1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዲያስፖራ አራማጆች ስለ ኢሕአዴግ ምርጫ ምን ይላሉ?

ረቡዕ፣ መጋቢት 19 2010

ለአቶ ግርማ "ዕድሉን ከተጠቀሙበት ዶ/ር አብይ አሕመድ የሽግግር ጊዜ መሪ" መሆን ይገባቸዋል። ለአቶ ሱራፌል ደግሞ ስኬታማ መሆን ካለባቸው "የኢትዮጵያ ሕዝብ የለውጥ ጥያቄ" መቀጠል ይኖርበታል። ለአቶ ግዛቸው ኢቢሳ ግን አዲሱ የኢሕአዴግ መሪ ፈፅሞ ችግር ፈቺ አይደሉም። ሶስቱም ለውጥን የሚያቀነቅኑ አራማጆች ናቸው።

https://p.dw.com/p/2v9Ss
Abiye Ahmed in Addis Ababa
ምስል Reuters/Stinger

አራማጆቹ ምን አሉ?

ለአቶ ግርማ ጉተማ "ዕድሉን ከተጠቀሙበት ዶ/ር አብይ አሕመድ የሽግግር ጊዜ መሪ" መሆን ይገባቸዋል። ለአቶ ሱራፌል አስፋው ደግሞ አዲሱ የኢሕአዴግ ሊቀ-መንበር ስኬታማ መሆን ካለባቸው "የኢትዮጵያ ሕዝብ የለውጥ ጥያቄ" መቀጠል ይኖርበታል። ለአቶ ግዛቸው ኢቢሳ ግን አዲሱ የኢሕአዴግ መሪ ፈፅሞ ችግር ፈቺ አይደሉም።ሶስቱም ከትውልድ አገራቸው ቢርቁም ለአገራቸው ለውጥን የሚያቀነቅኑ አራማጆች ናቸው። በተለያየ አቅጣጫ። መቀመጫውን በኖርዌይ ያደረገው ግርማ ጉተማ እንደሚለው ትናንት በኢትዮጵያ ዕኩለ ለሊት ሲቃረብ ከወደ አራት ኪሎ የተሰማው ዜና "ከተጠቀሙበት ጥሩ አጋጣሚ ነው"

ዶ/ር አብይ አሕመድ ውጤታማ ይሆኑ ዘንድ አራቱ ፓርቲዎች የመሠረቱት ግንባር ለሰላማዊ ለውጥ ፈቃድ ሊኖረው እንደሚገባ አቶ ሱራፌል አስፋው ይናገራሉ። ሊቀ-መንበሩም የሕዝብ ጫናና ጥያቄ ሊበረታባቸው ይገባል።

በኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች ተፈጽመዋል የተባሉ ግድያዎችን ማጣራት፣ ጥፋተኞችን መለየት እና ለሕግ ማቅረብ፤ የቀድሞው ሊባሉ ቀናት የቀራቸው ጠቅላይ ምኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ቃል የገቧቸው ሥራዎች ቢሆኑም አልተከወኑም። ግርማን የመሳሰሉን አራማጆች ይኸ የቤት ሥራ ወደ ዶ/ር አብይ አሕመድ መሻገሩን ያምናሉ። የዶ/ር አብይ የቤት ሥራዎች ግን ከዚያም በላይ ብዙ እና ውስብስብ ናቸው።

አቶ ግዛቸው ኢቢሳ አዲሱ የኢሕአዴግ ሊቀ-መንበር የተሰጣቸውን የቤት ሥራዎች ለመወጣት አቅም ያላቸው አይመስላቸውም። አቶ ግዛቸው እንደሚሉት የኢሕአዴግ ምክር ቤት ምርጫ ኢትዮጵያ የገባችበትን ውጥንቅጥ ከማረም ይልቅ ያባብሰዋል። ኢሕአዴግ ለሊቀ-መንበርነት ለውድድር ከቀረቡት ዶ/ር አብይ አሕመድ፣ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ እና ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል አሻግሮ ማየት ነበረበት ይላሉ አቶ ግዛቸው።

ወጣም ወረደ በኢሕአዴግ የአሠራር ሥርዓት መሰረት አቶ አብይ አሕመድ በኢትዮጵያ 27 አመታት ታሪክ ውስጥ 3ኛው ጠቅላይ ምኒስትር የመሆናቸው ጉዳይ የተረጋገጠ ነው። ወደ አራት ኪሎው ቤተ-መንግሥት ሲያመሩ ከተመረጡበት የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ በአጠቃላይም ከኢትዮጵያ የበረታ የማሻሻያ ጥያቄ ይከተላቸዋል። አቶ ሱራፌል እንደሚሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማንሳት የታሰሩ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች እና የሐይማኖት መሪዎችንም የመፍታት ድፍረቱ እና ነፃነቱ እንዳላቸው የሚታየው ግን ዘግይቶ ነው።

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ 

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ