1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመናዊው ጠፈርተኛ የምርምር ጉዞ

ሐሙስ፣ ግንቦት 21 2006

ትምህርታቸው የአፈርና ቋጥኝ ፊዚክስ ፤በተለይም የእሳተ ገሞራ ጥናት ነው። ይሁንና ዛሬ ፣ እመኻል አውሮፓ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 21 ሰዓት ከ 56 ደቂቃ ለምርምር ፣ ከባይኖኩር ካዛኽስታን ፤ በሩሲያ ሶዩዝ የጠፈር መንኮራኩር ወደ ዓለም አቀፉ

https://p.dw.com/p/1C8dI
ምስል AP

የምርምር ማካሄጃ የጠፈር ጣቢያ ይጓዛሉ። ። በዚያም ለ ስድስት ወራት ገደማ ምርምር ካደረጉ በኋላ ፤ በሚመጣው ዓመት በኀዳር ወር መግቢያ ላይ ይሆናል ወደ ምድር የሚመለሱት። የ38 ዓመቱ ጎልማሳ ጀርመናዊው ጠፈርተኛ አሌክሳንደር ጌርስት!

ISS Astronauten Gerst und Wiseman und Surajew 27.05.2014
ምስል Reuters

በዳርምሽታት ከተማ ፣ የአውሮፓ የሳቴላይት ጉዞ መቆጣጠሪያ ማዕከል የተገኙት ፣ ፕሬዚዳንት ዮአኪም ጋውክ በቪዲዮ መልእክት ለጠፈርተኛው፤ በሰላም ደርሰህ ለመመለስ ያብቃህ! በማለት መልካም ዕድል ተመኝተዋል። አያያዘውም ፣ አርአያነት ባለው መልኩ ወጣቶች፤ ይህን የመሰለ ኀላፊነት ሲወስዱ ማየት የሚያሥመሰግን ነው በማለት የጌርስትን ደፋርነት አድንቀዋል። በዛሬው ዕለት ፤ ከብሔራዊ ቡድናችን ይልቅ በአንተ ነው የምንኮራው! ሲሉም አወደሰዋቸዋል።

«ቬዘር ኩርየር» በተሰኘው ጋዜጣ ላይ ፣ ዩዑርገን ቬንድለር የተባሉት ሐያሲ ባቀረቡት ሐታታ ላይ እንዳሉት፣ በፕላኔታችን ፣ ብዙ ችግሮች በመኖራቸው፤ ወደ ሕዋ የሚደረገውን ማንኛውንም ጉዞ፣ ቅጥ ያጣ አድርገው የሚመለከቱ ብዙዎቶች ናቸው ። የሕዋ ምርምር ተጨባጭ የሆነ ጠቀሜታ አለው የሚሉም ጥቂቶች አይደሉም። ቀላል ፤ እጅግ ጠንካራ የብረታ ብረት ዓይነቶች ፣ ወይም ግለትን የበለጠ መቋቋም የሚችሉ ነገሮችን ማቅረብ የተቻለው ከኅዋ ጋር በተደረገ ምርምር ፤ ተያይዞ ወይም አንዱ በሌላው ተደግፎ ነው። የሕዋ ምርምርና ጎዞ ባይኖሮ ኖሮ በሳቴላይት የሚሠራ ቴሌቭዥን የሚታሰብ አይሆንም ነበር። በሳቴላይት አቅጫጭ ማመላከቻው ብልሃትም ሆነ መሣሪያም ባልቀረበ ነበር። በዚህ ረገድ፤ ሥነ ቴክኒክ ላሳየው ዕድገትም ፤ የሕዋ ጉዞ ነክ ምርምር አስተዋጽኦ ማበርከቱ የማይታበል ነው። ጠፈርተኛ አሌክሳንደር ጌርስት ወደ ዓለም አቀፉ የሕዋ የምርምር ጣቢያ ለመጓዝ መዘጋጀታቸው ትልቅ ከበሬታን ነው የሚያሰጣቸው።

እ ጎ አ ከ 1819 እስከ 1898 የኖሩት ታዋቂው የጀርመን ደራሲ ሃይንሪኽ ቴዎዶር ፎንታን፣ በድንፋታና ቡከንነት መካከል ሌላ ሦስተኛ አለ። እርሱም ከህልውና ጋር የተያያዘው ደፋርነት ሲሉ መጻፋቸው የሚታወስ ነው።

የአፈርና ቋጥኝ ተመራማሪ የፊዚክስ ምሁር ፤ ጠፈርተኛ አሌክሳንደር ጌርስት፣ ለ 6 ወራት ባልተለመደ ቦታና ሁኔታ በሥራ (ምርምር) ጊዜያቸውን ሊያሳልፉ ቆርጠው ሲነሱ፤ በምድር ላይ የሰዎች ኑሮ እንዲሻሻል ፣ የጠፈሩ ምርምር ያግዛል ከሚል ጽኑ እምነት በመነሣት ነው ፣ ከሳይንስ ተመራማሪ ከዚህ የበለጠ መጠበቅም አስቸጋሪ ነው፤ እንደ ሐያሲ ዩርገን ቬንድለር አገላለጽ!

ዛሬ ማታ ወደ ሕዋ የሚጓዙት ጌርስት ራሳቸው የሚሣፈሩበት መንኮራኩር የሚመጥቅበት ጊዜ እየተቃረበ ሲመጣ ምን እንደሚሰማቸው ተጠይቀው ሲመልሱ እንዲህ ነበረ ያሉት።

ISS Internationale Raumstation
ምስል Nasa/dpa

«ቀኑ ደርሶ መንኮራኩር ውስጥ በመቀመጥ 26 ሚሊዮን የፈረስ ጉልበት ባለው መሣሪያ ውስጥ ተሳፍሮ የሚመጥቅበትን ቅጽበት፤ ደቂቃ -ሴኮንዱን መጠበቁ ልብ የሚሠቅል ሁኔታ ነው። ነገር ግንእዚህ ከተማ ውስጥ ከባልደረቦቼ እንደሰማሁት በሥራ መጠመድ ስላለ፤ የጉዞው ጉዳይ ያን ያህል የሚያስስብ አይደለም።»

ዛሬ ወደ ሕዋ የሚጓዙት ጀርመናዊው ጠፈርተኛ አሌክሳንደር ጌርስት፣ በኅዳር መግቢያ ላይ ወደ ምድር ከመመለሳቸው በፊት በዚያው በዓለምአቀፉ የኅዋ ምርምር ጣቢያ ውስጥ፣ 100 ያህል የተለያዩ የምርምር ዓይነቶችን ያከናውናሉ። ይሁንና ከባዱን የሳይንስ ምርምር ከመጀመራቸው በፊት ፣ ጀርመናዊው ጠፈርተኛ ልልጆች መልእክት ለማስተላለፍ ነው የተዘጋጁት። የዛሬዎቹ ዘመን ልጆች፤ ነገ እንደ መርከብ የምትቆጠረውን ፤ ምድርን(ፕላኔታችንን) በአግባቡ መቅዘፍ ይኖርባቸዋል። እያንዳንዱ ልጅ ባለው ዕውቀትም ሆነ ችሎታ እን ዲጠቀምም መክረዋል። ይህን ያሉትም ለዓለም አቀፉ የልጆች የአስቸኳይ ሁኔታ ርዳታ አቅራቢው ድርጅት«ዩኒሴፍ» ባቀረቡት የድጋፍ መግለጫ ላይ ነው። እ ጎ አ በ 2009 ቤልጅጋዊው ፍርንክ ደ ቪነ እና አምና ኢጣልያዊው ጠፈርተኛ ሉካ ፓርሚታኖ፣ ከዚያው ከሕዋው የቤተ ሙከራ ጣቢያ ሆነው ለ ዩ ኒ ሴ ፍ ማስታወቂያ ማሰማታቸው ተነግሮላቸዋል።

የዳርምሽታቱ የአውሮፓ የሳቴላይት መቆጣጠሪያ ጣቢያ ፣ የ 14 ሰው ሠራሽ ሳቴላይቶችን ተግባር በመቆጣጠር ላይ ነው የሚገኘው።

ወደ ጠፈር የሚላክ ሰው -ሠራሽ ሳቴላይት ተልእኮ አንዱ አስቸጋሪ የበረራ እርከን ሳቴላይቱ የተመደበለትን ምሕዋር የሚይዝበት ሁኔታ ነው። የፊዚክስ ምሁርና የሕዋ በረራ ኢንጂኔር ኤድ ትሮሎፕ ፣ ይህ ምድር ላይ እንዴት እንደሚመስል በቤተ ሙከራ ጣቢያ ላይ በማሳየት ሲያስረዱ ይህን ብለዋል።

«ሳቴላይት በሮኬት ከምድር ወደ ሕዋ ተተኩሶ፤ የስበትን ኃይል መጥቆ በማለፍ ሕዋ ላይ ምሕዋር ሲያዝ፣ ፣ ይህ የተልእኮው እጅግ ከባዱ ፈተና ነው። ሳቴላይቱ ኃይል ለማግኘት የፀሐይ ኃይል ማጠራቀሚያው ሰሌዳ ያስፈልገዋል። ስለዚህም በተቻለ ፍጥነት እንዲጓዝ ማድረግ ነው የሚኖርብን።»

Alexander Gerst
ምስል picture-alliance/dpa

ወደ ዓለም አቀፉ የኅዋ ምርምር ጣቢያ ለመጓዝ አሌክስንደር ጌርት፤ ከቶማስ ራይተር እና ሃንስ ሽሌገል ቀጥሎ 3ኛ ፣ ባጠቃላይ ወደ ሕዋ በመጓዝ 11ኛው ጀርመናዊ ጠፈርተኛ መሆናቸው ነው። ዛሬ አብረዋቸው ከሚጓዙት መካከል ፣ አንድ አሜሪካዊና አንድ ሩሲያዊ ጠፈርተኞች ይገኙበታል።

እዚህ ላይ ፤ በዩክሬይን ሳቢያ የተቃቃሩ የመሰሉት ዩናይትድ ስቴትስና ሩሲያ፤ የዓለም አቀፉን የሕዋ የምርምር ጣቢያ ተግባር ፈጽሞ እንደማያስተጓጉለው ነው ለማወቅ የተቻለው።

«በዓለም ውስጥ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ሳይንሳዊ ምርምር፣ በፖለቲካ የአቋም ልዩነት ሳቢያ አይሠናከልም » ሲሉ ያስገነዘቡት፤ የዩናይትድ ስቴትስ የበረራና የሕዋ መስተዳደር ዋና ኀላፊ ቻርለስ ቦልደን ናቸው። እርሳቸውም ይህን ያሉት፤ እ ጎ አ ከ 2020 በኋላ የጠፈሩን የምርምር ጣቢያ ተግባሩን እንዲቀጥል በበኩሌ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር አልስማማም ስትል ሩሲያ ባሳወቀች በሳምንቱ ነው። የጠፈር የምርምር ጣቢያውን ተግባር በማከናወን ከሚሳተፉት አባል ሃገራት መካከል ፣ ጃፓን ፤ አውሮፓ፤ ካናዳ እንዲሁም ዩናይትድ ስቴትስ ይገኙበታል። ስንቅ አመላላሽ የጠፈር መንኮራኩሮቿን ተግባር በመግታት ፤ ዩናይትድ ስቴትስ በሩሲያ ሶዩዝ የጠፈር መንኮራኩር ነው ስትመካ የቆየችው። ቦልደን እንዳሉት፣ በ ዩናይትድ ስቴትሱ «ናሳ» እና በሩሲያው «ሮስኮስሞስ» መካከል በዚህ ረገድ የተደረገው ትብብር ያላንዳች ሳንክ በመከናወን ላይ ነው የሚገኘው። ፕሮጀክቱ ሳይሰናከል ተግባሩን በመፈጸም ላይ ነው የሚገኘው።

ሩሲያ በተጨማሪ፤ ባለፈው ሰኞ፤ በሰላማዊው ውቅያኖስ ከሚገኘው ተንሳፋፊ መድረክ ፣ ለፈረንሳይ አንድ የመገናኛ ሳቴላይት በተሳካ ሁኔታ ማምጠቋ ታውቋል። አምና በጥር ወር ማለቂያ ገደማ በዚያው ቦታ ያደረገችው ሙከራ ከሽፎባት እንደነበረ አልታበልም። ሳቴላይት ወደ ጠፈር በማምጠቅ በዓለም ውስጥ የመጀመሪያቱ ሃገር የሆነችው የቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት ያሁኗ ሩሲያ ፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ፤ አልቀናት ብሎ በተደጋጋሚ ወደ ሕዋ የሚላኩ ሳቴላይቶችና አንዳንድ መሣሪያዎቿ የከሸፉበት ሁኔታ የሚታወስ ነው። ይሁንና መንኮራኩር የሚያመጥቁት ጣቢያዎቿ ይበልጥ አስተማማኝ በመሆናቸው፤ ብዙዎች አገሮች ዩናይትድ ስቴትስ ጭምር በትብብርም በክፍያም ከሩሲያ ጋር መሥራታቸውን እንደቀጠሉ ናቸው።

በዩናይትድ ስቴትስ ፤ በሩሲያና በጀርመን ፣ ስለ ሕዋ ጉዞአቸው 4 ዓመታት ዝግጅት ያደረጉት ጌርስት፤ የልጅነት ሕልማቸው እውን የሚሆንበት ቅጽበት መቃረቡን አስመልክተው --« በልጅነቴ፤ በአድናቆት ነበረ ሰማይንና የሰማይ አካላትን የምመለከት። በለጋ ወጣትነቴም ወላጆችን እጠይቅ ነበር። ወደዚያ እንዴት መሄድ ይቻላል? በዚያ የሚኖሩ ፍጡራን ይገኙ ይሆኝ!? ለሁለቱም ጥያቄዎች በኅዋ ላይ ወደምትገኘው የጠፈር ቤተ ሙከራ (ISS) በሚያደርጉት በረራና ቆይታም ቢሆን መልሱን አያገኙም። ከዋክብቱ እንዲህ ቅርብ አ,ይደሉምና! እጅግ በጣም ትንሽ የአንድ አፅቅ ያህል መጠጋታቸውን ግን ሊገነዘቡ ይችሉ ይሆናል።

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ