1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አንድሪያ ናሕሌስ ከሥልጣናቸው እንደሚለቁ አስታወቁ።

እሑድ፣ ግንቦት 25 2011

የጀርመን ሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ ሊቀ-መንበር  አንድሪያ ናሕሌስ ከሥልጣናቸው እንደሚለቁ አስታወቁ። በአውሮፓ ምክር ቤት ምርጫ የከፋ ውጤት የገጠመውን ግራ ዘመም ፓርቲ የሚመሩት ናሕሌስ የደረሱበት ውሳኔ የመራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክልን መንግሥት ጥያቄ ውስጥ ጥሎታል።

https://p.dw.com/p/3JdQJ
Berlin Andrea Nahles SPD-Vorsitzende
ምስል Imago Images/E. Contini

የጀርመን ሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ ሊቀ-መንበር  አንድሪያ ናሕሌስ ከሥልጣናቸው እንደሚለቁ አስታወቁ። በአውሮፓ ምክር ቤት ምርጫ የከፋ ውጤት የገጠመውን ግራ ዘመም ፓርቲ የሚመሩት ናሕሌስ የደረሱበት ውሳኔ የመራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክልን መንግሥት ጥያቄ ውስጥ ጥሎታል። ናሕሌስ በፓርቲው እና በምክር ቤት አባላት ዘንድ በመሪነት የሚያስቀጥል ድጋፍ በማጣታቸው ለመልቀቅ መወሰናቸውን በዛሬው ዕለት ይፋ ባደረጉት መግለጫ አስታውቀዋል። አንድሪያ ናሕሌስ ከፓርቲ መሪነታቸው በመጪው ሰኞ እንዲሁም ከምክር ቤት ኃላፊነታቸው ማክሰኞ ይለቃሉ። ናሕሌስ "የእኔ ተተኪ ሥርዓት ባለው መንገድ ይመረጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ" ይበሉ እንጂ ውሳኔያቸው ፓርቲው በጀርመን መንግሥት ውስጥ ያለውን ተጣማሪነት አደጋ ላይ እንዳይጥል አስግቷል። የፓርቲው ምክትል ሊቀ-መንበር ሐራልድ ክሪስት ከአንጌላ ሜርክል ፓርቲ ጋር የተመሰረተው ጥምረት ጥርጣሬ ውስጥ መውደቁን ቢልድ ለተባለው ዕለታዊ ጋዜጣ ተናግረዋል። 
የአንጌላ ሜርክል ክርስቲያን ዴሞክራቶች ፓርቲ ከግራ ዘመሞቹ ሶሻል ዴሞክራቶች የፈጠሩት ጥምረት ከመነሾው ውጣ ውረድ የገጠመው ነበር። በጎርጎሮሳዊው 2017 ዓ.ም. በተካሔደው የጀርመን ምርጫ የከፋ ውጤት የገጠመው የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ሐሳቡን ቀይሮ በመንግሥት ጥምረት ውስጥ ከመግባቱ በፊት ከተቃውሞ ጎራ የመሰለፍ ውጥን ነበረው። 

እሸቴ በቀለ

ልደት አበበ