1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዳርፉር ጉባኤና ሥጋቱ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 14 2000

ታዛቢዎች እንደሚሉት ክፍፍሉ ሰላም የሌላትትን ግዛት የስርዓተ አርበኞች፣ የሽፍቶች፣ የዘራፊዎች መናኻሪያ እያደረጋት ነዉ

https://p.dw.com/p/E0aI
የዳርፉር ስደተኞች
የዳርፉር ስደተኞችምስል AP

የሲርት-ሊቢያ የፊታችን ቅዳሜ የሚደረገዉ የሰላም ጉባኤ እንዲሳካ ከየአቅጣጫዉ የሚሰነዘረዉ አስተያየትና ምኞት በርግጥ ከበቂ በላይ ነዉ።ጉባኤተኞች ከሁነኛ ዉል እንዲደርሱ ከአፍሪቃ ሕብረት እስከ ፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት፤ እስከ ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን ያሉ ተቋማትና ሹማንንት ካንገትም ሆነ ካንጀት በጎዉን መመኘት-መናገራቸዉ አልቀረም።ጉባኤዉ ዕለታት ሲቀሩት ትናንት በዳርፉር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ዤን ኤሊያሰን እንዳሉት ግን ተስፋዉ ከተስፋ ማለፉ አጠራጣሪ ነዉ።

«የነበረኝን ድምፀት ወይም ስሜት ምናልባትም የነበረንን ተስፋ ያስቀየሩንን ምክንያቶችና ችግሮች ማብራራት ያለብኝ ይመስለኛል። ችግሮቹ ከኛ ቁጥጥር ዉጪ የሆኑ ሁኔታዎች ናቸዉ።የዉጪዉ አፍራሽ ሁኔታ በተለይ ካለፈዉ ወር ወዲሕ በጣም አፍራሽ እየሆነ ነዉ።»

አፍሪሹ ሁኔታ ላሁኑ ድርድር ብቻ ሳይሆን ላጠቃላዩ የሰላም ተስፋም ታላቅ ድቀት ነዉ-የሚሆን።ሲዊድናዊዉ ዲፕሎማት ያሉትን ለማለት ደግሞ በቂ ምክንያት አላቸዉ።በቅርቡ የአፍሪቃ ሕብረት ሠላም አስከባሪ ወታደሮችን ሕይወት ያጠፋዉ ጥቃት-ከምክንያቶቹ አንዱ ነዉ። በመንግሥትና በተለያዩ አማፂ ሐይላት መካካል የሚደረገዉ ዉጊያ መጋሙ የትልላልቆቹን መገናኛ ዘዴዎች ትኩረት አይሳብ እንጂ-ሁለተኛዉ።

የዛሬ አራት አመት ግድም ዳርፉር በጦርነት ስትታበጥ ከየመኖሪያ የቀያቸዉ እየተሰደዱ በየሠፈራ መንደሩ ከተጠለሉት አብዛኞቹ ሴቶችና ሕፃናት ናቸዉ።ዘንድሮ በየእድሜቸዉ ላይ አራት አመት ከመንፈቅ የጨመሩት የያኔዎቹ ሕፃናት ኤሊያሰን እንደሚሉት አስተዳደጋቸዉ ከፅንፈኝነት እምነት አስተሳሰብ ጋር ነዉ።ሌላ ፈተና።

«በየሠፈራ መንደሩ ሥጋትና ቁጣዉ እየናረ ነዉ።ሠፈራ ጣቢዎቹ ዉስጥ ግጭትና ሁከት አለ።እዚያ የተጠለሉት ሕፃናት አሁን ወደ አስራዎቹ እድሜ እየደረሱ ነዉ።በጣም ነዉጠኛ ሆነዉ እያደጉ ነዉ።የጦር መሳሪያ ደግሞ ይገባላቸዋል።»

በሲርቱ ጉባኤ ላይ ከተፋላሚ ሐይላት ሹማንንት ሌላ የሲቢል ማሕበረሰብ-ተጠሪዎች፤ የሐገር ሽማግሌዎች፣ የየሠፈራ መንደሩ ተወካዮች እንዲገኙ ታቅዶ ነበር።ተጠሪ ተወካዮቹ ወደ ሊቢያ መሔድ የሚችሉት ግን የሱዳን ማዕከላዊ መንግሥት የመዉጪያ ፍቃድ ከሰጣቸዉ ብቻ ነዉ።በጉባኤዉ ቢካፈሉ ሥር እየሰደደ የመጣዉን ችግር ለማቃለል ይረዳሉ የተባሉት እነዚሕ ተወካዮች የመንግሥትን ፍቃድ ማግታቸዉ እስከ ዛሬ አልታወቀም።

በሱዳን ማዕከላዊ መንግሥት መካካል የተፈጠረዉ ልዩነት ደግሞ የሲርቱን ጉባኤ ተስፋ ለማጨለም ተጨማሪ ምክንያት ነዉ።ከሁለት አመት በፊት በተደረፈረዉ የሰላም ዉል መሠረት ምክትል ፕሬዝዳትነቱን ጨምሮ ከሱዳን መንግሥት ሃያ-ስምንት ከመቶዉን ሥልጣን የተጋራዉ የቀድሞዉ የደቡብ ሱዳን አማፂ ቡድን (SPLA-M በሕጻሩ) የሚጋራዉን ሥልጣን ላልተወሰነ ጊዜ ትቶቷል።እንደገና ኤሊያሰን።

«በመንግሥቱ ዉስጥ ልዩነት ልዩነቱ እየሰፋ ነዉ።ኤስ ፒ ኤል ኤም በመንግሥቱ ዉስጥ የነበረዉን ተስትፎ ለማቆም ወስኗል።ይሕ የሱዳንን ፖለቲካዊ የትኩረት አቅጣጫ እስቀይሮታል።»

የዳርፉር አማፂያን አላማረባቸዉም።ለወትሮዉ ሰወስት የነበሩት ቡድናት ተሰነጣጥቀዉ ሃያ-ስድስት ደርሰዋል።አንዳድ ታዛቢዎች እንደሚሉት ክፍፍሉ ሰላም የሌላትትን ግዛት የስርዓተ አርበኞች፣ የሽፍቶች፣ የዘራፊዎች መናኻሪያ እያደረጋት ነዉ።በድሮ-ስማቸዉ ከሚንቀሳቀሱት መካካል የሱዳን የእኩልነትና የፍትሕ ንቅናቄ ከተሰኘዉ ቡድን የአንደኛዉ አንጃ መሪ በጉባኤዉ እንደማይከፈሉ አስታዉቀዋል።ምክንያት የሌለኛዉ አንጃ መሪ ሥለሚካፈሉ።ሌሎችም ስድስት ያሕል ቡድናት እያንገራገሩ ነዉ።