1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የድሬዳዋ ባለሥልጣናት መታሰር

ረቡዕ፣ ነሐሴ 2 2010

በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል የክልሉን የፀጥታ ሃላፊ ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይገኙበታል ሲሉ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች እየተናገሩ ነው። የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ግን የተያዙ ተጠርጣሪዎች መኖራቸውን ባይክዱም ማንነታቸው እና ብዛታቸው ግን የሚካሄድባቸው ምርመራ ከተጠናቀቀ በኋላ ይፋ ይደረጋል ብለዋል።

https://p.dw.com/p/32rAk
Äthiopien Dire Dawa City
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

የድሬዳዋ ባለሥልጣናት መታሰር

ድሬዳዋው ዉስጥ የሰዉ ሕይወት ያጠፋዉን ግጭት እና ጠብ ቀስቅሰዋል በሚል ጥርጣሬ ከተያዙ ሰዎች መካከል የከተማይቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት  እንደሚገኙበት ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች አስታወቁ። ከተያዙት መካከል የክልሉ የፀጥታ ሃላፊ እና የቀድሞ ባለሥልጣናት ይገኙበታል ነው የሚባለው። የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ግን በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች መኖራቸውን ባይክዱም ማንነታቸው እና ብዛታቸው ግን የሚካሄድባቸው ምርመራ ከተጠናቀቀ በኋላ ይፋ ይደረጋል ብለዋል።
በድሬዳዋ አስተዳደር 09 ቀበሌ ባለፈው እሁድ በደረሰው ግጭት እና ሑከት በትንሽ ግምት 10 ሰዉ መገደሉ ተዘግቧል።ሁከት እና ረብሻዉን ቀስቅሰዋል ወይም አባብሰዋል ተብለዉ የተጠረጠሩ ሰዎች  በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ከሚሽን ሰሞኑን አስታውቋል። ፖሊስ የተያዙትን ሰዎች ማንነት እና ቁጥራቸውን ግን አልገለጸም። ይሁን እና  በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል የክልሉን የፀጥታ ሃላፊ ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይገኙበታል ሲሉ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች እየተናገሩ ነው። ሻለቃ አሊ ሰመሪ ሲገዱ የተቃዋሚው የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር የኦብነግ እና የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ጥምረት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ናቸዉ። ሻለቃዉ አለኝ ባሉት መረጃ መሠረት ከቀድሞ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ከአቶ አብዲ መሀመድ ዑመር ጋር ቅርበት ያላቸው የድሬዳዋ አስተዳደር ሃላፊዎች እንደታሰሩ ተናግረዋል። እንደ ሻለቃ አሊ ከመካከላቸው የክልሉ የፀጥታ ሃላፊ ይገኙበታል። 
የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ዋና ሳጂን ባንተ ዓለም ግርማ ግጭት በመቀስቀስ የተጠረጠሩ ሰዎች መታሰራቸውን ተናግረዋል። ሆኖም ማንነታቸውን እና ቁጥራቸውን ከመግለጽ ግን ተቆጥበዋል።
በሻለቃ አሊ እምነት የድሬዳዋውም ሆነ የሶማሌ ክልሉ ሁከት እና ረብሻ መነሻ ምክንያት አንድ ነው። ችግሩም የተያያዘ ነው በርሳቸው አባባል።
ዋና ሳጂን ባንተ ዓለም ግን የሶማሌ ክልሉ ግጭት እና የድሬዳዋ ሁከት ግንኙነት አለው የለውም የሚለው ከምርመራው በኋላ ይፋ የሚደረግ ይሆናል ብለዋል። 
ሳጂን ባንተ ዓለም አያይዘውም ድሬዳዋን ለማረጋጋት ፖሊስ እና ህብረተሰቡ በጋራ እይተንቀሳቀሱ መሆኑን ተናግረዋል። ወጣቶች በተለይ ችግር ወደ ተፈጠረባቸው አካባቢዎች በረብሻ እና ሁከት ጥቅም ላይ የሚውሉ ቁሳቁሶች እንዳይገቡ እየተቆጣጠሩ መሆንን እና በረብሻው ምክንያት የተዘጉ መደብሮች እየተከፈቱ መሆኑን ለዶቼቬለ ተናግረዋል።  

Äthiopien Dire Dawa City
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ