1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የደኅንነት ሥጋት የተጫናቸው የውጪ ባለወረቶች

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ጥቅምት 16 2009

በኢትዮጵያ የፍራፍሬ እና አበባ እርሻ ስራ ላይ የተሰማሩ የውጪ ኩባንያዎች በተቃውሞ የከፋ ጉዳት ከደረሰባቸው በኋላ መፃኢ ዕጣ ፈንታቸው አስግቷቸዋል። በባሕር ዳር አካባቢ የአበባ እርሻ የወደመበት ኤስሜራልዳ የተሰኘው የኔዘርላንድስ ኩባንያ ሥራውን አቋርጧል። ለሠራተኞቻችን እና ለንብረታችን የደኅንነት ዋስትና እንሻለን የሚሉም አሉ። 

https://p.dw.com/p/2Rk04
Äthiopien Gedeo Grundstücke Brand Protest
ምስል W/O Aynalem/R.Abeba

ኢትዮጵያ፤ ሕዝባዊ ተቃዉሞና የባለሐብቶች ሥጋት

መቀመጫውን በኔዘርላንድስ ያደረገው አፍሪቃ ጁስ ቲቢላ ኩባንያ ከአዲስ አበባ በሥተ-ደቡብ ምሥራቅ 150 ኪ.ሜትር ርቀት በላይኛው የአዋሽ ተፋሰስ በ500 ሔክታር የእርሻ ማሳ ላይ ያመረታቸው ፍራፍሬዎች ዘንድሮ ጭማቂ አይሆኑም። ኩባንያው ለአውሮጳ ገበያ የሚያቀርባቸው ምርቶቹንም አይልክም። የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚዎች መስከረም 24 ቀን 2009 ዓ.ም. የኩባንያው የጭማቂ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ላይ የፈጸሙት ጥቃት የወትሮው የሥራ ዑደቱን አስተጓጉሎበታል። ሐሪ ቫን ኔር የአፍሪቃ ጁስ ቲቢላ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ናቸው።

«የማቀነባበሪያ ማሽናችን ጉዳት ከገጠማቸው ንብረቶች መካከል አንዱ ነው። ቀደም ሲል በቦታው ያልነበረ እና በ2009 ዓ.ም. ሥራውን ስንጀምር የተከልነው የማቀነባበሪያ ፋብሪካ ወድሟል። በዚህም ምክንያት አሁን የውጪ ንግዳችን እየተከናወነ አይደለም። በዚህም የከፋ ተፅዕኖ ደርሶብናል። ወቅቱ ዋነኛ የማምረቻ ጊዜያችን በመሆኑ ፍራፍሬዎቹ ዝግጁ ናቸው። ይሁንና የማቀነባበሪያ ፋብሪካ ከሌለ ፍራፍሬዎቹ ይባክናሉ።»

Äthiopien Gedeo Grundstücke Brand Protest
ምስል W/O Aynalem/R.Abeba

ከሰባት ዓመታት በፊት የተመሠረተውና የቀድሞውን የመንግሥት የእርሻ ማሳ የገዛው አፍሪቃ ጁስ ኩባንያ በኢትዮጵያ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ጥቃት የተሰነዘረበት ብቸኛ ኩባንያ አይደለም። የአበባ እርሻዎች፤ የፕላስቲክ እና የስሚንቶ ፋብሪካዎች፤ መዝናኛዎች ተመሳሳይ ዕጣ ገጥሟቸዋል። ኢትዮጵያ ከቀጣናው አገራት አኳያ በነበራት አንፃራዊ መረጋጋት፤ መንግሥት ባቀረባቸው ማበራታቸዎች እና ርካሽ የሰው ጉልበት ለውጪ ባለወረቶች ተመራጭ መዳረሻ የነበረች ቢሆንም አሁን ግን ሁነኛ ፈተና ገጥሟታል። ሐሪ ኔር ቫር ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ከአፍሪቃ ጁስ የማቀነባበሪያ ፋብሪካ ባሻገር የሠራተኞች መኖሪያዎች እና ተሽከርካሪዎች ጭምር ጥቃት ተፈፅሞባቸዋል። ዋና ሥራ አስፈፃሚው መስከረም 4 የደረሰዉን እንዲህ ያስታውሱታል።

«በእኛ በኩል እስካሁን ባለን መረጃ እጅግ በርካታ ሰዎች ወደ ኩባንያችን ቅጥር ግቢ ገብተዋል።  ቅጥር ግቢው ከገቡ በኋላ ንብረቶቻችንን ማውደም እና ሥርቆት ጀመሩ። አሁን የምናውቀው ድርጊቱን የፈጸሙት በመቶዎች የሚቆጠሩ መሆናቸውን ነው። በኩባንያው ቅጥር ግቢ ውስጥ ይገኙ የነበሩ ወርክሾፖች፤ መጋዘኖች፤ ቢሮዎች፤ የሠራተኞቻችን የመኖሪያ ቤቶች፤ ተሽከርካሪዎች እና ትራክተሮች እንዲሁም ማሽኖች ወድመዋል አለያም ተሰርቀዋል።»

አፍሪቃ ጁስ ኩባንያ በዕለቱ የደረሰውን ኪሳራ እያጠና መሆኑን የተናገሩት ዋናሥራ አስፈፃሚው አሁን የጉዳቱን መጠን መናገር እቸገራለሁ ብለዋል። እንዲያም ሆኖ ግን ሐሪ ቫን ኔር በኩባንያቸው ላይ የደረሰው ጉዳት ከባድ መሆኑን አልሸሸጉም።

በኢትዮጵያ ተቃውሞ ጥቃት ከደረሰባቸው መካከል ቀዳሚው የሆነው የሆላንዱ ኤስሜራልዳ ኩባንያ ሙሉ በመሉ መዘጋቱ ተሰምቷል። የኩባንያው ቃል-አቀባይ እንዳስታወቁት መቀመጫውን በአሜሪካን ያደረገው የኤስሜራልዳ እናት ኩባንያ ከጥቃቱ በኋላ በኢትዮጵያ የጀመረው የአበባ እርሻ ሥራም ይሁን በኔዘርላንድስ የሚገኘው ቢሮው እንዲዘጉ ወስኗል። በዚህም በኢትዮጵያ 600 በኔዘርላንድስ ደግሞ 14 የድርጅቱ ተቀጣሪዎች ሥራቸውን አጥተዋል።

የአፍሪቃ ጁስ ሥራ አስፈጻሚ ሐሪ ቫን ኔርም ቢሆኑ በኢትዮጵያ የሚሠሩት ሥራ ዕጣ ፈንታ አስጊ መሆኑን ይናገራሉ። ሥራ አስፈፃሚው የሠራተኞቻቸው እና የኩባንያው ንብረቶች ዋስትና ያሻቸዋል ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

«የእኛ መፃኢ ጊዜ የሰዎቻችን እና የኩባንያችን ሀብቶች ደህንነት መጠበቅ ላይ የተመሠረተ ነው። ይህ ለእኛ እና ለሁሉም ማለት ባልችል እንኳ ለአብዛኞቹ የአበባ እና የፍራፍሬ አምራቾች ማኅበር አባል ኩባንያዎች በጣም ጠቃሚ ጉዳይ ነው። እኛ በኢትዮጵያ የምንሠራውን ሥራ ለመቀጠል ቁርጠኞች ነን። ምክንያቱም እጅግ ልማታዊ ጠቀሜታዎች በሥራ ላይ በተሰማራንበት አካባቢ ለሚገኙ ዜጎች አቅርበናል። ፈሰስ ባደረግንው መዋዕለ-ንዋይ  የአካባቢውን ነዋሪዎች እና ገበሬዎች በማሳተፍ ከፈጠርነው እሴት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ እንሻለን። ለዚያም በኢትዮጵያ በጀመርንው ሥራ አሁንም ቁርጠኛ ነን።»

Äthiopien Gedeo Grundstücke Brand Protest
ምስል W/O Aynalem/R.Abeba

የኢትዮጵያው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በተቃውሞው ጥቃት የደረሰባቸውን የአካባቢዎች ጎብኝተው መንግሥታቸው የኩባንያዎቹን ደኅንነት እንደሚያስጠብቅ ቃል-ገብተዋል። ለንብረቶቻቸው የራሳቸውን ጥበቃ ማጠናከር የጀመሩ ኩባንያዎችም አልጠፉም። ዎል ስትሪት ጆርናል እንደዘገበው አፍሪፍሎራ የተሰኘ የአበባ እርሻ በ730 ሚሊዮን ዶላር ከሁለት አመት በፊት የገዛው ኬ.ኬ.አር. የተሰኘ የአሜሪካ የግል የመዋዕለ ንዋይ ኩባንያ የጸጥታ ጥበቃውን በግሉ አጠናክሯል።

በተቃውሞው በንብረቶቻቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው እና ሥጋት የተጫናቸው ግን ድንበር ተሻጋሪዎቹ ብቻ አይደሉም። አገር በቀል ኩባንያዎች እና የግል ባለሀብቶች ተመሳሳይ ዕጣ ገጥሟቸዋል። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች በጉዳዩ ላይ ለመገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ ለመስጠት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይከለክለናል ሲሉ ተናግረዋል። በጥቃቱ የደረሰውን ኪሳራ ለማጥናት ኮሚቴ ያቋቋመው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንን ለማነጋገር ያደረግንው ጥረትም አልተሳካም። በአጠቃላይ 130 አካባቢ የግል ተቋማት ጥቃት እንደተፈጸመባቸው የተሰማ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት በቀጥታ የካሳ ክፍያ ባይሆንም ድርጅቶቹን መልሶ በሁለት እግራቸው ለማቆም ጥረት መጀመሩን አስታውቋል። ሐሪ ቫን ኔር ኩባንያቸው አፍሪቃ ጁስ በተለያዩ ውይይቶች ላይ እየተሳተፈ መሆኑን ገልጠዋል።

«የተለያዩ ውይይቶች በተለያዩ መንገዶች እየተካሔዱ ነው። የአበባ እና ፍራፍሬ አምራቾች እና ላኪዎች ማኅበር ጉዳት የደረሰባቸውን እርሻዎች እና ኩባንያዎች አስተባብሮ ምን አይነት ድጋፍ ያሻቸዋል በሚለው ጉዳይ ላይ ለመምከር የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር። ለሁሉም ኩባንያዎች ዋናው እና ቀዳሚው ጉዳይ የሠራተኞቻቸውን እና ንብረታቸውን ደህንነት መጠበቅ ነው። አለበለዚያ ተመሳሳይ ነገር ወደ ፊት ሊከሰት የሚችል ከሆነ ስለ ካሳ እና ሥራ እንደገና ማውራት ትርጉም የለውም። የካሳ ጉዳይ እና ሌሎች ኩባንያዎቹ ሥራ ለመጀመር ስለሚያስፈልጓቸው ድጋፎች በተመለከተ አሁንም ውይይት እየተደረገ ነው።»

ዋና ሥራ አስፈፃሚው ዛሬም ድረስ የአፍሪቃ ጁስ እና ሌሎች ኩባንያዎች በተቃዋሚዎች ጥቃት እና ዘረፋ ለምን ኢላማ እንደሆኑ እንዳልገባቸው ይናገራሉ።

«ባለን መረጃ መሠረት ይህን ድርጊት ከፈጸሙት መካከል ማንም ኃላፊነት የወሰደ ወይም ምክንያቱን የገለጠ የለም። ለምን አፍሪቃ ጁስ ጥቃት ተፈጸመበት? ይህን ድርጊት የፈጸሙትን ግለሰቦች ምክንያት መናገር አልችልም። አንድ የምናውቀው ነገር ቢኖር በአካባቢያችን እና ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ ኩባንያዎችም ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል። የማውቀው ይህን ብቻ ነው። ጥቃቶቹ እርስ በርስ ግንኙነት እንዳላቸው እንኳ አላውቅም።»

Äthiopien Gedeo Grundstücke Brand Protest
ምስል W/O Aynalem/R.Abeba

ሐሪ ቫን ኔር ይህን ይበሉ እንጂ የኢትዮጵያን ፖለቲካ የሚታዘቡ ተንታኞች የተለየ አቋም አላቸው። የገበሬዎች ከማሳቸው መፈናቀል፤ ፍትኃዊ የሀብት እና የሥልጣን ክፍፍል እና ሌሎች በርካታ ጥያቄዎች በፖለቲከኞች እና አቀንቃኞች በተደጋጋሚ የሚነሱ ጥያቄዎች ነበሩ። በአገሪቱ የተስፋፋውን ተቃውሞ ለማብረድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ገቢራዊ ያደረገው መንግሥት መረጋጋት መመለሱን እና ኩባንያዎችም ሥራ መጀመራቸውን እየገለጠ ነው። በአማራ ክልል በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ጉዳት ገጥሟቸው የነበሩ 18 ነባር እና አዳዲስ የአትክልትና የአበባ አምራቾች ወደ ሥራ ተመልሰዋል ሲል ለገዢው ፓርቲ ቅርበት ያለው ራዲዮ ዘግቧል።

በኢትዮጵያ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ኤስሜራልዳ ሙሉ በሙሉ በአገሪቱ የነበረውን ሥራ ሲያቋርጥ አፍሪቃ ጁስ በበኩሉ ለመቀጠል ወስኗል። የውጭዎቹ ኩባንያዎች ከተቃውሞው በኋላ በኢትዮጵያ የጀመሩትን ሥራ አቋርጦ በመውጣት አሊያም በመቀጠል መካከል ሲዋልሉ ይታያሉ። የኦክላንድ ኢንስቲቲዩት ኃላፊ አኑራድሐ ሚታል ግን ኩባንያዎቹ ጥለው በመውጣት የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎቹን እየበደለ የውጭ ባለሀብቶችን ቀልብ መሳብ እንደማይችል ማሳየት አለባቸው የሚል እምነት አላቸው። የኢትዮጵያ መንግሥት ለፖለቲካዊ ተቃውሞው መፍትሔ ማበጀት ከተሳነው የልማት አውታሮችን በመደበኛ ጦር አስጠብቆ የመዝለቁም ጉዳይ አጠራጣሪ ነው።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ