1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የጀርመኑ የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ማኅበር ኢትዮጵያን አወደሰ  

ዓርብ፣ መጋቢት 21 2010

የኢትዮጵያን የጠቅላይ ሚንስትርነት ሥልጣን ይይዛሉ ተብለዉ የሚጠበቁት ዶክተር አብይ አሕመድ የሐገሪቱን ምጣኔ ሐብት ለማሳደግ የሚደረገዉን ጥረት እንዲያጠናክሩ ጀርመን የሚገኘዉ የአፍሪቃ የኤኮኖሚ ማኅበር ጠየቀ።ማሕበሩ ኢትዮጵያ በኤኮኖሚዉ ዘርፍ አመርቂ ዉጤት አሳይታለች ሲልም አወደሷል።

https://p.dw.com/p/2vDrz
Afrika-Verein der deutschen Wirtschaft
ምስል picture-alliance/dpa/L. Schulze

«የዶክተር አብይ መመረጥ ለመዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች እፎይታን ፈጥሮአል»

 

መቀመጫዉን በርሊን እና ሃምቡር ከተማ ያደረገዉ የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ማኅበር ትናንት ባሰራጨዉ ጋዜጣዊ መግለጫ ዶክተር አቢይ አህመድ የምስራቅ አፍሪቃዊቱን ሃገር የኤኮኖሚ እድገት እንደሚያጠናክሩ ተስፋ አንዳለዉ አስታዉቋል።

የዶክተር አቢይ አህመድ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆኖ መመረጥን ተከትሎ በጀርመን የሚገኘዉ የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ማኅበር ባወጣዉ መግለጫ በኢኮኖሚ እድገት እያሳዩ ከሚገኙ የአፍሪቃ ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ እድገትን ያስመዘገበች ያለች ሃገር ሲል ጠቅሶአታል። የማኅበሩን ሊቀመንበር ስቴፋን ሊቢንግን የጠቀሰዉ መግለጫዉ በሃገሪቱ የሚታየዉ አስተማማኝ ያልሆነዉ የፖለቲካ ሁኔታ እስካሁንም መቀጠሉን እና ባለፉት ወራቶች በሃገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የታየዉ ግጭትና ተቃዉሞ  በዲፕሎማሲ ግንኙነቱ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮአል ብሎአል።

ከኢትዮጵያ ጋር በሚደረገዉ የኤኮኖሚ ልዉዉጥ እና ትብብር ላይም እንቅፋት መሆኑንም ተመልክቶአል። የጀርመን አፍሪቃ ኤኮኖሚ ማኅበር የአፍሪቃ ሃገራትን ብቻ ሳይሆን የአዉሮጳንም ሃገራት ያጠቃለለ ነዉ፤ ከተመሰረተም 80 ዓመት እንደሞላዉ የተናገሩት በጀርመን አፍሪቃ የኤኮኖሚ ማኅበር የፕሮጀክት ኃላፊ ጀርመናዊ- ኢትዮጵያዊት ማራያ ፍፁም ፈቃዱ የዶክተር አብይ መመረጥ ለጀርመን መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች እፎይታን ፈጥሮአል፤ ብለዋል።

የአፍሪቃ የኤኮኖሚ ማኅበር ሊቀመንበር ስቴፋን ሊቢንግ ማኅበራቸዉ ባወጣዉ መግለጫ ላይ ለኤኮኖሚ እድገት መሰረቱ ሠላም  እና መረጋጋት እንደሆን አስምረዉበታል። ማራያ ፍፁም ፈቃዱ በኢትዮጵያ ቢሮክራሲዉ ለባለሐብቶች አስቸጋሪ ሁኔታ መፍጠሩን አልደበቁም።  በማኅበሩ የምስራቅ አፍሪቃ ጉዳዮችን እንደሚከታተል የተናገሩት በጀርመን አፍሪቃ የኤኮኖሚ ማኅበር የፕሮጀክት ኃላፊ ማራያ ፍፁም ፈቃዱ ማኅበሩ የአፍሪቃ ባለስልጣናትን እና ባለሃብቶችን እንዲሁም የጀርመን መዋለ ንዋይ አፍሳሾችን እንደሚያስተዋዉቅ እና ኢትዮጵያ በኤኮኖሚ ትብብሩ ብዙ ተስፋ የተጣለባት መሆኑን ተናግረዋል። የማኅበሩ ሊቀመንበር ስቴፋን ሊቢንግ ጠቅሶ መግለጫዉ እንዳስቀመጠዉ ኢትዮጵያ በ 27 ዓመት ዉስጥ ለመጀመርያ ጊዜ የኦሮሞ ፖለቲከኛን ለጠ/ሚ ማዘጋጀትዋ የኤኮኖሚ ልዉዉጡን ለማጠናከር የሚረዳ፤ ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ የመራ ነዉ ሲሉ ተናግረዋል።  በተለይ በጨርቃ ጨርቅ ምርቷ እድገትን ያሳየችዉ ኢትዮጵያ ለኢንዱስትሪ ምርቱ የከባቢ ሁኔታዎችን ያገናዘበ የኢንዱስትሪ ፓርክ መገንባትዋንም የጀርመን አፍሪቃ ኤኮኖሚ ማኅበር ባወጣዉ መግለጫ አትቶአል።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ