1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ልማት-አገልግሎት ድርጅት(ዴኤዴ) እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ

ሐሙስ፣ የካቲት 17 1997

የጀርመን መንግሥት በየጊዜው የሚሰጠው መግለጫ እንደሚያስረዳው፥ በአጽናፋዊው ድህነት አንፃር የሚደረገውን ትግል የመንግሥታዊ መርሁ ማዕከላዊ ነጥብ ነው ያደረገው፣ በቡድን-፯ ከተጣመሩት ዓበይቱ እንዱስትሪ-ሀገሮች ጋር በሚደረገው ምክክር አማካይነት በተለይ አፍሪቃ ውስጥ ዘላቂው ልማት የሚነቃቃበትን መንገድ ይከታተላል።

https://p.dw.com/p/E0ex

በዚህ ረገድ ከአምስት ዓመታት በፊት በተባ መ ዘንድ የተተለመው የአሠርቱ ምእት ግብ ዓይነተኛውን ትኩረት ነው የሚያገኘው። ለልማት ርዳታ ቋሚ የሆነው የጀርመን ኤኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ለዚሁ የዘላቂ ልማት ዓላማ ልይዩ አራማጅ ድርጅቶችን ነው አማካይ የሚያደርገው። ክእነዚሁ መካከል አንዱ በአሕጽሮት “ዴኤዴ” የሚሰኘው የጀርመን ልማት-አገልግሎት ድርጅት ሲሆን፣ ኢትዮጵያን በመሳሰሉት አዳጊ ሀገሮች ውስጥ ለተለዩ የኤኮኖሚ ዘርፎች የተለየውን ትኩረት በመስጠት፣ በድህነት አንፃር ለሚደረገው ትግል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ዛሬ ይኸው የልማት አራማጅ ድርጅት(ዴኤዴ) ለሚንቀሳቀስባቸው ያገልግሎት ዘርፎች ትኩረት በመስጠት፥ በአዲስ አበባ የተመደቡት የዚሁ ድርጅት የሀገር መርሐግብር ኃላፊ ጌርት ኤምዘን ካሁን ቀደም ዶይቸቬለን በጎበኙበት ወቅት በዚሁ ጣቢያ ውስጥ የራዲዮ ሥራ ልምምድ ስታደርግ ለነበረችው ተናኘ ታደሰ የሰጡትን ቃለምልልስ ነው የምናቀርብላችሁ።

ከ፵ ዓመታት በፊት የተመሠረተው የጀርመን ልማት-አገልግሎት ድርጅት(ዴኤዴ) ለጀርመን መንግሥት የልማት መርሕ ትግበራ አማካይ ከሆኑት ከሌሎቹ ድርጅቶች---ማለት ከመልሶ ግንባታው የብድር ተቋም፣ ከዓለምአቀፉ የከፍተኛ ሥልጠና እና ልማት ማኅበር፣ እንዲሁም ከጀርመኑ የቴክኒካዊ ትብብር ድርጅት(ጂቲዜድ) እና ከተባ መ የልማት መርሐግብር(ዩኤንዲፒ) ጋር በመተባበር ነው የድህነት ቅነሳውን ግብ የሚከታተለው። እጎአ እስከ ፪ሺ፲፭ ድረስ የዓለም ድህነት በግማሽ እንዲቀነስ የተባ መ ጠቅላላ ጉባኤ ከአምት ዓመታት በፊት የተለመውን ግብ ማዕከላዊ የእንስቃሴ መስክ ያደረገው የልማት አገልግሎቱ ድርጅት(ዴኤዴ) በዚሁ የድህነት ቅነሳ መርሐግብር ረገድ ሕዝቡ በቀጥታ ተሳታፊ ለሚሆንበት ጥያቄ ከፍተኛውን ትርጓሜ ነው የሚሰጠው። በውጭ ሀገር የልማት ፕሮዤዎቹ በሚዘረጉባቸው ቦታዎች እየተገኙ፥ በሀገር ውስጥም ዝግጅቱን እያጠናቀቁ ይህንኑ የልማት ግብ የሚያራምዱት ባልደረቦቹ ከሁለት ሺህ ይበልጣሉ። “ዴኤዴ” በጠቅላላው ከ፵ በሚበልጡ ሀገሮች ውስጥ ነው የልማት ፕሮዤዎችን የሚያካሂደው።

የጀርመን የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ሚኒስቴር በልማት ርዳታው ረገድ ክብደት ከሚለግሳቸው ሀገሮች መካከል አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያ፥ ዴኤዴ በተለይ ለሁለት ዘርፎች ነው ቀዳሚውን ትኩረት የሚሰጠው። እነዚሁም፥ አንደኛ ተፈጥሮአዊውን ሐብት ዘላቂ ጥቅም ላይ በማዋል የመባልእትን አቅርቦት አስተማማኝ ማድረግ፤ ሁለተኛ የቴክኒካዊውን መርሐሙያ ሥልጠና በማነቃቃት የኤኮኖሚውን ተሐድሶ ለውጥ ማራመድና የገበያ ኤኮኖሚውን ሥርዓት መገንባት። በአዲስ አበባ የተመደቡት የመርሐግብሩ ኃላፊ ጌርት ኤምዘን ከጥቂት ጊዜ በፊት ቦን ውስጥ ተገኝተው ዶይቸ ቬለን በጎበኙበት ወቅት ተናኘ ታደሰ ላቀረበችላቸው ቃለመጠይቅ የሰጡት መልስ እነዚሁኑ የልማት ትኩረት መስኮች የሚያብራራ ነው።

ተናኘ ታደሰ ለሚስተር ጌርት ኤምዘን በጀርመንኛ ያቀረበችው መጀመሪያው ጥያቄ፥ የጀርመን የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት መሥሪያቤት ለኢትዮጵያ የሚዘረጋው የልማት ርዳታ መርሐግብር ኃላፊ በመሆን ከመቼ ጀምረው አዲስ አበባ ውስጥ በአገልግሎት ላይ እንደሚገኙ፣ ድርጅታቸው በተለያዩ አዳጊ ሀገራት ውስጥ ልይዩ የልማት ርምጃዎችን እንደሚከታተል በጠቅላላው ቢታወቅም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ የሚያተኩርበት የልማት አግጣጫ የትኛው እንደሆን የሚያመላክት ነበር። ጌርት ኤምዘን ይህንኑ ሲመልሱ፥”--------እኔ ከሚያዝያ ፲፱፻፺፭ ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ በመገኘት፣ ማዕከላዊ መሥሪያቤታቸውን በናይሮቢ ያደረጉት ያካባቢው ዋና ሥራ-አስኪያጅ ወኪልና ረዳት ሆኜ ለሀገሪቱ የተዘረጋውን መርሐግብር በኃላፊነት አስፈጽማለሁ። ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ ለሁለት ዐበይት ዘርፎች ነው ቀዳሚውን ትኩረት የምንሰጠው። ይኸውም፥ አንደኛው የገጠርን ልማትና የመባልእት አቅርቦትን ዋስትና የሚመለከት ሲሆን፣ ሁለተኛው የትኩረት መስክ ደግሞ የመርሐ-ሙያው ሥልጠና ነው። ራሱ የጀርመን ቴክኒካዊ ትብብር ድርጅት(ጂቲዜድ) ቀዳሚውን ትኩረት የሚሰጠው ለእነዚሁ ሁለት ዓበይት ዘርፎች ነው። ከዚህም በላይ መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶችም አስፈላጊውን ምክር በመለገስ፣ መታተሪያ መስካቸውን እናነቃቃለን፣ አሁን ደግሞ በሲቪል አገልግሎትም በኩል አዲስ ሐሳብ ለማንቀሳቀስ ነው ያቀድነው።”

ተናኘ ታደሰ ለጌርት ኤምዘን ያቀረበችው ሁለተኛው ጥያቄ፥ የምግብ አቅርቦቱን ችግር ሁኔታና የልማት ርዳታ ድርጅቱን ቀጣይ ሂደት ያስመለከተ ነበር፥ “--------------የጀርመን ልማት-አገልግሎት(ዴኤዴ) በቀጥታ በድንገተኛ ጊዜው ርዳታ ላይ አይደለም የሚንቀሳቀሰው፤ የኛ ሥራ፥ የተፈጥሮ ሐብቶች በረዥም ጊዜ ውስጥ ለሚለሙበት መርሐግብር ነው ትኩረት የሚሰጠው። የጀርመን ቴክኒካዊ ትብብር ድርጅት(ጂቲዜድ) በበኩሉ ይህንኑ መስመር ነው የሚከተለው። እኛ በተለይ በተፈጥሮ ሐብቶች እንክብካቤና ልማት፣ የተራቆተ መሬት እንደገና ደን በሚለብስበት ርምጃ፣ በንፁሕ ውሃ አቅርቦት ልማት ወዘተ---ከፍተኛ ተሳትፎ ነው ያለን። ይኸውም እንግዲህ፥ የድንገተኛ ጊዜውን ርዳታ ለዚሁ ተግባር ለቆሙት ድርጅቶች ሚና ነው የምንተወው፤ አስቀድሜ እንዳልኩት፥ እኛ በተለይ የምናተኩረው በተፈጥሮ ሐብቶች የረዥም ጊዜ ልማት ላይ ነው። በመርሐሙያ ሥልጠና ረገድ የግል ኤኮኖሚውም ዘርፍ ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝ ጥረት እናደርጋለን፤ መንግሥት ወይም መንግሥታዊ ያልሆኑት ድርጅቶች በግል ኤኮኖሚው ዘርፍ በኩል ምን ያህል የመርሐ ሙያ ሥልጠና አገልግሎት ዝግጁ እንደሚያደርጉ ማረጋገጥና ይህንኑ ማነቃቃት የዘወትር ፍላጎታችን ነው።”

ጀርመንና ኢትዮጵያ ዘንድሮ የዲፕሎማታዊ ግንኙነታቸውን ፩-መቶኛ ዓውዳመት በጋራ የሚያከብሩ እንደመሆኑ መጠን፣ በእነዚሁ ፩-መቶ ዓመታት ውስጥ የትኛው ክንውን እንደተገኘ፣ የልማት ትብብሩ ወኪል-ድርጅ ዴኤዴም ሲንቀሳቀስ በቆየበት የ፵ ዓመታት ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ምን ያህል ስኬት እንዳመጣ፣ የወደፊት እቅዳቸውም ምን እንደሚመስል ጠቅላላ ግምገማ ያደርጉ ዘንድ፥ ተናኘ ታደሰ ላቀረበችላቸው መደምደሚያ ጥያቄ የዴኤዴ አዲስ አበባ ቢሮ ኃላፊ ጌርት ኤምዘን ይህን ሰፊ መልስ ነበር የሰጡት፥ “-----------የአንድ መቶ ዓመታቱን ዲፕሎማታዊ ግንኙነት የሚያከብሩት የጀርመን መንግሥትና የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ አይደሉም፤ ዴኤዴም ጭምር ነው። አከባበሩ “ጂቲዜድ” እና ‘ዴኤዴ” የጋራ መንበር የሚይዙበትን፥ “ቤተ-ጀርመን” የሚሰኘውን ተቋም ምረቃም የሚያካትት ይሆናል። በዚህ አኳኋን፥ እኛ ኢትዮጵያ ውስጥ የጋራ መርሕ እንደምንከተል ወደ ውጭ ለማሳየትም ነው የምንፈልገው። ባለፉት ዓመታት ውስጥ የተገኙትን ክንውኖች መገምገም በጣም አስቸጋሪ አይደለም፣ እኔ እዚያ ማገልገል ከጀመርኩ ወዲህ አንድ ዓመት ተኩል ማለፉ ነው፣ ስለዚህ የሥራ ባልደረቦቼ እንደሚነግሩኝ፥ ባለፉት ዓመታት የተዘረጉት የልማት ፕሮዤዎች አሁንም ሕልውና አላቸው፣ አሁንም ቢሆን በጥሩ ሁኔታ ነው የሚካሄዱት። አሁን በሁለቱ ዓበይት የትኩረት ዘርፎች በኩል የሚካሄደው የልማት ሥራ ገና ወደ ክንውን ደረጃ አልተሸጋገረም፣ እኛ በዚህ ረገድ ለውጥን ለማስገኘት ነው የምንጥረው፤ ይህንኑ ለውጥ ለማስገኘት እንደምንበቃ እንተማመንበታለን። የኢትዮጵያውያኑ ችግሮች ለሚወገዱበት መንገድ ከፍተኛውን ትኩረት ነው የምንሰጠው፤ መሻሻልን ለማስገኘት በየጊዜው ነው ሙከራ የምናደርገው፤ ይኸው ሙከራ በአራት--በአምስት--በስድስት ዓመታት ውስጥ የሚያስገኘው ውጤት---ለምሳሌ በመርሐሙያ ሙያ ሥልጠናው መስክ በኩል የሚገኘው ክንውን---ኢትዮጵያ እመርታዋን በማጠናከር ራሷን ለኢንተርኔቱ መረብ ቅርብ አድርጋ የምታስተካክልበትን የዕድገት ደረጃ እንደሚሰጣት ነው የኛ ተሥፋ። እኛ ተሥፋ የምናደርግበት ክንውን የመርሐሙያውን አገልግሎት፣ የተፈጥሮ ሐብቶችን እንክብካቤና ልማት፣ እንዲሁም የመባልእት አቅርቦትን ዋስትና የሚያመላክት ነው። ከሁሉ ይልቅ ደግሞ፥ ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ አሜሪካን፣ ካናዳን ከመሳሰሉት ከታላላቆቹ እንዱስትሪ-ሀገሮች የእህል ርዳታ ጥገኝነት እንደምትላቀቅና የራሷን የምግብ አቅርቦት ችግር በራሷ አቅም ልትፈታው እንደምትችልም ነው እኛ አሁን ተሥፋ የምናደርገው። ኢትዮጵያ ይህንኑ ጥገኝነት ለምትቀንስበትና ለምታስወግድበት ርምጃ እኛም የበኩላችንን አስተዋጽኦ እንደምናደርግ ዓይነተኛ ምኞታችን ነው። ግን ይኸው ሙሉ የራስአገዝነት ግብ ምኑን ያህል እንደሚሳካና ምኑን ያህል እውን እንደሚሆን አሁን እኛም ራሳችን አናውቀውም፥ ቀጥሎ እንደገና የሚከሰት የድርቅ አደጋ ሁሉን ነገር ሊያመሰቃቅለው ይችላል፤ ሆኖም አሁን ትክክለኛው ርምጃ የተዘረጋ ስለመሆኑ እርግጠኛነትና ደስታ ይሰማናል። መንግሥት የዘረጋው የርምጃ ዕቅድና ያንቀሳቀሰው የልማት ሐሳብ ሊተገበር ችሎ፣ በሚቀጥሉት ዓመታት ውስጥ ሀገሪቱን ከውጭው የምግብ ርዳታ ጥገኝነት ሊያላቅቅ የሚበቃበትን መንገድ ነው አሁን እኛ አትኩረን የምንመለከተው።”