1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዶሮ እርባታ በኢትዮጵያ

Eshete Bekeleረቡዕ፣ ሐምሌ 13 2008

አዲስ አበባ ላይ ዛሬ አንድ እንቁላል ከ3 ብር ከ75 ሳንቲም እስከ አራት ብር ይሸጣል። በኢትዮጵያ የሚከወነው ልማዳዊ የዶሮ እርባታ የዜጎችን ፍላጎት ማሟላት ካለመቻሉም ባሻገር ከቀን ወደ ቀን የሚያሻቅበውን ዋጋ መግታት ተስኖታል።

https://p.dw.com/p/1JSjU
Frisch geschlüpfte Hühner-Küken
ምስል picture-alliance/dpa/Ph. Schulze

የዶሮ እርባታ ሥራ

በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ማዕከል እና ዓለም አቀፉ የቤት እንስሳት ምርምር ማዕከል ከምሥራቅ ወለጋ ሖሮ የተሰኘ አካባቢ የተገኘ የዶሮ ዝርያን ለማሻሻል በጥረት ላይ ናቸው። በዚህ የማሻሻል ጥረት ሖሮ የተሰኘ ሥያሜ የተሰጠው የዶሮ ዝርያ በዓመት የሚጥለውን እንቁላል ወደ 180 ማሳደግ ችለዋል። ይህ ግን ወደ አንድ መቶ ሚሊዮን ለሚደርሰው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት በቂ አይደለም። ዶ/ር ታደለ ደሴ በዓለም አቀፉ የቤት እንስሳት ምርምር ማዕከል የፕሮጀክት ኃላፊ ናቸው።

ዓለም አቀፉ የቤት እንስሳት ምርምር ማዕከል ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ከጥቂት ዓመታት በፊት ይፋ ባደረገው ጥናት 38.1 ሚሊዮን ዶሮዎች እንዳሉ ጠቁሟል። ከዚህ ውስጥ 99 በመቶው ያለ ዘመናዊ መጠለያ፤ የዓመጋገብ ሥርዓት እና የጤና አጠባበቅ በሌለበት በልማዳዊ የዶሮ አረባብ ሥርዓት ውስጥ የሚገኙ ናቸው። በኢትዮጵያ ቅይጥ ግብርና ከእርሻ ሥራና ከብት ርባታ በተጓዳኝ ዶሮ ማርባት ለዘመናት የቆየ ባህላዊ ሥራ ቢሆንም ከነበረበት ፈቅ አላለም። ዶሮ እርባታ ለዘመናት ለቤተሰብ ገቢ መደጎሚያ እና ጠቃሚ የፕሮቲን ምንጭ ሆኖ ዘልቋል የሚሉት ዶ/ር ታደለ ደሴ አሁንም የኢትዮጵያ ባለወረቶች በዘርፉ ለመሰማራት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ይተቻሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት የጥቃቅንና አነስተኛ እቅድን ሲያስተዋውቅ ለሥራ አጥ ወጣቶች ከታቀዱት መካከል አንዱ የሆነው ዶሮ እርባታና የእንስሳት መኖ ዝግጅት እንደታሰበው ውጤታማ አልሆነም። እስከ ሁለት ሚሊዮን ብር ከመንግሥት የገንዘብ ተቋማት ተበድረው ሥራውን ከጀመሩ ወጣቶች አንዳንዶቹ የዶሮ ዝርያ፤ መድሐኒት እና መኖ እጥረት ገጥሟቸው ለኪሳራ መዳረጋቸዉን ይናገራሉ። በዘርፉ ስኬታማ ሆነው የተሻለ ገቢ ማግኘት የቻሉም አሉ።
በመግሥት እና የግል ባለሐብቶች ጥምረት ባለቤትነት የሚተዳደረው መቀሌ እርሻ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የዶሮ ዝርያዎችን በማራባት ለገበሬዎች ያከፋፍላል። ድርጅቱ የፈረንሳይ፤ ሆላንድ፤ ሕንድ እና ቼክሪፐብሊክ ያመጣቸውን የዶሮ ዝርያዎች በማራባት ለገበሬዎች ያከፋፍላል። የድርጅቱ ኃላፊ ዶ/ር ብርሐነ ግርማይ በገበሬዎች ዘንድ የነበረው ግንዛቤ አነስተኛ መሆን ፈተና ፈጥሮባቸው እንደነበር ይናገራሉ።


ዶ/ር ታደለ ደሴ በቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የገንዘብ ድጋፍ ተግባራዊ የሚደረግ እቅድ በበላይነት ይመራሉ። እቅዱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በታንዛኒያ እና ናይጄሪያ ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን ለአገራቱ ሥነ-ምህዳር ተስማሚ የሆኑ የዶሮ ዝርያዎችን ፈትሾ ለገበሬዎች የማስተዋወቅ አላማ አለው።
ዶ/ር ብርሐነ ግርማይ የዶሮ እርባታ ሥራ ለቸልተኞች እንደማያዋጣ ነዉ የሚናገሩት። ከደንበኞቻቸው መካከል በጥንቃቄ እና በትጋት የሠሩት ስኬታማ ሆነዋልም ይላሉ።

ዶሮዎችን ከሚያጠቁ በሽታዎች መካከል ፈንግል፣ ፈንጣጣ፣ ሊምፎይድ፣ ሊውኮሲስ የሚባሉት በምሳሌነት ይጠቀሳሉ። በሽታዎቹ የሚተላለፉባቸው መንገዶችም አያሌ ናቸው። ከነዚህም ውስጥ በንክኪ፣ እርስ በርስ በመነካከስ፣ በተበከለ ውኃ ወይም መኖ፣ በአፈር፣ ደም በሚመጡ ተባዮች፣ በሰውና በእንቁላል አማካኝነት የሚተላለፉ አሉ። ዶሮዎቹን ለይቶ ማርባት፣ ሠራተኞችን በበቂ ሁኔታ ማስተማር፣ የንጽሕና አጠባበቅና ቁጥጥርን ማጠናከርና ክትባት በሽታዎቹን ለመከላከል የሚጠቅሙ ዘዴዎች ናቸው። ዶ/ር ታደለ ደሴ በሚመሩት እቅድ መሠረት በኢትዮጵያ በቂና ውጤታማ ክትባት እንዲኖር ለማድረግ እየተሠራ ነው።

እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ

Hühner Markt Kongo Afrika
ምስል Getty Images
Verdacht auf Täuschung bei Bio-Eiern
ምስል picture-alliance/dpa