1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዳርፉር ዘር በማጥፋት ወንጀለኛ ዓለምአቀፉ ፍርድቤት ቀረቡ

ሰኞ፣ ሰኔ 8 2012

በዳርፉር የዘር ማጥፋት ወንጀል ከተፈፀመ ከ 15 ዓመታት በኋላ ዛሬ በጦር ወንጀል የተጠረጠሩ  አንድ የ 70 ዓመት ሱዳናዊ ለመጀመርያ ጊዜ  በዴንሃግ ኔዘርላንድ በሚገኘዉ የዓለም አቀፍ የጦር ወንጀለኞች ተመልካች ፍርድ ቤት ቀረቡ። በምዕራባዊ ሱዳንም ከካርቱም መንግሥት ለማምለጥ የሞከሩ ሰዎች ጅምላ መቃብር መገኘቱ ተዘግቦአል።

https://p.dw.com/p/3dorJ
Belgien Den Haag | Internationaler Strafgerichtshof
ምስል picture-alliance/AP Photo/P. Dejong

በዳርፉር የዘር ማጥፋት ወንጀል ከተፈፀመ ከ 15 ዓመታት በኋላ ዛሬ በጦር ወንጀል የተጠረጠሩ  አንድ የ 70 ዓመት ሱዳናዊ ለመጀመርያ ጊዜ  በዴንሃግ ኔዘርላንድ በሚገኘዉ የዓለም አቀፍ የጦር ወንጀለኞች ተመልካች ፍርድ ቤት ቀረቡ። ዛሬ ዴንሃግ ላይ በዋለዉ ችሎት የቀድሞ የሱዳን ጦር ሰራዊት አዛዥና በጦር ወንጀልኝነት የተከሰሱት አሊ ሙሃመድ አሊ አብደራህማን በዳርፉር ከጎርጎረሳዉያኑ 2003 እስከ 2004 ዓም ድርስ በተፈፀመ ወንጀል በሰዉ ልጆች ላይ ከባድ የጦር ወንጀሎችን በፈፀም የዘር ማጥፋት አካሂደዋል ተብሎአል።  የ70 ዓመቱ ሱዳናዊ አሊ አብደራሃማን ክሱን ሃሰት ሲሉ አጣጥለዋል። ፍትህንም እንደሚያገኙ ተናግረዋል። የ70 ዓመቱ ሱዳናዊ በዳርፉሩ ጦርነት የጃንጀዊድ ሚሊሽያዎች መሪ ሳይሆኑ እንዳልቀረ  ነዉ የተነገረዉ። በተከሳሱ ላይ በዳርፉሩ ወንጀል ፤ በግድያ፤ሰዎችን በማሰቃየት፤በዘረፋ፤  ሴቶችን በመድፈር እና ነዋሪዎችን በማፈናቀል ጨምሮ ወደ 50 ክሶች ተመስሮቶባቸዋል። ከቀድሞዉ የካርቱሙ መንግሥት ጋር ግንኙነት እንደነበራቸዉ የሚነገረዉ የጃንጂዊድ ሚሊሽያዎች በሱዳንዋ ዳርፉር ወደ 300 ሺህ ሕዝብን አፈናቅለዋል። ዴንሃግ በሚገኘዉ የዓለም አቀፍ የጦር ወንጀለኞች ተመልካች ፍርድ ቤት የ70 ዓመቱ ሱዳናዊ ተከሳሽ የአሊ አብደራህማንን ችሎትን ለፊታችን ታሕሳስ ወር ለመመልከት ቀጠሮ ሰጥቶአል።       

በምዕራባዊ ሱዳን ከቀድሞ የካርቱም መንግሥት ለማምለጥ የሞከሩ ሳይሆኑ እንዳልቀረ የተነገረ ሰዎች ጅምላ መቃብር መገኘቱ ተነገረ።  አንድ የሱዳን አቃቤ ሕግ ዛሬ ይፋ እንዳደረገዉ የጅምላ መቃብሩ በጎርጎረሳዉያኑ 1998 ዓ.ም ከብሔራዊ ዉትድርና ካምፕ ለማምለጥ ሲሉ የተገደሉ ወጣቶች  ሳይሆን አይቀርም ብሎአል። የሱዳን አቃቤ ሕግ በአስራዎች የሚቆጠሩት ሰዎች የጅምላ ግድያና መቃምር  ጉዳዩ በመጣራት ላይም እንደሆን አስታዉቋል።  የቀድሞዉ የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር መንግሥታቸዉ ከአማፅያንን ሲዋጋ መንግስት  በሃገሪቱ የሚገኙትን ወጣቶች ኧል ኢፉአላኒ ወደተባለ የወታደራዊ ካንፕ በግዳጅ ይልክ እንደነበር ተገልፆአል።   

 

አዜብ ታደሰ 

ነጋሽ መሐመድ