1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ድርድር

Eshete Bekele ቅዳሜ፣ መስከረም 7 2009

የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የምርጫ የሚከናወንበትን የጊዜ ሰሌዳ ለመወሰን ገዢው ፓርቲ ከተቃዋሚዎች ጋር የጀመረው ድርድር እንደታቀደው ስኬታማ አልሆነም። የተቃዋሚዎች ተወካዮች ድርድሩን ረግጠው ቢወጡም መንግስት ግን አሁንም ይቀጥላል እያለ ነው።

https://p.dw.com/p/1K4Cx
Kongo Kinshasa Nationaler Dialog Maman Sambo Sidikou
ምስል Getty Images/AFP/J. D. Kannah

[No title]

የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ባለስልጣናት ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላ በሕገ-መንግስቱ ከተፈቀደላቸው ጊዜ በስልጣን ለማቆየት በተቃዋሚዎቻቸው ላይ ሥልታዊ አፈናና ማዋከብ ይፈፅማሉ እየተባሉ ይተቻሉ። በዕለተ አርብ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው ዘገባ የፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላን በስልጣን የመቆየት እቅድ የተቃወሙ ተቺዎችን ለማፈን የመንግስት ተቋማትን እንደ መሳሪያ እየተጠቀሙ ነው ሲል ወቅሷል። በአምነስቲ ዘገባ መሰረት የሶስት አካባቢያዊ አስተዳደሮች ባለስልጣናት በተቃውሞ ሰልፎች ላይ ገደብ ጥለዋል፤የተቃውሞ ሰልፎች ህጋዊ እውቅና ተነፍገዋል። ይሁንና የገዢው ጥምር ፓርቲ ደጋፊዎች በፖሊስ እና አካባቢያዊ አስተዳደሮች አመቻችተውላቸው የአደባባይ ሰልፎችን አካሂደዋል።
የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላ ከ15 ዓመታት የስልጣን ዘመን በኋላ በጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ.ም. መገባደጃ ይለቃሉ ይለቃሉ ተብሎ ይጠበቃል። ፕሬዝዳንቱ እስካሁን የሥልጣን ዘመናቸው ሲጠናቀቅ መንበራቸውን ስለማስረከባቸው አሊያም ለተጨማሪ ዓመታት በስልጣን ለመቆየት በድጋሚ ለመወዳደራቸው በግልፅ ያሳወቁት ነገር የለም። አገሪቱ በመጪው ህዳር ከምታካሒደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በፊት የጀመረችው የብሔራዊ እርቅ ጉባኤ እንደታቀደው አልሰመረም። ባለፈው ሳምንት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ድርድሩን ረግጠው ወጥተዋል። የተቃዋሚዎቹ ውሳኔ ድርድሩ ላለመሳካቱ ምልክት ሳይሆን አይቀርም እየተባለ ነው። የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መንግስት ቃል-አቀባይ ራማዛኒ ሻዳሪ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ረግጠው በመውጣት እንደ መደራደሪያ ሊጠቀሙበት ከጅለዋል ሲሉ ይወነጅላሉ።
«ይህ ድርድሩ አብቅቶለታል ወይም ተቃዋሚዎች ራሳቸውን አግልለዋል ማለት አይደለም። ይህ የመደራደሪያ ሥልት ነው። በጉዳዩ ላይ እንዲያሰላስሉበት ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው ይገባናል። ምናልባት በሌሎች ቦታዎች አገሮች እንደሆነው ወደ ድርድር ጠረጴዛው መመለስ አለብን ብለው ሊያምኑ ይችላሉ።»
Kongo Oppositionspolitiker Moise Katumbi
በሥደት ላይ የሚገኙት ሞይሴ ካቱምቢምስል Getty Images/AFP/F. Scoppa
ከመስከረም ወር ጀምሮ መንግስት፤የተቃዋሚዎች ተወካዮች እና የሲቪክ ማህበረሰብ ተወካዮች የህዳሩ ፕሬዝዳንታዊ እና አካባቢያዊ ምርጫዎች በሚካሔዱበት የጊዜ ሰሌዳ ላይ ሲመክሩ ነበር። ተቃዋሚዎች ሁለቱ ምርጫዎች በተከታታይ መካሔድ አለባቸው የሚል ቁርጥ አቋም ይዘዋል። ተቃዋሚዎች ፕሬዝዳንታዊ ምርጫው በሕገ-መንግስቱ መሰረት የጆሴፍ ካቢላ የስልጣን ዘመን ከማብቃቱ ዘጠና ቀናት በፊት ሊካሔድ ይገባል ብለው ይከራከራሉ። በእነሱ እምነት መሰረት አካባቢያዊ ምርጫዎች ፕሬዝዳንታዊውን ተከትለው ሊካሔዱ ይገባል።
ይሁንና ያለፉት ሳምንታት ለተቃዋሚዎቹ መልካም አልነበሩም። ሞይሴ ካቱምቢ፤ ቪታል ካሜርሔ እና ኤትየን ሺሴኬዲ የጋራ ጥምረት የመሰረቱት በቅርቡ ነበር።
የሕዝብ ኃይል
ከተቃዋሚዎቹ መካከል አንዱ የሆኑት ካቱምቢ ጠንካራ የሕዝብ ድጋፍ ምርጫውን ለማሸነፍ ትልቁ መሳሪያቸው እንደሆነ በቅርቡ ከዶይቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ተናግረዋል።
«ጠንካራው ጦራችን ሕዝቡ ነው። ምርጫን ለማሸነፍ የተባበረ ተቃዋሚ ያስፈልገናል። በጋቦን በቅርቡ የተፈጠረው ሁኔታ ልናስወግደው የሚገባ ክስተት ነው።»
በሥደት ላይ የሚገኙት ካቱምቢ በድርድሩ ላይ ተዓቅቦ አድርገዋል። መንግስት ድርድሩን በስልጣን ለመቆየት እንደ መሳሪያ እየተጠቀመበት ነው ሲሉም ይወነጅላሉ። ይሁንና በውዴታ አገራቸውን ጥለው ወደ ደቡብ አፍሪቃ መሰደዳቸው ካቱምቢ በአገራቸው በተለይም በተፈጥሮ ኃብት በበለፀገው የካታንጋ ግዛት ያላቸውን ተቀባይነት እና ተፅዕኖ ሳይቀንሰው አልቀረም።በርካታ ተከታዮች ያሏቸው ሌላው የተቃውሞ ፖለቲካ መሪ የ83 ዓመቱ ኤትየን ሺሴኬዲ አንድነት ለዴሞክራሲ እና ማሕበራዊ ለውጥ ፓርቲ (UDPS) መሪ ናቸው። ሞቡቱ ሴሴኮ የቀድሞዋን ዛየር የዛሬዋን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከ1965-1997 ካስተዳደሩበት ጊዜ ጀምሮ የተቃውሞ ፖለቲካ መሪ የነበሩት ኤትየን ሺሴኬዲ በቅርቡ ከቤልጅየም ወደ አገራቸው ሲመለሱ በዋና ከተማዋ ኪንሻሳ በርካታ ህዝብ ወደ አደባባይ ወጥቶ ተቀብሏቸዋል።
ይሁንና በድርድሩ የተቃዋሚዎች ሁነኛው ተወካይ ለኮንጎ አንድነት(UNC) የተባለው ፓርቲ ተወካይ ቪታል ካሜርሔ ናቸው። ቪታል ካሜርሔ የተቃዋሚዎች ቃል-አቀባይ ጭምር ናቸው። ካሜርሔ ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ለድርድሩ መጓተት ገዢውን ጥምር ፓርቲ ተጠያቂ አድርገዋል።
Kongo Präsident Joseph Kabila
ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላምስል picture-alliance/AP Photo/J. Bompengo
«የፕሬዝዳንታዊ ሃያላን ጥምረት ጓደኞቻችን የሚቀጥለውን እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ሊረዱ ይገባል። ይህን ቀውስ የፈጠሩት እነሱ ናቸው። ይበልጥ ሊያባብሱትም ይፈልጋሉ። ለዚህ ቀውስ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ሊረዱ ይገባል።»
ማዘግየትን እንደ ሥልት
ገዢው የፕሬዝዳንታዊ ሃያላን ጥምረት ፕሬዝዳንታዊው ምርጫ ከአካባቢያዊው በኋላ ለማካሔድ ቆርጠው ተነስተዋል። ተቃዋሚዎች ይህ በ ታኅሣሥ ወር የሚጠናቀቀውን የፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላ ሥልጣን ለማራዘም የሚጠቀሙበት ሥልት ነው ሲሉ ይከራከራሉ።
እስካሁን ካለየለት የምርጫ ሰሌዳ በተጨማሪ የመዘገባቸውን ድምፅ ሰጪዎች ዝርዝር ማሻሻል የሚጠበቅበት የምርጫ ኮሚሽን ከፊቱ ፈተና ተደቅኖበታል። እንደ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ባለ ሰፊ እና ምቹ መንገዶች በሌሉበት አገር የመራጮች ምዝገባን ለማሻሻል ቀላል አይደለም። «እስካሁን የመራጮች ምዝገባ የተጀመረው በሰሜናዊ የኡባንጊ ግዛት ብቻ ነው። አሁን እኛ የምርጫ ኮሚሽኑን የቆጠራ ውጤት በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን። ከዚያ የሌሎች ግዛቶች ሁኔታን ለመፈተሽ የሚያስችል መረጃ እናገኛለን።» ሲሉ የምርጫ ተቆጣጣሪ የሆኑት አንድሬ ካዮምቤ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ሁሉንም ግዛቶች ለማዳረስ ግን እስከ አስራ ስድስት ወራት ይፈጃል። ይህ ማለት ደግሞ ፕሬዝዳንት ካቢላ በህገ-መንግስቱ እና የምርጫ ውጤት ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ በስልጣን ይቆያሉ ማለት ነው። ባለፈው ግንቦት ወር የአገሪቱ ሕገ-መንግስታዊ ፍርድ ቤት የአገሪቱ መንግስት በታቀደው ጊዜ ምርጫ ለማካሔድ ከተሳነው ጆሴፍ ካቢላ ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ በስልጣን እንዲቆዩ ውሳኔ አስተላልፏል። ፍርድ ቤቱ ይህን ውሳኔ ያስተላለፈው የስልጣን ቅብብሎሹን ለማስጠበቅ እና በከፍተኛው አመራር ዘንድ የሚፈጠር ክፍተትን ለማስወገድ መሆኑን ገልጧል።
ዩኒስ ዋንጂሩ/እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ