1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን መራሔ መንግሥት የሊብያ ጉብኝት ፍፃሜ

ሰኞ፣ ጥቅምት 8 1997

የጀርመን መራሔ መንግሥት ጌርሀርት ሽረደር ባለፈው ሐሙስና ዓርብ ሊብያን ጎብኘዋል። አንድ የጀርመን መራሔ መንግሥት ሊብያን ሲጎበኝ ሽረደር የመጀመሪያው ናቸው።

https://p.dw.com/p/E0kr
ጌርሀርት ሽረደረ ሞአመር ኤል ጋዳፊ ጋር በትሪፖሊ
ጌርሀርት ሽረደረ ሞአመር ኤል ጋዳፊ ጋር በትሪፖሊ

ቀደም ባሉ ጊዚያት የአሸባሪዎች ደጋፊ ይባሉ የነበሩት የሊብያ ዓብዮታዊ መሪ ሞአመር ኤል ጋዳፊ ካለፉት ጥቂት ጊዚያት ወዲህ ያደረጉትን ፖለቲካዊና ኤኮኖሚያዊ ተሐድሶ ሽረደር በዚሁ ጉብኝታቸው ወቅት ቢያሞግሱም፡ የዶቸ ቬለ ባልደረባ ዩዲት ሀርትል እንደዘገበችው፡ የሀገር ውስጡ ተሐድሶ ልክ በውጭው ፖሊሲ ላይ እንደታየው ለውጥ ፍጥነት እንዲታይበት ከማሳሰብ ወደ ኋላ አላሉም።
ሙአመር ኤል ጋዳፊ እንደ ሽብር አራማጅ ይታዩ የነበረበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። ይሁንና፡ ሊብያ በሎከርቢ ስኮትላንድ ሲበር በተጣለበት ጥቃት በተከሰከሰው ያሜሪካውያኑ የፓናም አይሮፕላን፡ እንዲሁም፡ በበርሊን የላ ቤል ዳንኪራ ቤት ላይ በተጣለው ጥቃት ለሞቱት ሰለባዎች ቤተሰቦች ካሣ ከከፈለችና ለሁለቱ ጥቃቶችም ኃላፊነቱን ከወሰደች ወዲህ፡ ምዕራቡ ዓለም ጋዳፊን ወደ ዓለም አቀፉ የፖለቲካ መድረክ መልሶዋል፤ እንደ ዋነኛ ተጓዳኙም መመልከት ጀምሮዋል። በዚሁ የአመለካከት ለውጥም መደዳ ነበር የጀርመን መራሔ መንግሥት ጌርሀርት ሽረደር ባለፈው ሣምንት ሊብያን የጎበኙት። በሊብያ ላይ ተጥሎ የነበረው ማዕቀብ እንደተነሣ ወዲያውኑ ነበር ምዕራባውያት ሀገሮች ከጋዳፊ ጋር ለመገናኘት የተሯሯጡት። የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር ትሪፖሊን የጎበኙት ከ፿ጥቂት ጊዜ በፊት ነበር። የኢጣልያው ጠቅላይ ሚንስትር ሲልቭዮ በርሉስኮኒም በሊብያ አዘውትረው የሚታዩ እንግዳ ሆነዋል፤ የፈረንሣይ ፕሬዚደንት ዣክ ሺራክም በቅርቡ ሊብያን እንደሚገበኙ አስታውቀዋል። አሜሪካውያኑ ደግሞ ወደ ሊብያ በጓሮ በር በመግባት የሀገሪቱን አማላይ የነዳጅ ዘይት ምንጮችን መያዝ ጀምረዋል። ሁሉም በብዛት በሚገኘው የሊብያ ነጃጅ ዘይትና ጋዝ ምርት ለመሳተፍ ነው ፍላጎታቸው። ጋዳፊ የሀገራቸውን የኃይል ምንጭና ኤኮኖሚ ከማነቃቃታቸው ሌላ፡ ታጋቾችን ከሙሥሊሞቹ አክራሪዎች እጅ ለማስለቀቅና አሸባሪነትን ለመታገል ይረዳሉ፤ በሊብያ በኩል አድርጎ ወደ አውሮጳ የሚጎርፉት ስደተኞች ለሚያስከተሉት ችግርም መፍትሔ ለማስገኘት ይጥራሉ። ይህ ሁሉ ጋዳፊ በወቅቱ ለሚነሡ ዓለም አቀፍ ችግሮች መፍትሔ የሚያስገኙ አስመስሏቸዋል። ይሁንና፡ ጋዳፊ ያው የቀድሞው ጋዳፊ መሆናቸው ሊረሣ አይገባም፤ ካለፉት ሠኣሣ ስድስት ዓመታት ወዲህ የአንድ ሰው አገዛዝን ያስፋፉት ጋዳፊ ከጥቂት ጊዜ በፊት በምዕራባውያን አንፃር የሚጣሉ ጥቃቶችን መደገፋቸውም አይዘነጋም። ታድያ አሁን በስድሣ አንድ ዓመታቸው፡ ያውም ባጭር ጊዜ ውስጥ በድንገት ተቀይረዋል መባላቸውን በጥርጣሬ የሚመለከቱ ጥቂቶች አይደሉም። ጋዳፊ ሀገራቸው ዓለም አቀፉ ኅብረተ ሰብ አሳርፎባት በነበረው ማዕቀብ ይበልጡን እንዳትጎዳ በማሰብ ከምዕራባውያኑ ጋር ቢያንስ በፖለቲካው መድረክ ገላጋይ ሀሳብ ለመድረስ መወሰናቸው ብልህ ያሰኛቸዋል። ምዕራቡ ዓለም አመናቸው አላመናቸውም ጅምላ ጨራሹን የጦር መሣሪያ ለማምረት ዕቅድ እንደሌላቸው እና ሽብርተኝነትንም እንደሚያወግዙ ግልፅ አድርገዋል። የሊብያ እጅ አለባቸው ለተባሉት ጥቃቶች ሰለባዎችም በሚልያርድ የሚቆጠር ዶላር ካሣ በመክፈል ታማኝነታቸውን ለማሳየት ሞክረዋል። ምዕራባውያቱ ሀገሮችም ይህንኑ ርምጃቸውን አጥጋቢ አድርገው ተመልክተውታል። ይህም በሁለቱ መካከል የተጀመረውን ግንኙነት፡ ሁለቱም ወገኖች ተጠቃሚዎች ስለሚሆኑ፡ የተሳካ እንደሚያደርገው አመላክቶዋል። ይሁን እንጂ፡ ዓለም አቀፉ ኅብረተ ሰብ በጋዳፊና በሊብያ ዙርያ በወቅቱ በሚሰማው አዎንታዊ አስተያየት መዘናጋት አይኖርበትም፤ በዚህ ፈንታ የጋዳፊ መለወጥ ዘለቄታ ይኖረው መሆን አለመሆኑን መከታተል ይጠበቅበታል።