1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዳቦ ለዓለም ርዳታ በመቶ ሀገራት

ሰኞ፣ ነሐሴ 13 2005

በዓለማችን ሶስት ቢሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በሁለት የአሜሪካን ዶላር የየቀን ኑሯቸዉን ይገፋሉ። የጀርመኑ የወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን Brot für die Welt ማለትም ዳቦ ለዓለም የተሰኘዉ የልማት ተቋም እንዲህ ያሉ የድሃ ደሃ የሚባሉ ወገኖችን ኑሮ ለመደጎምም

https://p.dw.com/p/19RHH
ምስል Fotolia/Grecaud Paul
24112006 PZ TEFF.jpg
ምስል DW-TV

በተለያዩ ሀገራት ይንቀሳቀሳል። ዳቦ ለዓለም ባለፉት ዓመታት ድሃ በሚባሉ አንድ መቶ ሀገራት ዉስጥ ከሁለት ሺህ በላይ ፕሪዤዎችን ተግባር ሲደግፍ ቆይቷል። ዋና ትኩረቱም የአፍሪቃ ሀገራት ናቸዉ፤ የዶቼ ቬለዋ ዛቢነ ኪንካርትዝ ያጠናቀረችዉን ዘገባ ሸዋዬ ለገሠ አሰባስባዋለች።
የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ትምህርትና ሥልጠና፣ እንዲሁም ጤና ዳቦ ለዓለም የተሰኘዉ የጀርመኑ ግብረ ሠናይ ድርጅት የሚያተኩርባቸዉ ዋነኛ ጉዳዮች ናቸዉ። ይህንን ግን ድርጅቱ በሚንቀሳቀስባቸዉ ድሃ ሀገራት ለምሳሌ እንደምስራቃዊ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ በመሳሰሉት ማረጋገጥ ቀላል የሚባል ተግባር አይሆንም። ክላዉዲያ ቫርኒንግ የዳቦ ለዓለም ዓለም ዓቀፍ መርሃ ግብር እና የሀገር ዉስጥ ጉዳዮች ደህንነት ተጠሪ ስፍራዉ ጎብኝተዉ ገና መመለሳቸዉ ነዉ።

በተጠቀሰዉ ስፍራ ስላለዉ ጦርነትና ብጥብጥ፣ ስደትና መፈናቀል፣ ስለሴቶች እና ታዳጊ ልጃገረዶች መደፈር፣ እንዲሁም ለዉትድርና ስለሚመለመሉና ስለሚገደሉ ሕጻናት ዝርዝር ዘገባ አቅርበዋል። በተጓዳኝም እዚያ ስለሚከናወነዉ የእርዳታ ተግባርና በምስራቅ ኮንጎ ስለሚታይ ተስፋም ይናገራሉ፤
«እዚያ የምንሠራዉ ይህን ቀዉስ ለመታደግ፤ በተልይም ትምህርትና ጤናን ለማዳረስ አልመዉ ከሚንቀሳቀሱ ከበርካታ የፕሮቴስታን አብያተክርስቲያናት ጋ ነዉ። አብያተክርስቲያናቱ ምስራቅ ኮንጎ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ሁለት ሶስተኛዉን ይደግፋሉ። ጎማ በሚገኘዉ የባብቲስት ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ቤት አንድ መቶ ስልሳ ተማሪዎች ይገኛሉ። እዚያ የሚማሩት ተማሪዎች ልጆች አይደሉም፤ በልጅ ወታደርነት ለመልምለዉ ጫካ ዉስጥ ሲዋጉ የኖሩ ናቸዉ።»
Brot für die Welt ማለትም ዳቦ ለዓለም የተሰኘዉ ግብረ ሠናይ ድርጅት 6000 ተማሪዎችን ለሚያስተናግዱ ሁለት ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ እና ለተማሪዎች የኪስ ገንዘብ በመስጠት ፕሮዤዉን ይደግፋል። ኮንጎ ሃኪሞች፣ መምህራን፣ መሃንዲሲች እና ገበሬዎች እጅግ ያስፈልጓታል። ክላዉዲያ ቫርኒንግ፤
«ይህ እንግዲህ እኛ እንዴት እንደምንሠራ ከሚያሳይ ዓይነተኛ ምሳሌ አንዱ ነዉ። ወደአንድ መቶ በሚጠጉ ሀገራት እኛ ራሳችን ሳንሆን የራሳቸዉን መርሃግብር በኃላፊነት እየመሩ ያሉትን ወቅታዊ ችግሮችን ለማስወገድ ለሚጥሩ አጋሮቻችን ድጋፍ እናቀርባለን።»

Ausbildung in der DR Kongo
ምስል Thomas Einberger/Brot für die Welt


ህንድና ብራዚል ዉስጥ ካሉት መርሀግብሮች በተጓዳኝ ባለፈዉ ዓመት በርከት ያለ ገንዘብ ከዳቦ ለዓለም ድርጅት ያገኘዉ የኮንጎዉ ፕሮዤ ነዉ። የኬንያና የኢትዮጵያዉ ደግሞ ከዚያ ይከተላል። ብራዚል ዉስጥ ወደሁለት ሺ የሚጠጉ ፕሮዤዎችን ለመደገፍ ባለፈዉ የጎርጎሪዮሳዊ 2012ዓ,ም ብቻ ድርጅቱ ለብራዚል 234,6 ቢሊዮን ዩሮ አዉጥቷል። የወንጌላዉያኑ የልማት ድርጅቶች ከተጣመሩ ከአንድ ዓመት ወዲህም ወንጌላዉያኑ የሚከናዉኑት የልማት ተግባራት በዳቦ ለዓለም እንቅስቃሴ ዉስጥ ተካቷል። የፋይናንስ ጉዳይ ተጠሪ ቲልማን ሄንከ የጥምረቱን ጥቅም ይገልጻሉ፤
«በዚህ አማካኝነትም ይበልጥ የተሻለ እና ለተመረጡ ፕሮዤዎች መርዳት እንችላለን። የገንዘብ አቅማችን በሶስት ዋልታዎች ማለትም፤ ከምጽዋትና ከሚሰባሰበዉ ርዳታ በተጓዳኝ የቤተ ክርስቲያን ግብር ወይም አስራት፤ ላይ የተደገፈ ነዉ። ባለፈዉ ዓመት ከየአብያተክርስቲያናቱ የልማት ተልዕኮዎች 51 ሚሊዮን ዩሮ አግኝተናል። በዚያ ላይ በዚሁ ጊዜ ከፌደራል ጀርመን የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ሚኒስቴር 122,8 ሚሊዮን ዩሮ ተጨምሯል።»

Logo - Brot für die Welt


በጎርጎሪዮሳዊዉ 2012 ዓ,ም ከአብያተክርስቲያናት ምጽዋትና ርዳታ የመጣዉ ካለፉት ዓመታት ጋ ሲነፃጸር መቀነሱ ነዉ የተገለጸዉ፤ 55,2 ሚሊዮን ዩሮ። በ2011 56,2 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን ከዚያ አንድ ዓመት በፊት ደግሞ 62,1 ሚሊዮን ዮሮ መገኘቱ ተመልክቷል። ሄንከ እንዲህም ቢሆን ከለጋሾች የተገኘዉ ድጋፍ አበረታች ነዉ ይላሉ፤


«የልገሳዉን ሁኔታ እኛ ማስተዋል ይገባል፤ መገናኛ ብዙሃኑ ስለተለያዩ አደጋዎች በሚያቀርቡት ዘገባ የሚመራ ነዉ። ከመገናኛ ብዙሃኑ አንዱ ስለአንድ ትልቅ አደጋ በጣም ጠንከር ያለ ዘገባ ቢያቀርም ለምሳሌ ማለቴ ነዉ ሁላችንም ያ እንዲሆን አንመኝም፤ Brot für die Welt ጠቀም ያለ የእርዳታ ገንዘብ ያሰባስብ ነበር። እንዲህ ያለ ሁኔታ በማይኖርባቸዉ ዓመታትም ሆነ በዚህ ዓመት አነስተኛ የሚሆነዉ ለዚህ ነዉ።»
በጎርጎሪዮሳዊዉ 2010ዓ,ም ጃፓን ላይ የሱናሚ አደጋ ሲደርስ በጣም ብዙ ገንዘብ በእርዳታ ገብቷል። ባለፈዉ የጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ደግሞ የተገኘዉ 55ሚሊዮን ዩሮ ብቻ ነዉ፤ ይህም እሳቸዉ ያሉትን ይገልጻል።

ሳቢነ ኪንካርትዝ/ሸዋዬ ለገሰ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ