1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመኑ የልማት ተራድኦ ሚንስትር በአፍቃኒስታን

ዓርብ፣ መጋቢት 24 2002

አፍቃኒስታንን ዳግም ለመገንባት የሚደረገዉ ጥረት አበረታች ዉጤት ቢያሳይም ሐገሪቱ የመንግሥት አመራር ጉድለት፥ ሙስናን የመዋጋት እጥረትና የፀጥታ ችግር አልተለያትም

https://p.dw.com/p/Mm9t
ኒበል ከካርዛይ ጋርምስል picture-alliance/dpa

02 04 10

የጀርመን የልማት ተራድኦ ሚንስትር ዲርክ ኒበል በአፍቃኒስታን የሚያደርጉን የሰወስት ቀን ጉብኝት ትናንት ጀምረዋል።ኒብል ትናንት ወደ ካቡል ከመሔዳቸዉ በፊት እንዳስታወቁት አፍቃኒስታንን ዳግም ለመገንባት የሚደረገዉ ጥረት አበረታች ዉጤት ቢያሳይም ሐገሪቱ የመንግሥት አመራር ጉድለት፥ ሙስናን የመዋጋት እጥረትና የፀጥታ ችግር አልተለያትም።ሚንስትሩ ከአፍቃኒስታን ባለሥልጣናት ጋር በሚያደርጉት ዉይይት የተሐድሶ ለዉጡ ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ያተኩራሉ።ማርክ ክሌበር የዘገበዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

ትናንት ካቡል የገቡት ያዉ በሚንስትርነት ሥልጣን-ማዕረጋቸዉ ነዉ።ዲርክ ኒበል። ለአፍቃኒስታን ግን እንግዳ አይደሉም።ከስምንት አመት በፊት ያዉቋታል።እሳቸዉ በርግጥ ተለዉጠዋል።እድገት። አፍቃኒስታንም ብዙ ተለዉጣለች።ግን የቁልቁሊት።«በአሉታዊ ገፅታዋ» አሉ እሳቸዉ።

«ከስምንት አመት በፊት ከዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ፊሸር ጋር አፍቃኒስታን ሥመጣ ገና የፈገግታና የሠላምታ ጊዜ ነበር።ወታደሮቻችን በግልፅ መኪኖች ከሥፍራ ሥፍራ የሚዘዋወሩበት፥እግረኛ ቃኚዎች በአንፃራዊ ሁኔታ ያለ ብዙ መከላከያ በየመንደሮቹ የሚንቀሳቀሱበት፥ መንደርተኛዉ እንደ ጥሩ እንግዳ ይቀበላቸዉ የነበረበት ወይም በሕዝቡ መሐል የሚንቀሳቀሱበት ወቅት ነበር።ያ-ግን አሁን ተለዉጧል። (አደጋ) ይጣላል የሚለዉ ሥጋት በጣም አይሏል።»
የሚንስትሩም ሆነ የሌሎቹ የምዕራባዉያን ሐገራት ባለሥልጣናት ጉብኝት፥የሚጓዙበት አካባቢም በሚስጥር የሚያዘዉ፥ በጥብቅ የሚጠበቀዉም ለዚሕ ነዉ።አደጋ ይጣላል-ተብሎ ሥለሚፈራ።ኒበል በመጀመሪያ የጉብኝታቸዉ ዕለት ትናንት ከአፍቃኒስታኑ ፕሬዝዳት ሐሚድ ካርዛይ ጋር ተነጋግረዋል።ዉይይቱ በወዳጅነት መንፈስ የተደረገ ነበር-ይላሉ።መልዕክታቸዉ ግን ግልፅ ነበር።

«የጀርመን ፌደራል ኢፐብሊክ ለሲብሉ መስክ የምታደርገዉን ድጋፍ በእጥፍ ትጨምራለች።ይሁንና ገንዘቡን በመስኮት አናሽቀነጥረዉም።ቀረጥ ከፋዮቻችን ብዙ የደከሙበት ነዉና።»
ኒበል በእጥፍ ይጨምራል ያሉትን የመንግሥታቸዉን አዲስ ሥልት ለአፍቃኒስታን ባለሥልጣናት አስረድተዋል።ያስረዳሉም።በአዲሱ ሥልት መሠረት ጀርመን ለሲቢል ተቋማት ግንባታ የምትሰጠዉ ርዳታ በአመት ወደ 430 ዩሮ ከፍ ይላል።ከበፊቱ በእጥፍ ገደማ ያድጋል ማለት ነዉ።ከዚሕ ገንዘብ ዉስጥ 250 ሚሊዮኑ እራሳቸዉ ኒበል ከሚመሩት ከልማትና ተራድኦ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ካዝና የሚወጣ ነዉ።

አብዛኛዉ ገንዝብ ሥራ ላይ የሚዉለዉ ደግሞ የጀርመን ጦር በሠፈረበት በሰሜናዊ አፍቃኒስታን ለሚገኙ ተቋማት ግንባታ ነዉ።ሚንስትሩ ቀደም ሲል የጀርመን የርዳታ ገንዘብን ሥራ ላይ የሚያዉሉት ከጀርመን ጦር ጋር ተባብረዉ የሚሰሩ የርዳታ ድርጅቶች ብቻ ናቸዉ ማለታቸዉ ከፍተኛ ትችት አስከትሎባቸዉ ነበር።ትችቱ በበረታበት ሰሞን አቋማቸዉን የለወጡ መስለዉም ነበር።በአፍቃኒስታን ጉብኝታቸዉ ግን የመጀመሪያ እምነታቸዉን ደገሙት።
«ሰሜናዊ አፍቃኒስታን በግልፅ በሚታወቅ መስክ ና እዚያ የሰፈረዉ የጀርመን ሠራዊት ከሚያከናዉነዉ መርሕ ጋር ተቀናጅቶ መስራት የማይፈልግ በርግጥ የመስራት ግዴታ የለበትም።ነገር ግን ለልማት ከተመደበዉ ገንዘብም ተጠቃሚ አይሆንም።»

ሚንስትሩ የካቡል ጉብኝታቸዉን እንዳጠናቀቁ ወደ ሰሜናዊ አፍቃኒስታንን አቅንተዋል።ወደ ሰሜን አፍቃኒስታን ከማቅናታቸዉ በፊት መንግሥታቸዉ የሚሰጠዉ ርዳታ ለሕዝቡ በትክክልና ባስቸኳይ መድረስ እንዳለበት አስታዉቀዋል።

ማርክ ክሌበር

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለስ