል ለአፍሪቃ የምትሸጠው ምርት በዓይነቱ ብዙ ነው። ሲሦው ብቻ ነው በጥሬ መልክ የሚላከው። ሁለት-ሶሥተኛው በአንጻሩ ተሠርቶ ያለቀ ምርት ነው። ይህም ከጨርቃ-ጨርቅ እስከቤት ዕቃና እስከ እርሻ ልማት መኪናዎች ብዙ ዓይነት ምርቶችን ያዳርሳል። ለዚህም የብራዚሉ የንግድ ባለሙያ ካርሎስ አቢጃኦዲ እንደሚሉት ምክንያት አልጠፋም።

“አፍሪቃ ገና የራሷን ኢንዱስትሪ ማሳደግ አልቻለችም። ስለዚህም አፍሪቃውያን ከብራዚል የኢንዱስትሪ ምርቶች ብዙውን ይገዛሉ። ብራዚል ለአፍሪቃ ቀረብ ያለችም ናት። ከዚሁ ሌላ ተመሳሳይ ወግም አለን። አንጎላንና ሞዛምቢክን ከመሰሉት ፖርቱጋልኛ ተናጋሪ አገሮች ጋር ደግሞ ቋንቋውም አንድ ዓይነት ነው። ይህም ቀድሞ በተለይ ከሰሜኑ የኢንዱስትሪ አገሮች ይገዙ የነበሩ ምርቶችን በገበያ ላይ አቅርቦ መሸጡን ያቀለዋል። እርግጥ እነዚህ አገሮች በወቅቱ ለፉክክር ብቁ አይደሉም ወይም ኢንዱስትሪዎቻቸው በቀውሱ ተመትተዋል”

ያም ሆነ ይህ በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም የብራዚል ዋነኛ የንግድ ሸሪክ አንጎላ ናት። ከቀውሱ በፊት በነበሩት ዓመታት ከፍተኛ የኤኮኖሚ ዕድገት ይጠበቅባት በነበረችው በነዳጅ ዘይት ሃብት የታደለች አገር ብዙ የብራዚል ኩባንያዎችም ገንዘባቸውን በሥራ ላይ ያውላሉ። በከፊል በመንግሥት ዕጅ የሆነው ነዳጅ ዘይት አውጭ ኩባንያ ፔትሮብራስ ለምሳሌ በአንጎላ ጠረፍ ላይ በዘይት ፍለጋ ተግባር ተሰማርቶ ይገኛል። ኩባንያው በመንገድ ሥራ ላይ የተሰማራም ነው። በ 370 ሚሊዮን ዶላር አዲስ የሲሞንቶ ፋብሪካ በማነጽ ላይ የሚገኝ ሌላ የብራዚል ኩባንያም እንዲሁ አለ።

ብራዚል በሚቀጥሉት ዓመታት ከሞዛምቢክ ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት በሰፊው እንደምታጠናክር ነው የሚጠበቀው። ከወዲሁ አንድ የብራዚል የማዕድን ኩባንያ በማዕከላዊው ሞዛምቢክ የሚገኝ የማዕድን ከሰል ለማውጣት 1,3 ሚሊያርድ ዶላር መድቦ እየሰራ ነው። ማዕድኑ እስካሁን በዓለም ላይ ያልተነካው ታላቁ ምንጭ ሲሆን ከመቶ ዓመት በላይ ከፍተኛ ጥራት ያለው ከሰል ሊወጣበት እንደሚችል ነው የሚታመነው።

ለማንኛውም የደቡብ ደቡቡ ንግድ በዓለምአቀፉ ቀውስ ሳቢያ ጫና እንደገጠመው ይቀጥላል። ለአካባቢው ንግድ አንዱ ድክመት እስከቅርቡ በተመሳሳይ ጥሬ ዕቃዎች ላይ ማተኮርና እንዲያም ሲል የፉክክሩ መጠናከር ሆኖ ቆይቷል። በነዚህ ሃገራት መካከል ያለው የንግድ ግንኙነት ትልቅ እመርታ ያደረገው በሕንድና በቻይና የተፋጠነ የኢንዱስትሪ ዕድገትና ይሄው ያስከተለው የፍጆት ፍላጎት መጨመር ነው። በሌላ በኩል የደቡቡ ዓለም አገሮችም ቀላል ጉዞ አይጠብቃቸውም። የዓለም ባንክ እንደሚገምተው የእሢያ የውጭ ንግድ ለምሳሌ በዚህ ዓመት ካለፈው ሲነጻጸር ከአርባ በመቶ በላይ ያቆለቁላል። የዓለም ኤኮኖሚ ቀውስ በፍጥነት መገታቱ እስካሁን የተገኘው ዕርምጃ ቀጣይነት እንዲያገኝ ግድ ነው።

MM/DW/AA