1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመኑ የተረት አባት ዛንድማን

እሑድ፣ ኅዳር 27 2002

በጀርመን የተረት አባት እንደሆነ የሚነገርለት አሻንጉሊት ባለፉት ሳምንታት ዉስጥ ሃምሳ አመት ሞልቶት ልደቱ ተከብሮለታል። ጀርመናዉያኑ ዛንድ ማን ይሉታል። በኛ አገር በአፈ ታሪክ በተረት ስንዝሮ ብለን እንደምናዉቀዉ አይነት ማለት ነዉ።

https://p.dw.com/p/KqtN
ዛንድማንምስል picture-alliance/ dpa

የጀርመናዉያኑ ስንዝሮ ማለት ዛንድ ማን በጣም አጭር፣ ነጭ የፍየል አይነት ጢም አንተልጥሎ፣ ሾለል ያለ ቆብም የደፋ ነዉ። ዛንድ ማን በጀርመን ብቻ ሳይሆን በመላ አዉሮጻ ታዋቂ ነዉ ብል ከእዉነት የራኩ አይመስለኝም። ዘንድሮ ጀርመናዉያን ታድያ የዛንድ ማንን ሃምሳኛ አመት የልደት በአል ሲያከብሩ በኩራት ነበር፣ ለምን? ዛንድ ማን ትዉልዱ ምስራቅ ጀርመን በመሆኑ እና ለሁለት ተከፍላ የነበረችዉ ጀርመን አንድ ከሆነች በኻላም ዛንድ ማን በምዕራቡ ክፍል ይበልጥ ተወዳጅነትን በማጎልበቱ ነዉ። በዛሪዉ ዝግጅታችን በጀርመናዉያን ህጻናት ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ስለሆነዉ የተረት አበት ዛንድ ማን እና ባገራችን ስላለዉ የእንቆቅልሽ የተረት ጨዋታ ጋር እያዛመድን ይዘን ቀርበናል
«የተወደዳችሁ ህጻናት ከናንተ ጋር በማምሸቴ ደስታ ተሰምቶኛል
አሁን ቶሎ ወደመኝታችሁ ሂዱ የሰላም ጥሩ እንቅልፍም ይዉሰዳችሁ
ደህና እደሩ» ይላል፣ ሙዚቃዉ
በጀርመን አመሻሹ ላይ ህጻናት ለመኝታ ወደ አልጋቸዉ ከመሄዳቸዉ በፊት መልካም ምሽት መልካም እንቅልፍ እንዲሆንላቸዉ በቴሌቭዥን እና በራድዮ ለሃያ ደቂቃ ያህል ተረት ካወራ በኻላ ህጻናቱ ይህንን ሙዚቃ ከሰሙ በኻላ፣ ወደ አልጋቸዉ እንዲሄዱ፣ የሚያዛቸዉ የለም፣ የታወቀ በመሆኑ፣ ከተረቱ በኻላ ወደ መኝታ ነዉ። ታድያ ይኸዉ የአሻንጉሊት ምስል ማለት ዛንድ ማን በብዙሃን መገናኛ ለሃምሳ አመታት ያላማቋረጥ መረሃ ግብሩን ለህጻናት በማቅረቡ፣ ለዝያዉ ለአሻንንጉሊቱ ልደቱ፣ ባለፉት ሳምንታት ዉስጥ ሲከበርለት ሰንብቶአል። ይህ ነጭ ረዘም ያለ የፍየል ጢም የመሰለ ያለዉ አሻንጉሊት፣ የደፋዉም ቆብ ሾለል ያለ እና ባጠቃላይ በጣም አጭር በመሆኑ፣ በጀርመናዉያን ህጻናት ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ነዉ። በጀርመን የመገናኛ ብዙሃን የመግብያዉን ሙዚቃ ሲሰማ ልጅ ሁሉ፣ ይረብሽም ይጫወትም ሌላል ነገር ይሰራ ከሆነ፣ ተረቱን ለማዳመጥ ወደ ቴሌቭዥኑ ወይም ጆሮዉን ወደ ራድዮ ማድረጉ የግድ ነዉ። ማዉራት የለም አብሮ በመዘመር ይጀመራል። በለቱ ይዞት የሚቀርበዉን ተረት አሻንጉሊቱ እየተወዛወዘ ጺሙን ከፍ ዝቅ እያደረገ ተረቱን አዉርቶ እስኪ ጨርስ እረጭ ይላል። ጀርመን በሁለት ርዮተ አለም ተከፍላ ቆይታ መልሳ የተቀላቀለችበትን ሃያኛ አመት ዘንድሮ ስታከብር ይሄዉ በህጻናት ዘንድ ተወዳጅ የሆነዉ ምስል ማለት ዛንድ ማን ትልቅ የመነጋገርያ ርእስም ነበር።
እ.አ 1959 አ.ም በምስራቅ ጀርመን Gerhard Behrendt ለመጀመርያ ግዜ ለቴሌቭዥን የህጻናት መረሃግብር እንዲሆን ብለዉ የቀረጹት አሻንጉሊት እንደሆነ ጽሁፎች ያሳያሉ። ከምሽቱ አንድ ሰአት ግድም፣ በቴሌቭዥን ህጻናትን የደህና እደሩ ሊልና፣ ተረት ሊያወራ ብቅ ማለት የጀመረዉ። ከአሻንጉሊቱ በስተጀርባ ይህንኑ ምስል የቀረጹት ጀርመናዊ፣ ተረታቸዉን አዘጋጅተዉ ከበስተጀርባ ተደብቀዉ ተረትን በማዉራት ጥያቄ በመጠየቅ፣ ህጻናቱን፣ ደስ ወደ ሚለዉ የህልም አለም በመዉሰድ ትምህርት በማስተማር ተረታቸዉን አዉርተዉ ደህና እደሩ ብለዉ ይጨርሳሉ። በጀርመን ህጻናት ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የሆነዉ ይህ ምስል ማለት ዛንድማን ጀርመን ከተወሃደ በኻላ በምእራቡ ክፍል ባሉ አንዳንድ የራድዮ እና የቴሌቭዥን ጣብያዎች ጀምሮ፣ እንደ አ.አ 1997 አ.ም ጀምሮ ግን በመላ አገሪቱ ባሉ የብዙሃን መገናኛ ጣብያዎች፣ ስርጭቱ እንደቀጠለ ጽሁፎች ያሳያሉ። በጀርመን ህጻናት ቢያንስ ከምሽቱ ሁለት ሰአት ለመኝታ አልጋ ዉስጥ መግባት አለባቸዉ። ይህንኑ የህጻናት መረሃ-ግብር በቴሌቭዥን ከተከታተሉ በኻላ በርካታ ቤተሰቦች ህጻናቱ አልጋቸዉ ዉስጥ ለመኝታ ሲገቡ ህጻናቱ መጽሃፍ የማንበብ ባህላቸዉ እንዲዳብር በማለት ረጋ ብለዉ እንዲያደምጡ ልብ የሚስብ መጻህፍን እስኪያሸለቡ ያነቡላቸዋል።
በአገራችን ባህል በተለያዩ ብሄረሰቦች ተረት፣ እንቆቅልሽ ምሽት ላይ ከመኝታ በፊት ተሰባስቦ የማዉራት ባህል አለ፣ ይኸዉም ልጆች ለልጆች፣ ወይም አዋቂዎች ለልጆች ተረትንም ሆነ እንቆቅልሽን ይጠያየቃሉ። ነገር ግን ይህን አይነቱን የተረት ማዉራት ወይም የእንቆቅልሽ አጠያየቁ ስነ-ስርአት አንድ አይነት ነዉ ማለት ያስቸግራል፣ የሚሉን የባህል መድረክ የብዙ ግዜ ተሳታፊ መምህር መስፍን መሰለ ወደ አማራዉ ትግሪዉ እንዲሁም ደግሞ ኦሮሞዉ አካባቢ እንቆቅልሽ ወይም ተረት ማዉራት ቀንም ሆነ ምሽት ላይ ይፈቀዳል፣ ወደ ሲዳማ የሄድን እንደሆነ ግን ቀን ቀን ተረት ወይም እንቆቅልሽ የመጠያየቅ ባህል የለም።
«ምክንያቱም ቀን ቀን ተረት ወይም የእንቆቅልሽ ወግ የተጀመረ ከሆነ ሰዎች ስራቸዉን መስራታቸዉን ትተዉ ሊዘናጉ ስለሚችሉ ቀን ቀን በፍጹም ተረት ማዉራት የተከለከለ ነዉ» ሲሉ ይገልጻሉ ባንጻሩ በአማራዉ በትግሪዉ እንዲሁም በኦሮሞዉ ህብረተሰብ አካባቢ በአረሞ በአጨዳ፣ በሌሎችም የስራ መስኮች ተረት ወይም እንቆቅልሽ መጠያየቅ የተለመደ ነዉ» ሲሉ ይገልጻሉ።
ተረት ወይም እንቆቅልሽ በአገራችን ሰዎች ለመዝናናት እና ለማስተማር የዘየዱት ዘዴ ነዉ። በሌላ በኩል የዘመናዊ ቴክኖሎጂ እያደገ በመጣ ቁጥር ተረት የማዉራት እንቆቅልሽ የመጠያየቁ ሁኔታ በሌሎች ነገሮች ሲተካ ይታያል። ለምሳሌ እንደ ስፖርት እና ፊልም የመሳሰሉት ነገሮች ተጠቃሾች ናቸዉ። ይህ ባህላዊ የማስተማርያ ዘዴ በዘመናዊ መተካቱ ሊያስከትል የሚችለዉ ጉዳት ምን ይሆን መምህር መስፍን መሰለ በመልሳቸዉ «እንቆቅልሽና ተረት ሰዎች ከራሳቸዉ ባህል ተነስተዉ አካባብያቸዉ ያለዉን ገጠመኝ መሰረት በማድረግ የፈጠሩት የማስተማርያ ባህላዊ መሳርያ ነዉ። እነዚህን ማወቅ ደግሞ አንድ ህጻን ወይም ወጣት በህብረተሰቡ ዉስጥ ያለዉን ማህበራዉ ኢኮነሚያዊ ግንኙነት እንዲሁም ህብረተሰብ ዉስጥ ያለዉን የመብት እና የፍትህ ጉዳይ የሚገነዘብበት ነዉ። ያደግሞ ይላሉ መምህር መስፍን መሰለ ወጣቱ የራሱን ባህል እንዲያከብር በራሱ እምነት እንዲኖረዉ እድል ይፈጥርለታል። የራሱን ማንነት በዉል አዉቆ በራሱ በመተማመን ከሌላዉ ህብረተሰብ ጋር ግንኙነት ለማድረግ ትልቅ እርዳታን ይሰተዋል።»

Kind schläft glücklich im Bett
ምስል picture-alliance / maxppp

አዜብ ታደሰ