1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የድሬደዋ ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 9 2006

ለዘመናት ከድህነት ወለል በታች ተፈርጃ መቆየቷ በሚነገርላት ኢትዮጵያ ምንም እንኩዋን መንግስት እና ኣንዳንድ ዓለም ዓቀፍ ተቐማትም ቢሆኑ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ፈጣን እድገት እያስመዘገበች መሆኗ ቢሰማም የድህነቱ ጥልቀት ግን እንዲህ በቀላሉ የሚቀረፍ ኣለመሆኑን ሁሉም ወገኖች ይስማሙበታል።

https://p.dw.com/p/1AcAB
Zugmodell in Dire Dawa Äthiopien
ምስል DW

ከዚህም የተነሳ አዲስ አበባን ጨምሮ በኢትዮጵያ ከተሞች የሚታየው ስራ ኣጥነት ከጠቅላላው ኗሪ ከ20 በመቶ በላይ እንደሆነ ይገመታል። ይህንኑ ለማቃለል በእርግጥ በተለያዩ ከተሞች በግልም ሆነ በቡድን እያደራጁ በተለይም ወጣት ስራ ኣጦችን ስራ እንዲፈጥሩ ለማስቻል ኣንዳንድ እንቅስቃሴዎች እየተካሄዱ መሆናቸው ይስተዋላል። በዚህ ረገድ ከሚጠቀሱት ከተሞች ኣንዷ የምስራቅ ኢትዮጵያዋ ድሬደዋ ስትሆን በዛሬው የኢኮኖሚ ዝግጅታችንም ከድሬደዋ ኣስተዳደር ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይሶች ልማት ኤጀንሲ እና በስሩ ከተደራጁት ማህበራት ጋር እናስተዋውቃቿለን፣

የድሬደዋ ኣስተዳደር አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይሶች ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ወጋየሁ ጋሻው እንዳስረዱት የኤጀንሲው ተግባር ስራ ፈላጊዎችን መመዝገ፣ ማሰልጠን እና ማደራጀት እንዲሁም ብድር ማመቻቸት እና የምክር አገልግሎት መስጠትንም ያጠቃልላል።

Polizisten in Dire Dawa Äthiopien
ምስል DW

በዚህ መልክ ከተደራጁት ማህበራት ኣንዱ የጥረት ለኣንድነት ማህበር ሲሆን የማህበሩ ሊቀመንበር ወጣት ግሩም የሺጥላ እንደሚለው ኣጥጋቢ ሊባል ባይችልም አስር ያህል የማህeበሩ አባላት ኣሁን እራሳቸውን ለማስተዳደር ችለዋል።

የኤጀንሲው ኃላፊ አቶ ወጋየሁ ጋሻው እንደሚሉት ባሳለፍነው የበጀት ዓመት ብቻ በድሬደዋ ከተማ 18 000 ስራ ፈላጊዎችን ኣሰልጥኖ እና ኣደራጅቶ ስራ ለማስያዝ ተችሏል። በያዝነው ዓመትም ከማይክሮ ፋይናንስ የ30 ሚሊየን ብር በጀት ተይዞለታል ተብሏል።

ጋሻሞ በመባል የሚታወቀው ማህበርም በኤጀንሲው ኣማካኝነት ከተደራጁት ማህበራት መካከል ኣንዱ ሲሆን ሊቀመንበሩ ወጣት ኣንዱዓለም ክፍሌ እንደሚለው የብረታብረት ዕቃዎችን እያመራቱ ኣትራፊ ለመሆን ችሏል። ከራሳቸው ኣልፈው ተጨማሪ ሰራተኞችንም እየቀጠሩ እንደሚያሰሩ ሊቀመንበሩ ተናግሯል።

የድሬደዋ ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይሶች ልማት ኤጀንሲ ስራ ፈላጊዎችን በኮንስትራክሺን፣ በማኒዩፋክቸሪንግ፣ በከተማ ግብርና፣ በንግድ እና በአገልግሎት ዘርፎች ኣሰልጥኖ እንደሚያደራጅ የገለጹት ኃላፊው አቶ ወጋየሁ የማምረቻ ቦታ ኣቅርቦትን በተመለከተ ችግሮች እንዳሉባቸው ግን ኣልሸሸጉም።

በኤጀንሲው መረጃዎች መሰረት በድሬደዋ ከተማ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ 1611 ምሩቃን በስራ ፈላጊነት የተመዘገቡ ሲሆን ቀደም ሲል የተመዘገቡትን ጨምሮ 13 000 ያህል ስራ ፈላጊዎች ተመዝግበው የስራ ዕድል በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል። ይህ ቁጥር ግን በትምህርታቸው ያልገፉትን እና ያልተመዘገቡትን ኣለመጨመሩ ሲታይ የስራ ኣጡ ቁጥር በከተማይቱ ከዚያ በላይ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል።

Polizisten in Dire Dawa Äthiopien
ምስል DW

ከአዲስ ኣበባ በስተ ምስራቅ 525 ኪ ሜ ላይ የምትገኘው ድሬደዋ የተቆረቆረችው የኢትዮ ጂቡቲ ባቡር ሀዲድ ዝርጋታን ተከትላ እአኣ በ1902 ሲሆን በኣሁኑ ጊዜ ከ400 000 በላይ ህዝብም ኣላት።

ጃፈር ዓሊ

ሸዋዬ ለገሰ