1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመኑ የዉኃ ስርጭት እና አያያዝ በዓለም ቅርስ ማህደር

ዓርብ፣ ሐምሌ 5 2011

በጀርመኗ ከተማ አዉግስቡርግ ከ 800 ዓመት በላይ የሆነዉ የከተማይቱ የውኃ ማስተላለፊያ ስርዓት ቦዮች፣ፏፏቴዎች፣እና በርካታ ድልድዮች ብሎም በዉኃ ላይ የተመሰረተ መሰረተ ልማትን ያካትታል ። የከተማዋ የዉኃ ዝርጋታ አጠቃቀም 22 ቦታዎች በጥበቃዉ መዝገብ እንዲካተቱ ሆንዋአል። የኢትዮጵያዉ የላሊበላ ዉቅር አብያተ ክርስትያናት ጉዳይም ርዕስ ነዉ።

https://p.dw.com/p/3LvG9
Historische Augsburger Wasserwirtschaft
ምስል picture-alliance/dpa/S. Puchner

የጀርመኑ የዉኃ ስርጭት እና አያያዝ በዓለም ቅርስ ማህደር

ለአስር ቀናት የተካሄደዉ 43 ኛዉ የተባበሩት መንግሥታት የትምሕርት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት «ዩኔስኮ» ዓመታዊ ጉባዔ ላይ በጀርመኗ ከተማ አዉግስቡርግ ከ 800 ዓመት በላይ የሆነዉ የውኃ አያያዝ እና የዉኃ ስርጭት አጠቃቀም ስርዓቷ ብሎም በዉኃ ላይ የተመሰረቱ የልማት ተግባሮች  በዓለሙ ቅርስ መዝገብ መካተቱ የተሰጠበት ዉሳኔ ነዉ። የዉሳኔዉን መዶሻ ያነሱት የዩኒስኮ ምሁር፤ መዶሻዉን ጠረቤዛ ላይ ከማሳረፋቸዉ በፊት «ሌላ ተቃዉሞና አስተያየት ከሌለ፤ ዉሳኔ  ተራ ቁጥር 43 ፀድአል።» አሉ ።  አዘርባጃን  መዲና ባኩ ላይ በተካሄደዉ ጉባዔ ላይ የተገኙት የጀርመን ልዑካን ቡድን በርግጥ ይህ እሆናልን እንዳላሰቡ ተመልክቶአል። ምክንያቱ ደግሞ ጀርመን ጥንታዊዉን የዉኃ ስርጭት እና አጠቃቀም ስርዓት በዓለሙ ለማስመዝገብ ከዛሬ ዘጠኝ ዓመት በፊት ጀምሮ ስትሞክር ስለነበር ነዉ። በእለቱ ዝግጅታችን በዓለም ቅርስነት ስለተካተተዉ ስለ ጀርመንዋ ከተማ ጥንታዊ የዉኃ ስርጭት አጠቃቀም ይዘን በባኩ ከተማ የነበሩ የኢትዮጵያ ተወካይን አነጋግረናል።

Historische Augsburger Wasserwirtschaft
ምስል picture-alliance/dpa/K.-J. Hildenbrand

የጀርመኗ ከተማ አዉግስቡርግ ከ 800 ዓመት በላይ የሆነዉ የውኃ አያያዝ እና የዉኃ ስርጭት አጠቃቀም ብሎም የዉኃ ልማት በዓለም ቅርስ ለያለምንም ማንገራገር መመዝገቡ ሲታወጅ ጀርመናዉያኑ የጉባዔዉ ተሳታፊዎች በርግጥ በደስታ መዝለላቸዉ ደስታ ብቻ ያመጣዉ ሳይሆን ሲጨነቁበት የነበረዉ ነገር ዉጤት አግኝቶ እፎይታን ስላስገኘላቸዉም ጭምር እንጂ። ከ 800 ዓመት እድሜ ያለው የከተማይቱ የውኃ ማስተላለፊያ ስርዓት ቦዮች፣ፏፏቴዎች፣እና በርካታ ድልድዮች ብሎም በዉኃ ላይ የተመሰረተ መሰረተ ልማትን  ያካትታል። 2 ሺህ ዓመት እድሜ እንዳላት የሚነገረው እና በደቡብ ጀርመኑ በባቫሪያ ግዛት የምትገኘው የአውግስቡርግ ከተማ የውሐ ስርዓት ከመካከለኛው ዘመን አንስቶ በንጽህ የመጠጥ ውሐ አቅርቦት እና በፍሳሽ ማስወገድ አገልግሎቱ ይታወቃል። በከተማይቱ ከ500 በላይ ድልድዮች ይገኛሉ። የከተማይቱ መሐንዲሶች በግድብ ግንባታ ውኃን በአካባቢው ከሚገኙ ወንዞች በመጥለፍ እና ለልዩ ልዩ አገልግሎቶች በማዋል ከአውሮጳ የተመሰከረላቸው የመስኩ ባለሞያዎች መሆናቸው ተዘግቧል። 42ኛዉ የዩኔስኮ ጉባዔ የተካሄደዉ ባህሪን ነበር ዘንድሮ ባኩ ላይ ነዉ እኛም በጉባዔዉ ላይ ተገኝተን ነበር ሲሉ የነገሩን በፓሪስ ፈረንሳይ የሚገኘዉ በኢትዮጵያ ቋሚ መልክተኛ ጽ/ቤት ዉስጥ የባህል ጉዳይ ዋና ተጠሪ ፊበን ተወልደ ናቸዉ። ፊቨን የዓለም የቅርስ ጥበቃ ኮሚቴ ለቅርስ ጥበቃ ትኩረት ለመስጠት በየዓመቱ ጉባዬ እንደሚቀመጥ ተናግረዋል።

« የዓለም ቅርስ ኮሚቴ በየአመቱ ነዉ የሚሰበሰበዉ። 21 ኮሚቴ አሉት። እነዚህ 21 የኮሚቴ አባላት የሚወያዩት በአንደኛ ደረጃ በድርጅቱ የቅርስ ጥበቃ መዝገብ ዉስጥ የተመዘገቡ ቅርሶች ላይ አደጋ አለ ሊታደስ የበለጠ ጥበቃ ያስፈልገዋል የሚል ጥቆማ አልያም መረጃ ለድርጅቶ ደርሶ ከሆነ በዚህ ርዕስ ላይ ዉይይት ይደረጋል። ከዚህ በተጨማሪ ሃገራት ጥንታዊ ታሪካዊ ነዉ ያልዋቸዉን እና በቅርስ ጥበቃ ማህደሩ እንዲመዘገቡላቸዉ በጠየቁዋቸዉ ጉዳዮች ላይ ዉይይት ያደርጋሉ። የሃገራቱ ቅርሶች በቅርስ ጥበቃ ማህደሩ ከመመዝገቡ በፊት የቅርስ ጥበቃ ድርጅቱ ገለልተኛ ምሁራን ሃገሪቱ ዉስጥ ሄደዉ የቅርሱን ታሪካዊነት እድሜ በማጤን ለኮሚቴዉ አሉታዊ አልያም አዎንታዊ መጃን ይሰጣሉ። ከዝያ ነዉ የቅርስ ጥበቃዉ ኮሚቴ 21 አባላት ይመዝገብ አልያም ይቆይ ብለዉ ዉሳኔን ያስተላልፋሉ።»

የጀርመኗ ከተማ አዉግስቡርግ ከ 800 ዓመት በላይ የሆነዉ የውኃ አያያዝ እና የዉኃ ስርጭት አጠቃቀም ስርዓት በዓለም ቅርስ መዝገብ ለመካተቱ ዉሳኔዉን በቀጥታ ስርጭት ሲከታተል ከነበረ የዓለም ሕዝብ መካከል የጀርመንዋ ከተማ አዉግስቡርግ ነዋሪና ከንቲባዋ ግን ደስታቸዉ ከሁሉ ከሁሉ የላቀ ነበር። ከመኖርያ ቤታቸዉ የቀጥታ ስርጭቱን ከመኖያ ቤታቸዉ በቀጥታ ስርጭት ሲከታተሉ የነበሩት እና ከዉሳኔዉ በኋላ ደስታቸዉን መቆጣጠር ያቃታቸዉ የከተማዋ ከንቲባ ኩርት ክሪብል እንደሚሉት ከ 500 ዓመት በላይ የሆነዉ የከተማዋ የዉኃ ዝርጋታ አጠቃቀም በዓለሙ የቅርስ ጥበቃ መዝገብ እንዲመዘገብ ከዘጠኝ ዓመት በላይ ጠብቀናል።

Historische Augsburger Wasserwirtschaft
ምስል DW/A. Kirchhoff

«እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል፤ የዉኃ አጠቃቀም እና አያያዝ ስርዓቱ በዓለም የቅርስ ጥበቃ ድርጅት ለመመዝገብ ይሁንታ ያግኝ አያግኝ ስንል ዉጥረት ይዞን ነበር፤ ትልቅ እፎይታ ነዉ። በማኅበራዊ መገናኛ ሲሰራጭ የነበረዉን ዉሳኔ የተከታተልኩት በቀጥታ ነበር ። ዉሳኔዉ ሲሰራጭ እና የአዉግስቡርግ የዉኃ አጠቃቀም ስርዓት በዓለሙ የቅርስ ጥበቃ ድርጅት ማኅደር ስር ተካቶአል ብሎ መዶሻ ሲመታ የነበረዉ ስሜት እጅግ አስደሳች ነበር»

የከተማዋ የዉኃ ዝርጋታ አጠቃቀም 22 ቦታ ዎች በጥበቃዉ መዝገብ እንዲካተቱ መሆኑ ተመልክቶአል። በባኩ በተካሄደዉ ጉባዔ የጀርመንዋን ከተማ ጥንታዊ የዉኃ መስመር ዝርጋታ በቅርስ ማኅደር ለማስገባት ምንም አይነት ክርክር እንዳልተካሄደና በተለይ ቻይና፤ አዘርባጃን እና ቱኒዝያ በዉሳኔዉ እጅግ መደሰታቸዉን መግለፃቸዉ ተመልክቶአል።  በዓለማችን የንጹኃ አጠቃቀም ምን ያህል አስፈላጊነቱን የሚሳይ ነዉም ተብሎለታል። በቅርስነት እንዲመዘገብም ሊበቃ የቻለበት ዋና  ምክንያት ዓለማችን የንጹህ ዉኃ አጠቃቀም ፤ የዉኃ ንጽህና ዋንኛ እና አስፈላጊነቱ እየጎላ በመጣበት በአሁኑ ወቅትም መሆኑን የአዉግስቡርግ ከንቲባ ኩርት ክሪብል ተናግረዋል።  

« ዛሬ ስለ ዉኃ ርዕስ ሲነሳ ጦርነት እና ሰላም የሚለዉን ርዕስ የሚወስን መሆኑን እናዉቃለን። አሁን የከባቢ አየር ለዉጥ በሚታይበት ዓለማችን ዉኃ ወሳኝ ሚናንን ይጫወታል። የዉኃ ኃይል ምንጭ ፤ ንጹሕ የመጠጥ ዉኃ፤ የዉኃ ንጽሕና አጠባበቅ የመሳሰሉትን ሁሉ ያጠቃልላል። የአዉግስቡርጉ  የዉኃ አጠቃቀም ስርዓት ይህን ሁሉ ያካተተ ነዉ ፤ ብሎም የዉኃ ኤኮኖሚያዊ አጠቃቀምን ሁሉ ይዞአል። የአዉግስቡርግ ጥንታዊና እጅግ የዳበረ የዉኃ አጠቃቀም ዘዴ ለዓለም በማሳየት ዘዴዉን መጭዉ ትዉልድ እንዲሰራበት እናደርጋለን»

የከተማዋ ነዋሪዎችም ቢሆኑ በዩኔስኮ አዎንታዊ ዉሳኔ ደስታቸዉን ገልፀዋል።  

« በዓለም የቅርስ መዝገብ መካተቱን መስማት እጅግ ያስደስታል። በዓለም ቅርስ የተመዘገበ ጥንታዊ እና የሰለጠነ  የዉኃ አጠቃቀም ባለበት ከተማ በመኖሬ እኮራለሁ። ምክንያቱም የአዉግስቡርግ ከተማ የመጠጥ ዉኃ ዝርጋታ በዓለማችን ብቸኛዉ በመሆኑ ነዉ»

Aserbaidschan Baku | UNSESCO 43 rd World Heritage Committee Meeting
ምስል UNESCO/Tewolde Feven

« የምህንድሳ ባለሞያ ነኝ። ይህ የአጠቃቀም ዘዴ ምጡቅ ነዉ ሲባል ምን እንደሆን በደንብ እረዳለሁ» « ይህ የዓለም ዉሳኔ አዉግስቡርግን ይበልጥ ታዋቂና ተፈላጊ  ያደርጋታል »

ዘንድሮ ባኩ ላይ በተካሄደዉ ጉባዔ ላይ እኛ ተገኝተን ነበር ሲሉ የነገሩን በፓሪስ ፈረንሳይ በሚገኘዉ በኢትዮጵያ ቋሚ መልክተኛ ጽ/ቤት ዉስጥ የባህል ጉዳይ ዋና ተጠሪ ፊቨን ተወልደ ናቸዉ። 21 የኮሚቴ አባል ሃገራት የተካተቱበት የዓለም ቅርስ ማዕከል፤ በየዓመቱ በዙር የኮሚቴ አባላቱ ሃገራት የዓለም ቅርስ ጉባዔን በየሃገሮቻቸዉ ያስተናግዳሉ። በወቅቱ ኢትዮጵያ የኮሚቴዉ አባል ባትሆንም የኮሚቴ አባል ለመሆን በእጩነት መቅረብዋን ፊቨን ደስአለኝ ተናግረዋል። የዓለም ቅርስ ድርጅት ኮሚቴ ለመሆን ከአፍሪቃ ከአረብ ሃገራት በኮታ እንደሚደለደል የተናገሩት ፊበን ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የኮሚቴ አባል እንደነበረችና ሃገራቱ በሙሉ በዙር እንደሚደርሳቸዉ ገልፀዋል።

«ኮታ አለዉ ። እያንዳንዱ የኮሚቴ አባል ኮታ አለዌዉ። አራት አፍሪቃ ሃገራት አሉ። አረብ ሃገራትም ያራሳቸዉ የሆነ ኮታ አላቸዉ። ከሃያ አንዱ የኮሚቴ አባላት መካከል አራቱ የአፍሪቃ ሃገራት ናቸዉ። » በዚህ ወቅት አራቱ አፍሪቃ ሃገሮች ታድያ የትኞቹ ናቸዉ?

«ቡርኪናፋሶ ፤ ዩጋንዳ ታንዛንያ እና አንጎላ ናቸዉ።  በጎርጎረሳዉያኑ 2010 ላይ ኢትዮጵያ የኮሚቴዉ አባል ነበረች። ሃገራቱ የኮሚቴ አባል መሆን የሚችሉት ለአራት አመት ነዉ። በዚህም ምክንያት ዘንድሮ ኢትዮጵያ የኮሚቴ አባል አልነበረችም። ሃገራት ከኮሚቴ አባልነት ሲወጡ ዳግም የኮሚቴ አባል መሆን የሚችሉት ሁለት ተርም ጠብቀዉ ነዉ ያ ማለት ስምንት ዓመት መሆኑ ነዉ።» 

የኢትዮጵያን ቅርስን በተመለከተ የተነገረ ነገር ነበር?

« በኢትዮጵያ ጉዳይ አልነበረም ። ይሁንና የላሊበላ ዉቅር አብያተ ክርስትያን መጠለያ ተብሎ የተሰራዉ ማማ ብዙ ዉዝግቦችን አስነስቶ እንደነበር ይታወቃል። ከዚህ በፊት መጠለያዉ ቤተ ክርስትያኑን ላይ የመሰንጠቅ አደጋ ደቅኖአል እና ይነሳ የሚል ጥያቄዎች ተነስቶ ነበር። ከዚያም በቅርቡ በእድሳት ጉዳይ ላይ ይሆናል በተባለዉ ከፈረንሳይ ጋር በሚካሄደዉ ፕሮጀክት ላይ ዩኔስኮ ባለፈዉ የጎርጎረሳዉያን ዓመት በጉዳዩ ምሁራን ወደ የላሊበላ ዉቅር አብያተ ክርስትያናትን ሄደዉ እንዲያዩ እና እንዲገመግቡ ወደ ቦታዉ ልኮ ነበር። መጠለያዉ የተሰራዉ ለአስር ዓመት ነበር ፤ አስር ዓመት አልፎታል። በዚህም ምክንያት መነሳት ይችላል ብለዉ ግምገማ ሰጥተዉ ነበር ይሁንና መጠለያዉ ከመነሳቱ በፊት መሰራት ያለባቸዉ ቅድመ ዝግጅቶች እንደሚያስፈልጉ ቅርሱ እንዳይጎዳ የእድሳት ስራዎች እንዲከናወን፤ መጠለያዉ ሲነሳም ምን አይነት ጥንቃዌ ሊደረግ እንደሚገባ የዩኔስኮ ልዑክ ቡድን ግምገማ ሰጥቶአል። የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ወደ ፈረንሳይ በመጡ ወቅት ፕሬዚደንት ማርኮን በላሊበላዉ ጉዳይ እንዲረዱን በጠየቁት መሰረት የፈረንሳይ መንግሥት ኢትዮጵያን ለመርዳት ፕሮጀክቱን ጀምሮአል። ለጊዜዉ ስራቸዉን ከመጀመራቸዉ በፊት ብዙ ጥናት እንደሚያስፈልዉ ተነግሮ ምሁራኑ ጥናት ላይ ነዉ የሚገኙት።»   

Historische Augsburger Wasserwirtschaft
ምስል DW/A. Kirchhoff

43 ኛዉ በተባበሩት መንግሥታት የትምሕርት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት «ዩኔስኮ» ዓመታዊ ጉባዔ ከ 800 ዓመት በላይ የሆነዉን የጀርመኗን ከተማ አዉግስቡርግ የውኃ አያያዝ እና የዉኃ ስርጭት አጠቃቀም ስርዓት ብቻ ሳይሆን በዓለሙ ቅርስ መዝገብ ያካተተዉ ፤ በቅርስ መዝገቡ የኢራቅ  ጥንታዊት ከተማ ባቢሎንንም ተመዝግቧል። ከዛሬ 4 ሺህ ዓመት በፊት ስሟ የተጠቀሰው ባቢሎን ናቡከደነጾር እና ሃሙራቢንን ጨምሮ የበርካታ ኃያላን መሪዎች መናገሻ ከተማም ነበረች። አብዛኛው የከተማይቱ ክፍል ግን በዩናይትድ ስቴትሱ  የኢራቅ ወረራ ወቅት ከባድ ጉዳት እና ዝርፊያ ደርሶበታል።  

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ