1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ከፓርቲ ፖለቲካ መራቅ

ሰኞ፣ ጥር 12 2006

የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በእንግሊዝኛው ምህጻሩ UDJ ሊቀመንበርነታቸውን መልቀቃቸውን አስታወቁ። ሊቀመንበርነታቸውን ብቻም ሳይሆን ከUDJ አባልነትም የተሰናበቱት ዶ/ር ነጋሶ ከዚህ በኃላ በማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ አልሳተፍም ብለዋል።

https://p.dw.com/p/1Atwc
Äthiopien Partei UDJ
ምስል DW/Y.Gebreegziabher

ይህ ማለት ግን ከኣገሪቱ ፖለቲካ ጨርሶ መራቅ ኣለመሆኑንም ኣክለው ኣስታውቐል።

ዶ/ር ነጋሶ ከዚህ ውሳኔ የደረሱት የእድሜ ጫናን ጨምሮ በጤንነታቸው ምክንያትና በተለይም ደግሞ በፓርቲያቸው ውስጥ በተፈጠሩ ፖለቲካዊ ልዩነቶችም ጭምር መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

ዶ/ር ነጋሶ ከኣንድነት ፓርቲ ብቻም ሳይሆን ከዚህ በኃላ በማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ እንደማይሳተፉም ነው የገለጹት።

አንደኛው ምክንያት የእድሜ ጫና ሲሆን የጤንነታቸው ሁኔታም እንደ ምክንያት ተጠቅሷል። ይህ ብቻም ሳይሆን ግን ዶ/ር ነጋሶ እንደሚሉት በእርሳቸው እና በተቀሩት የኣንድነት ፓርቲ ኣመራሮች መካከልም ልዩነቶች ተፈጥሯል።

Bildergalerie Demonstration Oppositionspartei UDJ in Äthiopien
ምስል DW

ቀደም ባሉት ዓመታት የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን ጨምሮ በኦሮሞ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዲድ) ውስጥም ከፍተኛ የዓመራር አከል የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በቡድን መብቶች መከበር ላይ የማይደራደሩ ፖለቲከኛ መሆናቸው ሲታወቅ ህብረ ብሔራዊ ከሆነው የኣንድነት ፓርቲ ኣመራር አባላት ጋር ያልተጣጣሙበት ሌላኛው ምክንያት በግለሰብ መብት እና በቡድን መብት መካከል ባለው ኣንድነት፣ ልዩነትና ቅደም ተከተል ላይ ነው የሚሉ ወገኖችም ኣሉ።

ዋናው ምክንያት ግን ዶ/ር ነጋሶ እንደሚሉት ከመድረክ ጋር ሊኖር በሚገባው ግንኙነት ላይ ነው። የኣንደነት ኣመራሮች ከዚህ በኃላ ውህደት ካልሆነ በግንባርነት ከማንኛውም ፓርቲ ጋር ላለመቀናጀት አቋም ሲይዙ ዶ/ር ነጋሶ ግን በዚህ ኣይስማሙም።

ምንም እንኳን ምርጫ በተቃረበበት ወቅት ቢሆንም የእኔ መገለል በፓርቲው ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ያንን ያህል የጎላ ኣይመስለኝም የሚሉት ዶ/ር ነጋሶ ከፓርቲ ፖለቲካ ቢለዩም ታዲያ ከኣገሪቱ ፖለቲካ ጨርሶ እንደማይርቁ ግን ኣረጋግጧል።

Äthiopien Partei UDJ
ምስል DW/Y.Gebreegziabher

ከ1960 ዎቹ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ጀምሮ በኣውሮፓ የኦሮሞ ተማሮዎች ማህበር ኣመራር አካል የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ በጀርመን ኣገር የኦሮሞ ነጻነት ግምባር ከፍተኛ ዓመራርም የነበሩ ሲሆን ከ1983 ዓም ጀምሮ ግን ወደ ኣገር ቤት ተመልሰው የኦሮሞ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዲድን) መቀላቀላቸው ይታወቃል።

ኦህዲድን በመወከል ከካቢኔ ሚኒስትርነት እስከ ር/ብሔርነት የደረሱት ዶ/ር ነጋሶ በገዢው ፓርቲ ውስጥ ተፈጥሮ በነረው ፖለቲካዊ ቀውስ ከጠ/ሚ መለስ ጋር ቅራኔ ውስጥ በመግባታቸው ሰኔ 15 ቀን 1993 ዓም ያውም በድፍረት ተናግረው ኦህዲድንም ሆነ ኢህኣዲግን ለቀው በመውጣት ጭምር ይታወቃሉ።

ከዚያ ወዲህ በኢንጅነር ግዛቸው ተተክተው ሲመሩ የቆዩትን ኣንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲንም ኣሁን ሲለቁ እንደ ኢህኣዲግ እያወገዙ ሳይሆን ግን መልካሙን ሁሉ በመመኘት መሰናበታቸውን ኣውጀዋል። ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ።

ጃፈር ዓሊ

ነጋሽ መሓመድ