1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመኑ ፕሬዝዳንት የአፍሪቃ ጉብኝት

ሰኞ፣ ሚያዝያ 2 1998

የጀርመኑ ፕሬዝዳንት Horst Köhler የአፍሪቃ ጉብኝታቸውን እንደቀጠሉ ነው።

https://p.dw.com/p/E0dt
Horst Köhler
Horst Köhlerምስል picture-alliance / dpa/dpaweb

ጉብኝታቸውን በሞዛምቢክ የጀመሩት Köhler ከዚያም ወደ ማደጋስካር አቅንተው አሁን የጉብኝታቸው የመጨረሻ አገር የሆነችው ቦትስዋና ይገኛሉ።Köhler ወደ እነዚህ አገራት የተግዋዙት አስራ አምስት የንግዱን ማህበረሰብ አባላት በመምራት ነው።ይህም ፕሬዝዳንቱ ከነዚህ አገራት ጋር የኢኮኖሚ ግንኙነት ለመፍጠር ከፍተኛ ትኩረት እንደሰጡ አመልካች ነው ።ፕሬዝዳንቱ የሄዱባቸው ሞዛምቢክ ማዳጋስካርም ሆነች ቦትስዋና ከጀርመን ጋር የጠበቀ የኢኮኖሚ ግንኙነት እንዲኖራቸው ይሻሉ ከፕሬዝዳንቱ ጋር አብራ የተግዋዘችው የዶይቼቬለዋ ኡተ ሼፈር እንደዘገበችው የጀርመኑ ፕሬዝዳንት ሆርስት ኮለር የጎበኙዋቸው ሞዛምቢክና ማደጋስካርም ሆኑ አሁን የጉብኝታቸው መጨረሻ ያደረግዋት ቦትስዋና በተለያየ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ነው የሚገኙት።እነዚህ ሀገራት የኢኮኖሚ ተሀድሶ እያደረጉ ነው።ይሁንና ጀርመን እስካሁን ከሶስቱም የአፍሪቃ አገራት ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት እከዚህም ነው።የአሁኑ የፕሬዝዳንት ኮለርና የጀርመን የንግድ ማህበረሰብ ልዑካን ጉብኝት ዓላማም ባለሀብቶቹ የየአገሮቹን ተጨባጭ ሁኔታ በቅርብ አይተው ገበያ እንዲያፈላልጉ ነው።በአፍሪቃ የጀርመናውያንን የኢኮኖሚ ጥቅም የሚያስጠብቀው ማህበር የበላይ ሀንስ ማየር ኤቨርት በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን እንደሰጡት የጀርመን ባለሀብቶች በአንድ አቅጣጫ ብቻ መመልከታቸውን ትተው በአፍሪቃም ሊያገኙ የሚችሉትን የገበያ ዕድል መሞከር አለባቸው።
ድምፅ
“የልኡካኑ ፍላጎት በመጀመሪያ አገራቱን ማወቅ መመልከት ነው። በዚህ ወቅት የትኛው ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል የሚለውንም ያጤናሉ። ማንኛውም ሰው ዕንቁላሎቹን በተለያዩ ጎጆዎች ማስቀመጥ መቻል አለበት።ይህን ወደ ንግዱ ህብረተሰብ ስናመጣው በሌላውም አቅጣጫ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል።ይህ ዓይነቱ ሙከራ አንዳንዴ ላያዋጣ ይችላል የሚል ስጋት ቢኖረውም በሌላ በኩል አትራፊ አሸናፊ መሆንም ሊያጋጥም ይችላል።”
ፕሬዝዳንቱ በመጀመሪያ የጎበኙዋት ሞዛምቢክ ለአስራ አራት ዓመታት የርስ በርስ ጦርነት የተካሄደባት አገር ናት። ከአስሩ የአለም ድሀ አገራት አንድዋ የሆነችው የሞዛምቢክ የኢኮኖሚ መሰረትዋ ግብርናና የአሳ ምርት ነው።ኢኮኖሚዋ ደካማ በመሆኑም በሀገሪቱ ያን ያህል አጥጋቢ ውጤትና ለውጥ አይታይም ።ያም ሆኖ በሞዛምቢክ ለውጭውም ሆነ ለአገሪቱ ባለሀብት ገበያ ሊኖር ይችላል ይላሉ ማየር ኤቨርት
ድምፅ
“የወጣት ደቡብ አፍሪቃውያኑን ባለሀብቶችም ሆነ የነባሮቹን ፖርቱጋሎች የኢኮኖሚ ተሳትፎ ስናይ ምንም ዓይነት ፉክክር የለም።ሆኖም በዚህች አገር ንግድን ማስፋፋት የሚያስችል አቅም አለ። ገበያውን በህጋዊ መንገድ በዕጅ የማስገባቱ ዕድል አለ።ግን ባለሀብቱ ብዙ ሀይል ይዞ መምጣቱ አስፈላጊ ጉዳይ ነው።
ፕሬዝዳንት ኮለር የጎበኙዋቸው የሌሎቹ የአፍሪቃ አገራት የማደጋስካርና የቦትስዋና ኢኮኖሚ ከሞዛምቢክ የተሻለ ነው።በማዳጋስካር የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ራቫሎማናና ጠንካራ የኢኮኖሚ ተሀድሶ እንዲካሄድ አድርገዋል።ይህም አጠቃላዩን ማህበራዊ ሁኔታ ለመቀየር፣የኢኮኖሚውን ዕቅድና መዋቅር ለማስተካከል እንዲሁም ቢሮክራሲውን መልሶ ለመገንባት አስፈላጊ ነው።በሀገሪቱ የመሰረተ ልማት ግንባታ እየተፋጠነ ነው።የመንገድ ስራ ፣ውሀና መብራትን የማዳረሱ ተግባርም እንዲሁ።የቱሪዝሙ ዕንቅስቃሴም መልካም ነው።በማዳጋስካር ሁኔታዎች እየተመቻቹ መሆናቸውን ነው ከፕሬዝዳንቱ ጋር የተግዋዙት የሀምቡርግ ንግድ ምክርቤት ምክትል ሊቀመንበርና የንግዱ ማህበረሰብ አባል ሚሻኤል ኦቶ የተናገሩት።
ድምፅ
“ማደጋስካር ውስጥ የምንንቀሳቀስ የጀርመን ባለሀብቶች ምርቶቻችንን ከማዳጋስካር ወደ ጀርመን እንልካለን ማዳጋስካር ቀልጣፋ ሊባል የሚችል ኢንዱስትሪ አላት።በተለይ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪው፤ ሞዛምቢክ ውስጥ ግን የጨርቃ ጨርቁ ኢንዱስትሪ እንደ ማደጋስካር በስፋት አልተያዘም።ይሁንና ሞዛምቢክም ብትሆን መልካም ጎዳና ላይ ናት።”
የጀርመኑ ፕሬዝዳንት የጉብኝታቸው ማሳረጊያ ያደረጉዋት ቦትስዋና የኤች አይ ቪ ወረርሽኝ ከመሰራጨቱ አስቀድሞ በዓለም በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትዋ የምትጠቀስ አገር ነበረች። የልማት ዕርዳታ ጥገኝነት ካቅዋረጠች ቆይታለች።አገሪቱ በአልማዝ ሀብትዋ ስምዋ የገነነ ነው።አሁን በዚህች አገር የሚፈለገው የኢኮኖሚዋን ምንጭ ማስፋት ነው።