1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዶክተር ፍቅሩ ማሩ እቅድ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 21 2010

በቅርቡ በምህረት የተፈቱት የልብ ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ፍቅሩ ማሩ የሳቸው ሕክምና እና ክትትል ያስፈልጋቸው የነበሩ ከ 20 የሚልቁ ሕሙማን በእስር ማረሚያ ቤት በቆዩባቸው ዓመታት ውስጥ መሞታቸውን አስታወቁ :: ከመታሰራቸው በፊት የልብ ባትሪ የገጠሙላቸውን እነዚህኑ ሕሙማን በፖሊስ እየተጠበቁም ቢሆን ለማከም ቢጠይቁም ውድቅ ተደርጎባቸዋል።

https://p.dw.com/p/2yYnc
Addis Abeba, Äthiopien
ምስል Belay Manaye

Ber. Frankfurt(Intv. Dr. Fikru Maru) - MP3-Stereo

 

በአሁኑ ወቅት ስዊድን የሚገኙት ዶክተር ፍቅሩ እንዳሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ከስዊድን መንግሥት እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ በመሰረቱት የልብ ሕክምና መስጫ ተቋም አማካኝነት ለበርካታ ዓመታት ለልብ ሕሙማን ነጻ የሕክምና እና ለጤናው ዘርፍ ባለሙያዎች የዕውቀት ሽግግር ሥልጠና ለመስጠት ይመጡ የነበሩ የስዊድን የሕክምና ባለሙያዎች አገልግሎት ለደህንነታቸው ባደረባቸው ሥጋት ምክንያት መቋረጡንም አስረድተዋል :: ያለማስረጃ በተመሰረቱብኝ የሙስና እና የሽብር ወንጀል ሃሰተኛ ክሶች ከ 4 ዓመታት በላይ በማረሚያ ቤት ስቃይ እና በደል ተፈጽሞብኛል የሚሉት የቀዶ ሕክምና ባለሙያው ያም ቢሆን አሁንም ተመልሰው የሚወዱትን ሕዝባቸውን እና ሃገራቸውን በሙያቸው የማገልገል ዕቅድ እንዳላቸው በተለይ ለዶቼቨለ ገልጸዋል :: ::

በስዊድን አሉ ከሚባሉ ሥመጥር የልብ ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስቶች መካከል ስማቸው ይጠቀሳል :: በሙያቸውም እዛው አውሮፓ ውስጥ ከ 35 ዓመታት በላይ በማገልገል ክህሎታቸውን ያስመሰከሩ ባለሙያ ናቸው ዶክተር ፍቅሩ ማሩ:: የስዊድን ዜግነት ያላቸው 66 ዓመቱ የልብ ሕክምና ስፔሻሊስት ከዛሬ 19 ዓመታት በፊት የተጠናከረ የልብ ሕክም ዘመናዊ መሳሪያ እና በቂ ባለሙያ ባልነበረበት ሁኔታ በሺዎች የሚቆጠሩ ህሙማን ህይወታቸውን ያጡበት የነበረውን ችግር ተገንዝበው ሕዝብ እና ሃገራቸውን ለማገልገል ወደ ኢትዮጵያ መጡ :: እ.ኤ.አ በ2006 ዓ.ም በምሥራቅ አፍሪካ በአይነቱ ልዩ የሆነ ዘመናዊ የልብ ሕክምና መስጫ ማዕከል ከ 19 ሚልዮን ብር በሚልቅ ወጭ በስዊድን መንግሥት የልማት እርዳታ በኢትዮጵያውያን ድጋፍ እና በራሳቸው መዋጮ ጭምር አቋቋመዋል :: በዚህም በጎ ተግባር የልብ ሕክምና ለማግኘት ወደ ውጭ ለሚሄዱ ኢትዮጵያውያን ሀገሪቱ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማሰቀረት ተችሏል፡፡ ከዚህ ሌላ ሃኪሞች እና ነርሶች ስዊድን ሄደው በልብ ሕክምና ሙያዊ ብቃታቸውን እንዲያጎለብቱ ትልቅ እገዛ አበርክተዋል :: ዶክተር ፍቅሩ ከ 4 ዓመታት በፊት ከቀድሞው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣኖች ጋር የጥቅም ግንኙነት በማድረግ ለሕክምና መስጫ ማእከሉ ከቀርጥ ነጻ የሆነ የሕክምና መስጫ መሳሪያ ለማስገባት ሞክረሃል የሚል ክስ ተመሰረተባቸው:: ቆይቶም በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ከተሳው ቃጠሎ የህይወት እና ንብረት መውደም ጋር በተያያዘ ግንቦት 7 ለተባለ “ሽብርተኛ” ቡድን የገንዘብና የማስተባበር እርዳታ በማድረግ ተሳትፏል የሚል ክስ ተጨምሮባቸው ለ 4 ዓመታት ከ 8 ወራት ማረሚያ ቤት ቆይተዋል :: በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና የስዊድን መንግሥት ባለሙያው እንዲፈቱ ከፍተኛ ግፊት አድርገዋል :: በቅርቡ በምህረት የተለቀቁት ዶክተር ፍቅሩ እሳቸው ሲከታተሏቸው የነበሩ ከ 20 የሚልቁ ልዩ መሳሪያ የተገጠመላቸው የልብ ሕሙማን እሳቸውን ተክቶ የሚሰራ ስፔሻሊስት ሃኪም ሃገር ውስጥ ባለመኖሩ ለሕልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን በተለይ ለዶቼቨለ ገልጸዋል :: ባለሙያው በፖሊስ እየተጠበኩም ቢሆን ነጻ የሕክምና አገልግሎት ልስጣቸው ስል ለፍርድ ቤት ያቀረቡት ተደጋጋሚ ጥያቄ ከአንድ ጊዜ በስተቀር ሰሚም ተቀባይነትም አላገኘም ይላሉ ::

ታዋቂው የልብ ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ፍቅሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ከስዊድን መንግሥት እና ከሌሎችም የሃገር ውስጥ ሙያተኞች ጋር በጋራ ባቋቋሙት ልዩ የልብ ሕክምና መስጫ ተቋም አማካኝነት እ.ኤ.አ ከ 2008 ዓ.ም ጀምሮ በዓመት ለ 3ጊዜያት ያህል በሃገሪቱ የሚገኙ የልብ ሕሙማንን ለማከም እና ለባለሙያዎችም ዘመናዊ የዕውቀት ሽግግር ሥልጠና ለመስጠት ከስዊድን ድረስ ይመጡ የነበሩ የሕክምና ባለሙያዎችም የሳቸውን መታሰር ተከትሎ ለደህንነታቸው ሥጋት ስላደረባቸው አገልግሎቱ መቋረጡን ነግረውናል :: በእስር ቆይታቸው ሕይወታቸውን ለአደጋ የሚያጋልጥ ከባድ ሕመም ገጥሟቸው እንደነበረ የሚያስታውሱት ባሉሙያው ምንም እንኳን ባልፈጸሙት ወንጀል የተቀነባበረ ክስ ተመስርቶባቸው ብዙ ሰቆቃ የሰብአዊ መብት ጥሰት እና እንግልት ቢፈጸምባቸውም አሁንም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የሚወዱትን ሕዝብ እና ሃገራቸውን በቀሪ እድሜያቸው በትጋት ለማገልገል ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸውም ነው የገለጹልን:: አዲስ አበባ ውስጥ በጋራ የመሰረቱት የልብ ሕክምና መስጫ ሆስፒታልም ቢሆን አሁንም ተጠናክሮ አገልግሎቱን እንዲሰጥ እገዛ ማበርከታቸውን ቀጥለዋል ::

በኢትዮጵያ ያለው አጠቃላይ የፍትህ ሥርዓት አድሎአዊ እና ቢሮክራሲያዊ ውጣወረድ የበዛበት በመሆኑ ከሥር መሰረቱ መሻሻል አለበት የሚሉት የልብ ቀዶ ሕክምና ባለሙያው ዶክተር ፍቅሩ ማሩ አሁን በሃገሪቱ የሚታየው የለውጥ ጭላንጭል በተለይም ፍርድ ቤት ማረሚያ ቤት እና ፖሊስ በጋራ በተከሳሾች ላይ የሚፈጽሙትን ጭቆና እና በደል የሚያስቀር የፍትሕ አካላቱ በነጻነት እና ያለ አድልዎ የሚሰሩበትንም መንገድ የሚያስተካክል ሊሆን ይገባዋል ሲሉ አስገንዝበዋል ::

እንዳልካቸው ፈቃደ

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ