1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዶሃ ድርድር ሕያው ውይስ ሙት?

ረቡዕ፣ የካቲት 14 2004

የዓለም ንግድን ደምቦች በማለዘብ ፍትሃዊ ለማድረግ ለረጅም ጊዜያት የታለመው ሕልም እስከዛሬ ድረስ ጨርሶ ዕውን ሊሆን አልቻለም።

https://p.dw.com/p/146jY
ምስል dapd

የዓለም ንግድን ደምቦች በማለዘብ ፍትሃዊ ለማድረግ ለረጅም ጊዜያት የታለመው ሕልም እስከዛሬ ድረስ ጨርሶ ዕውን ሊሆን አልቻለም። በጅምሩ ብዙ ተሥፋ ተጥሎበት የነበረው የዓለም ንግድ ድርጅት የዶሃ ድርድር ዙር ይሄው ሊሞት ሲያጣጥር ከቆየ በኋላ ዛሬም በድን እንደሆነ ነው። ባለፉት ዓመታት አንድም ነገር ወደፊት ፈቀቅ ሲል አልታየም። በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታትና ታዳጊ ሃገራት ከአሥር ዓመታት ወዲህ በዓለም ንግድ ላይ ወደፊት በሚሰፍኑ ደምቦች ጉዳይ ሲወዛገቡ ነው የኖሩት።

ውዝግቡ ከተካረረ ከረጅም ጊዜ አንጻር ምናልባትም የዓለም ንግድ ድርጅትን ተሰሚነት እንዳያሳጣም የሚያሰጋ ነው። ይህ ሁሉ እንዳይሆን በቅርቡ የተገባደደው ያለፈው የጎርጎሮሣውያኑ 2011 ዓመተ-ምሕረት የዶሃን ድርድር ዙር ከግብ በማድረሱ በኩል «የሞት-የሽረት» ወሣኝ ዓመት እንደሚሆን ነበር የተነገረው። ግን የተባለው ገቢር አልሆነም። በዓመቱ መጨረሻ በታሕሣስ ወር የተካሄደው የድርጅቱ የሚኒስትሮች ስብሰባ ያላንዳች ውጤት መፈጸሙ ገና የቅርብ ትውስት ነው። ለምን? ጉዳዩ እንዴት ንው የሚቀጥለው?

የዓለም ንግድ ድርጅት ዓባል ሃገራት በ 2001 ማለት ከአሥር ዓመታት በፊት ካታር ርዕሰ-ከተማ ዶሃ ላይ ለፍትሃዊ ንግድ አዲስ የድርድር ዙር ለመጀመር ሲስማሙ ትልቅ ውጥን ይዘው ነበር የተነሱት። ዕቅዱ ገቢር ቢሆን ቀረጥንና ሌሎች የንግድ መሰናክሎችን በማስወገድ ዓለምአቀፉን ንግድ የሚያጠናክርና በተለይም ብልጽግናን የሚያስከትል ይሆናል ተብሎ ነበር የታመነው። በንግድ መሰናክሎቹ መነሣት ደግሞ ይበልጥ ተጠቃሚዎቹ ታዳጊዎቹ ሃገራት በሆኑ ነበር። ለዚህም ነው ድርድሩ በጊዜው «የዶሃ የልማት ድርድር ዙር» ተብሎ መሰየሙ!

የሆነው ሆኖ ዛሬ ያ ሁሉ ሕልም ከንቱ ሆኖ መቅረቱ ነው ጎልቶ የሚታየው። በዕውነቱ የዶሃ ድርድር ሞቷል ባይ አጣ እንጂ ከመቃብር አፋፍ ላይ እንደቆመ ያህል ቢቆጠር ማጋነን አይሆንም። አሥር ዓመታት ባስቆጠረው የድርድር ወቅት ዓለምአቀፉን ንግድ በሚመለከቱ ሃያ ቁልፍ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ አንድነት ሳይገኝ ቀርቷል። በነገራችን ላይ በጉዳዩ ከስምምነት ቢደረስ እንኳ በዓለም ንግድ ድርጅት ድምብ መሠረት በአንድ ድምጽ ተቀባይነት ማግኘቱ ግድ በሆነ ነበር።

ይሄው የጀኔቫው ተቋም በአንድ በኩል ዓባላቱ ትንሽ ሆኑ ትልቅ ሁሉንም እኩል የሚያደርግ መብት የሚሰጥ ደምብ ቢኖረውም በሌላ በኩል እርግጥ በአንድ ድምጽ ውሣኔ ማስፈንን የሚያከብድ መሆኑ አልቀረም። ይህን በዚሁ ተወት እናድርገውና በዶሃው ድርድር ዙር ሂደት ለረጅም ጊዜ ዋና የክርክር ነጥብ የነበረው የእርሻ ልማት ጉዳይ ነው። በአንድ በኩል በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት ምዕራባውያን መንግሥታት ዓምት-ከዓመት ለአገራቸው ገበሬዎች የሚሰጡትን በብዙ ሚሊያርድ ዶላር የሚገመት የገንዘብ ድጎማ በአግባብ ለመቁረጥ ዝግጁ አለመሆናቸው ለድርድሩ መስናከል ትልቁ ምክንያት መሆኑ ያታወሣል።

ታዳጊዎቹ ሃገራትም በፊናቸው ገበሬዎቻቸውን ከምዕራቡ ፉክክር ለመጠበቅ ገበዮቻቸውን ልቅ ማድረጉን አልፈቀዱትም። እነዚህ መሠረታዊ ነጥቦችም ነበሩ በ 2003 ዓመተ-ምሕረት ሜክሢኮ-ካንኩን ላይ ተካሂዶ ለነበረው ድርድር መክሸፍ ምክንያት የሆኑት። እንዲህ ሲል በተከታዮቹ ዓመታት ደግሞ ሌላ የውዝግብ ነጥብ ግንባር ቀድም እየሆነ ይመጣል። የዓለም ንግድ ድርጅት ጠቅላይ ጸሐፊ ፓስካል ላሚይ ባለፈው ታሕሣስ ጀኔቫ ላይ በተካሄድው በቅርቡ የሚኒስትሮች ጉባዔ ዋዜማ በጉዳዩ የሚከተለውን ነበር የተናገሩት።

«ከሃያዎቹ ነጥቦች መካከል የትኛው የውሣኔያችን መሰናክል እንደሆነ እናውቃለን። ይህም በኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ የሚደረግ ቀረጥ ቅነሣን የሚመለከት ነው። በዚህ ጉዳይ በአንድ በኩል በአሜሪካና በሌላ በኩል በተፋጠነ ዕድግት ላይ በሚገኙት ሃግራት መካከል የማይታረቅ ቅራኔ ነው ያለው»

ይህ ቅራኔ ደግሞ የዓለም ኤኮኖሚ ይዞታ በፍጥነት መለወጥ ያስከተለው ነገር ነው። በዓለም ላይ ለረጅም ጊዜያት ሁለት ዓይነት የመንግሥታት ቡድኖች ብቻ ሕያው ሆነው ቆይተዋል። በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታትና ድሆቹ ታዳጊ ሃገራት ብቻ! ሆኖም ግን በቻይና፣ በሕንድ ወይም በብራዚል የተከሰተው ፈጣን የኤኮኖሚ ዕድገት ሌላ ሶሥተኛ ቡድን ሕያው እንዲሆን አድርጓል። እነዚህ ደግሞ ዛሬ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸገውን ዓለም በአውቶሞቢል፣ በምርት መኪናዎችና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጥበብ ጭምር ተፎካካሪ ለመሆን የበቁ ናቸው።

«አሜሪካ በወቅቱ የያዘችው የክርክር ነጥብ በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙት እነዚህ ሃገራት ተፎካካሪዎቻችን ስለሆኑ ለእኛ የሚሰራው ደምብ በነርሱም ላይ ሊጣል ይገባል የሚል ነው። በተፋጠነ ዕድገት ላይ ያሉት መንግሥታት ደግሞ አዎን ከሶሥተኛው ዓለም ድሆች አገሮች የበለጠ ሃላፊነት እንዳለብን እናውቃልን፤ እንቅበለዋለንም ባዮች ናቸው። ይሁን እንጂ ከኢንዱስትሪው ዓለም ጋር በአንድ ዓይንት ደምብ መታቀቡን አይፈቅዱትም»

የዓለም ንግድ ድርጅት ጠቅላይ ጸሐፊ ፓስካል ላሚይ አያይዘው እንደሚያስረዱት ቻይናን የመሳስሉት መንግሥታት ለያዙት ለዚህ አቋም ብዙ ምክንያቶች አሉ። ከነዚህም አንዳንዶቹ ፖለቲካዊ ሲሆኑ እነዚህን ደግሞ በመሠረቱ ከዓለም ንግድ ድርጅት ጋር የሚያገናኛቸው ነገር የለም።

«ቻይና፣ ሕንድ፤ ብራዚል ወይም ኢንዶኔዚያ እንደ ኢንዱስትሪው ዓለም የሚቆጠሩ መሆናቸውን አምነው ቢቀበሉ ይሄው በአካባቢ አየር ጥበቃ ድርድር ላይም ግዴታቸውን የሚያጠናክር ነው የሚሆነው»

ስለዚህም እነዚህ ሃገራት ጠንካራ የአካባቢ ጥበቃ ደምብ እንዲጣልባቸው የማይፈልጉ ሲሆን ይህንኑም አጥብቀው ሲከላከሉ ነው የቆዩት። ዕድገትን አደጋ ላይ ይጥላል ባዮች ናቸው። ከዚሁ ሌላ በኢንዱስትሪ ልማት ከበለጸጉት ሃገራት አንጻር በነፍስ ወከፍ ሲሰላ ተፈጥሮን ይበልጥ ከሚበክሉት ከነርሱ እኩል መገፋቱን አይቀበሉም።

አሜሪካም ቢሆን በዓለም ንግድ ድርድር ላይ አወዛጋቢውን መንግድ ለመምረጧ የራሷ ምክንያት አላት። ባለፉት ዓመታት የአገሪቱ ኢንዱስትሪ ስራ-አጥ ቁጥር እጅጉን እየጨመረ ሲመጣ የንግድ ኪሣራዋም ከፍተኛ ጣራ ላይ ደርሷል። የተዳከመችው ሃያል መንግሥት አሜሪካ ዛሬ ራሷን የዓለም ኤኮኖሚ ትስስር-የግሎባላይዜሺን ተጠቃሚ ከመሆን ይልቅ ሰለባ አድርጋ ነው የምትመለከተው። ከዚህ አንጻር ለዓለም ንግድ ፍትሃዊነት መቆም በምርጫ ለማሸንፍ የሚበጅ እንደማይሆን ግልጽ ነው።

በሌላ አነጋገር ታዋቂው የኒውዮርኩ ኮሉምቢያ ዩኒቨርሲቲ የኤኮኖሚ ተመራማሪ ጃግዲሽ ባግዋቲ እንደሚያስረዱት ከአሜሪካ ኢንዱስትሪና የሙያ ማሕበራት አኳያ የዶሃው ድርድር ዙር መክሸፉን የሚሹት ጥቂቶች አይደሉም። ምክንያቱም የንግድ ገደብን ማንሣቱ በያንዳንዱ ዘርፍ የፉክክር መጠናከርን የሚያስከትል ሆኖ ነው የሚታየው።

«ፕሬዚደንት ኦባማ በንግዱ ጉዳይ ላይ ዝግ ያሉ ናቸው። እንደማስበው ዶሃ የምትለዋን ቃል ባለፈው ዓመት አንዴ እንኳ ከአፋቸው አላስገቡም። ይሄ ደግሞ በጣም የሚያሳዝን ነው። ምክንያቱም፤ እስቲ የድርድሩን ዙር እስካሁን በደረስንበት ውጤት እንደምድም፤ የተቀሩትን ገና ማሰሪያ ያላገኙ ነጥቦች ደግሞ አቆይተን በአዲስ ድርድር እንቀጥላለን ብለው ሊናገሩ በተገባ ነበር። በዚህ መንገድ ውሣኔ ላይ መድረስ በተቻለ»

እርግጥ የአሜሪካ አቋም ኦባማ ወደው የመረጡት አይደለም። መላው ካቢኔያቸው የንግድ ጉዳይ ሲነሣ በፍርሃቻ እንደሚዋጥ ነው የኒውዮርኩ የኤኮኖሚ ጠቢብ ባግዋቲ የሚናገሩት። በዚሁ የተነሣም ከዓለም ንግድ ድርጅት ውጭ የሁለት ወገን የነጻ ንግድ ውል የማስፈኑ ጥረት እንደገና እየጠነከረና አማራጭ እየሆነም ነው። ይህን የጀርመኗ ቻንስለር ውሮ/አንጌላ ሜርክልም ባለፈው ጥር በዳቮሱ ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ መድረክ ላይ ጠቅሰውት ነበር።

«በዶሃው ድርድር ወደፊት መራመድ መቻሉን ከባድ ሆኖ ስላገኘነው ምንም እንኳ እኔ በበኩሌ ጥሩው አድርጌ ባልመለከተውም በአካባቢዎች መካከል ውል ማስፈኑ አማራጭ መንገድ ነው። ለምሳሌ የአውሮፓ ሕብረት ከሌላው አካባቢ ጋር የንግድ ውል ሊፈራረም ይችላል። ይህን ክደቡብ ኮሪያ ጋር አድርገነዋል። ከጃፓን ጋር ደግሞ እየተዘጋጀንበት ነው። በተረፈ በትራንስ አትላንቲክ ደረጃም ለዚህ ብዙ ዕድል እንዳለ ነው የማምነው»

የአውሮፓ ሕብረትንና አሜሪካን ለመሳሰሉት በምጣኔ-ሃብት ሃያል ለሆኑ አካባቢዎች እርግጥ ደቡብ ኮሪያን ወይም ሕንድን ከመሳሰሉ ሃገራት ጋር በነጻ ንግድ ውል በቀጥታ መደራደሩ ፍላጎታቸውን ለማራመድ እንደሚቀላቸው አንድና ሁለት የለውም። በአንጻሩ በዓለም ንግድ ድርጅት ስር መደራደሩ ደግሞ ለታዳጊዎቹ ሃገራት በተናጠል እንዳይገፉ የሚበጅ ነው። በመሆኑም በዓለም ንግድ ድርጅት መክሸፍ ይበልጥ ተጎጂዎቹ በተለይም እነዚሁ ታዳጊዎቹ ይሆናሉ።

ያም ሆነ ይህ የዶሃውን ድርድር ዙር ወደፊት ለማራመድ የተደረገው የቅርቡ ጥረት ከከሸፈ ወዲህ ለሁሉም ወገን የሚስማማና ሁሉንም የሚያስማማ ውል ገሃድ የመሆኑ ዕድል ይብስ እየራቀ ነው የሄደው። ባለፈው ታሕሣስ ወር ሩሢያ በንግድ ድርጅቱ ዓባልነት መታከሏ ሲታሰብ ደግሞ የወደፊቱ ድርድሮች እንዲያውም ይከብዱ እንደሆን እንጂ እየቀለሉ መሄዳቸው የማይጠበቅ ነገር ነው። ይሁንና የዓለም ንግድ ድርጅት ጠቅላይ ጸሐፊ ፓስካል ላሚይ የዶሃውን ዙር ሞት ለማወጅ ፈቃደኛ አይደሉም። ይልቁንም በዙ ትዕግሥት ያስፈልጋል ባይ ናቸው።

«ዓለምአቀፍ ድርድሮች ጨርሶ አይሞቱም። ይህ ክታሪክ የምንማርው ነገር ነው። ለምሳሌ የባሕር እንስሳ ማጥመድን የሚገድብ ውል ለማስፈን የሚደረገው ድርድር ይሄው ከ 45 ዓመታት በላይ መቀጠሉ መዘንጋት የለበትም»

የላሚይ ጽናት ዶሃን ክማዳኑ ተሥፋ ይልቅ የዓለም ንግድ ድርጅታቸውን ዝና በመጠበቁ ላይ ይበልጡን ያለመ ነው የሚመስለው። ታዳጊ ሃገራትን ከዓለም ንግድ ጋር በተሻለ ሁኔታ ለማዋሃድ ከእንግዲህ ተጨማሪ አሠርተ-ዓመታት እንደገና መንጎድ የለባቸውም። በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት ለታዳጊ ሃገራት የእርሻ ምርቶች ገበዮቻቸውን በመክፈት ለዕድገት አስተዋጽኦ ማድረጋቸው በመሠረቱ ነገ የማይባልበት ጉዳይ ነው። በጥቅሉ አዳጊዎቹን ሃገራት የዕርዳታ ጥገኛ በማድረግ ፋንታ ለመልማት የሚጠቅማቸውን በር መክፈቱ ቀናው መንገድ ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ