1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመንና የእስራኤል ግንኙነት 50 ኛ ዓመት

ማክሰኞ፣ ግንቦት 4 2007

ጀርመንና እሥራኤል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከመሠረቱ ልክ ዛሬ 5o ዓመት ሞላቸው ። ሁለቱ ሃገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እስኪመሠርቱ ድረስ ብዙ ዓመታት ወስዶባቸዋል ። ምክንያቱ ምን ይሆን ? የዛሬው አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን የግንኙነቱን መሠረትና ያለፈው የጀርመን ታሪክ በግንኙነት ላይ ያሳደረውን ተፅእኖ ይመለከታል ።

https://p.dw.com/p/1FOpi
Symbolbild Deutschland Israel Flaggen
ምስል picture alliance / dpa

ጀርመንና እስራኤል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመመሥረት የበቁት የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ ከሁለት አሥርት ዓመታት በኋላ ነው ፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በናዚ ጀርመኑ በሂትለር ዘመነ መንግስት 6 ሚሊዮን የተገመቱ ይሁዲዎች በመጨፈጨፋቸው መጀመሪያ ላይ እሥራኤል ግንኙነት መመሥረቱን ተቃውማ ነበር ።በወቅቱ እስራኤላውያን ጀርመናውያንን በጥርጣሬ ዓይን መመልከታቸው ግንኙነቱ ዘግይቶ እንዲመሠረት አንዱ ምክንያት ሆኗል ። ምዕራብ ጀርመን በይሁዲዎች ላይ ለተካሄደው ጭፍጨፋ የሞራልና የገንዘብ ካሳ ለመክፈል ቃል ስትገባ የግንኙነቱ ምሥረታ መንገድ ተከፈተ ። ሁለቱ ሃገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመመሥረት የበቁት ግን ምዕራብ ጀርመን ለእስራኤል ካሳ ለመክፈል ከተስማማች ከ 15 ዓመት በኋላ ነበር ። እሥራኤል ከምዕራብ ጀርመን እንዲከፈላት በጠየቀችው ካሣ ላይ የምዕራብ ጀርመንና የእሥራኤል መንግሥታት በጎርጎሮሳዊው 1950 መደራደር ጀመሩ ። ሁለቱ ሃገሮች የሉክስምበርጉ ስምምነት በመባል የሚታወቀውን የካሳውን ስምምነት የፈረሙትም በጎርጎሮሳዊው መስከረም 1952 ቢሆንም ተግባራዊ የሆነው ግን መጋቢት 1953 ነበር ።በሰነዱ ላይ ናዚ ጀርመን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ይሁዲዎች በባርነት ላሰራበት ና በግፍ ለገደለበት እንዲሁም በናዚዎች ለተሰረቀው የይሁዲዎች ንብረት ምዕራብ ጀርመን ካሳ ለመክፈል ተስማማታለች ።ከስምምነቱ በኋላ ሁለቱ ሃገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመመሥረት መልካም ፈቃዱ እያላቸው 15 ዓመት ሊወስድ የቻለበት ምክንያት ምን ይሆን !? የበርሊኑ ወኪላችን ይልማ ኃይለ ሚካኤል ምክንያቱ ፖለቲካዊ ነው ይላል ።
ድምፅ ከት አንድ
ከጀርመን ካሳ መጠየቁ በእሥራኤል በወቅቱ አከራካሪና አጨቃጫቂ ነበር ። በወገኖቻችን ደም ምክንያት የመጣ ገንዘብ ከጀርመናውያን አንቀበልም የሚሉ ቡድኖች በተለያዩ ጊዜያት በእስራኤል ፓርላማ ክኔሴት ተቃውሞአቸውን ያሰሙ ነበር ። ሆኖም የያኔው የእስራኤል መንግሥት ካሳውን ለመቀበል በስምምነቱ ሰነድ ላይ ፈርሟል ። ይልማ እንደሚለው እስራኤልና ጀርመን ያኔ በነበሩበት ሁኔታ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲፈጥሩ እስራኤልም የገንዘቡን ካሳ እንድትጠይቅ ያስገደዷቸው ምክንያቶች ነበሩ ።
ድምፅ ከት 2
ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ መጀመሪያ ላይ በተለይ ለጀርመናውያኑ ቀላል አልነበረም ። በእስራኤል የመጀመሪያው የጀርመን አምባሳደር ሮልፍ ፓውላስ እሥራኤል ሲገቡ ህዝቡ የተቀበላቸው በተቃውሞ ሰልፍና ቲማቲም በመወርወር ነበር ። ሁለቱ ሃገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከመሰረቱ በኋላም እስራኤልና ከእስራኤል ውጭ የሚገኙ ይሁዲዎች በጀርመንና በጀርመናውያን ላይ የነበራቸው አለመተማመን በቀላሉ ሊወገድ አልቻለም ።ሆኖም ጥርጣሬውና ያለመተማመኑ ደመናቀስ በቀስ እየገፈፈ የሁለቱ ሃገራትም ግንኙነት እየጠነከረ ለመሄድ በቃ ። ከ50 ዓመት በኋላ ዛሬ በጀርመንም ሆነ በእሥራኤል ውስጥ ብዙ ለውጦች አሉ ። እዚህ ጀርመን የቀድሞዎቹ የእስራኤል አምባሳደሮች በጀርመን ቴሌቪዥን ጣቢያዎች በተደጋጋሚ በእንግድነት ይቀርባሉ ።የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ሰሞኑን እንደተናገሩትም ወዳጅነቱ አሁን እጅግ የተጠናከረ ደረጃ ላይ ደርሷል ። «የጀርመናውያንና የእስራኤላውያን የጉብኝት ልውውጥ የዕለታዊው የፖለቲካ ተግባራችን ን አንድ አካል ሆኗል ። እንዲያውም የሁለቱ መንግሥታት የባለስልጣናት ቡድን በዓመት አንድ ጊዜ በአንድ ትልቅ ጠረቬዛ ዙሪያ ተሰባስበው አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ይነድፋሉ ይሳሳቃሉ ይጨቃጨቃሉ ይህ ደግሞ በወዳጆች መካከል የተለመደ ሁኔታ ነው ። አስተዋዩ ፖለቲከኛ ቤን ጎርዮን በኋላም ኮንራድ አደናወር ሁለቱም ተባብረው የዘሩት ዘር በቅሎ አብቦ ጎምርቶ ፍሬ አፍርቷል ።ይህም ከኛ ድንበር ባሻገር አልፎ በዓለም ዓቀፍ መድረክ በፀረ-ሴማዊነትና በዘረኛነት ጉዳዮች ላይ በሚንፀባረቅ የጋራ አቋማችን የሚታይ ነው ።» ነው ።
የእስራኤልና የጀርመን ወዳጅነት በተጠናከረበት በአሁኑ ጊዜ በርካታ ወጣት እስራኤላውያን ጀርመንን መኖሪያቸው አድርገዋል ። ብዙ ጀርመናውያንም እስራኤል ይገኛሉ ።
ይልማ
በተለያዩ ጊዜያት ስልጣን የሚይዙ የጀርመን መንግሥታትበሚከተሉት የውጭ ፖሊሲያቸው ለእስራኤል ህልውና በማያወላዳ ሁኔታ መቆም ግንባር ቀደም አቋማቸው ነው ።ይህም የተመድ ን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም ዓቀፍ መድረኮች የሚንፀባረቅ የጀርመን አቋም ነው ። የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በጎርጎሮሳውያኑ 2008 በእስራኤል ፓርላማ ክኔሴት ተገኝተው ባሰሙት ንግግር ይህኑ ነበር ያረጋገጡት
«ለኔ እንደ ጀርመን መራሂተ መንግሥት የእሥራኤል ደህንነት ከቶውንም ለድርድር አይቀርብም »
ጀርመን የእስራኤል መንግሥት እንዲነካ ባለመፈለግና እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ የምትወስዳቸውን እርምጃዎች ደፍሮ ባለመተቸት ትወቀሳለች ። በዚህ ረገድ አንዳንድ ሂሰኞች በሚቀራረቡ ወዳጆች መካከል ደስ የማይሉ የወቀሳ ቃላት ሊነገሩ ይገባል ሲሉ ቅሬታቸው ይገልፃሉ ።አንዳንድ የጀርመን ፖለቲከኞች ግን የእስራኤል መንግሥት በፍልስጤማውያን ላይ የሚወስዳቸውን የኃይል እርምጃዎች መቃወማቸውና ለእስራኤልና ፍልስጤም ሰላም ፣ጎን ለጎን የሚመሰረቱ የሁለት መንግሥታት መፍትሄን መደገፋቸው አልቀረም ።
ኂሩት መለሰ

Staatsbesuch Israels Präsident Rivlin trifft Merkel in Berlin
የእስራኤል ፕሬዝዳንት ሪቪሊን በበርሊን ከሜርክል ጋርምስል Reuters/H. Hanschke
Deutschland Israel Israelischer Ministerpräsident Izchak Rabin in Bonn bei Helmut Schmidt
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ይስሃቅ ራቢን በ1975 ቦንን ሲጎበኙምስል picture-alliance/dpa
Israel Brandt besucht Israel 1973
የጀርመን መራሄ መንግሥት ቪሊ ብራንት የ1973 የእሥራኤል ጉብኝትምስል picture-alliance/dpa

ነጋሽ መሐመድ