1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የድሬዳዋ የመጠጥ ውኃ ችግር ሊቀረፍ ነው ተባለ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 24 2011

ድሬዳዋ ከነዋሪዎቿ ገሚሱ በሚባል ደረጃ በመጠጥ ውኃ እጥረት ስትሰቃይ የከረመች ከተማ ናት። ከተማዪቱ አሁን ምናልባት መቶ በመቶ ባይኾን እንኳን 90 በመቶ የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ልታገኝ ነው ተብሏል።

https://p.dw.com/p/3HprU
Äthiopien Projekt Trinkwasserversorgung in Dire Dawa
ምስል DW/M. Teklu

ድሬዳዋ ከውኃ ጥም ልትላቀቅ ይኾን?

ድሬዳዋ ከነዋሪዎቿ ገሚሱ በሚባል ደረጃ በመጠጥ ውኃ እጥረት ስትሰቃይ የከረመች ከተማ ናት። ከተማዪቱ አሁን ምናልባት መቶ በመቶ ባይኾን እንኳን 90 በመቶ የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ልታገኝ ነው ተብሏል። ለዚያ ደግሞ የዛሬ አራት ዓመት ጥናት እና ንድፉ ተጀምሮ፤ ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦለት ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ግንባታ የገባው የድሬዳዋ ከተማ የመጠጥ ውኃና ንጽህና ፕሮጀክት ዛሬ ተመርቋል። ፕሮጀክቱ ከዓለም ባንክ በተገኘ 18 ሚሊዮን ዶላር ብድር እና 4.2 ሚሊዮን ዶላር ርዳታ እንዲሁም ከድሬዳዋ አስተዳደር በተመደበ ከ375 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦለት የተሠራ መኾኑ ተገልጧል። ነዋሪዎች አሁንም የንጹህ መጠጥ ውኃ ችግራችን አልተቀረፈም እያሉ ነው። 

ላለፉት ስድስት አመታት ሲከናወን የቆየው የድሬደዋ ውሀና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ተጠናቆ ዛሬ ተመርቋል ። የውሀ ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ  ኃይል ሚንስትሩን ጨምሮ የፌደራልና አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በምረቃው ላይ ተገኝተዋል። የውሀ መስኖና ኤሌክትሪክ ሀይል ሚንስቴር ሚንስትር ዶ/ር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ መንግስት በከተሞች ያለውን የውሀና ሳኒቴሽን ችግሮች ለመፍታት በአለም ባንክ የበጀት ድጋፍና ብድር እንዲሁም በመንግስት አስተዋፅኦ ከሚሰራቸው ፕሮጀክቶች ዛሬ በድሬደዋ የተመረቀው አንዱ መሆኑን ተናግረዋል። 

ፕሮጀክቱ ከአለም ባንክ በተገኘ አስራ ስምንት ሚሊየን ዶላር ብድር አራት ሚሊየን ዶላር ያክል ድጋፍና የድሬደዋ መስተዳድር በመደበው ሶስት መቶ ሰባ ሚልዮን ብር በጥቅሉ ሰላሳ አምስት ሚልዮን ዶላር ወይም ዘጠኝ መቶ ሚሊየን ብር ያክል ወጭ የወጣበት  መሆኑን ጠቁመዋል።በድሬደዋ ቀድሞ የነበረውን የአርባ አምስት በመቶ የውሀ ስርጭት ሽፋን ዘጠና በመቶ የሚያደርሰው የውሀና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃት ነዋሪው ሲያነሳቸው ለነበሩ የመልካም አስተዳደር እና የፍትሀዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ ነው ያሉት ደግሞ የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ መሀዲ ጊሬ ናቸው።

Äthiopien Projekt Trinkwasserversorgung in Dire Dawa
ምስል DW/M. Teklu

ይሁን እንጂ በከተማው ከሚገኙ ዘጠኝ የቀበሌ መስተዳድሮች የስምንቱን ችግር ሙሉ በሙሉ ይቅር ድል የተባለው ይህ ፕሮጀክት ዛሬም ችግራቸውን አልመቅረፉን DW ያንጋገራቸው አስተያየት ሰጪ ተናግርዋል። በከተማው በተለምዶ ገንደቦዬ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አስተያየት ሰጪ ዛሬም ቤት ገብቼ ቧንቧ ከፍቼ የለም ብለዋል ።የአካባቢውን ችግር በሚመለከት ከሃያ ቀናት በፊት የውሀ መስመሮችን በአዲስ የመተካት ስራ እየተሰራ ነው ይህም በአስራ አምስት ቀናት ያልቃል ቢባልም ዛሬ በምረቃው እለት እንኳ ይሄ ችግር አለመፈታቱን አስረድተዋል።

የውሀና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቱ ከተገቢው ጊዜ የተጓተተ በመሆኑም ቅሬታዎች ሲቀርቡበት ቆይቷል ። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን በፕሮጀክቱ መጓተት ለተፈጠረው ችግር የአስተዳደሩ ውሀና ፍሳሽ አገልግሎት ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ መሀመድ ነዋሪውን በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል። በድሬደዋ ዛሬ ለምረቃ የበቃው የውሀና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት አብዛኛውን የከተማው ችግር ይቀርፋል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል።

መሳይ ተክሉ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ