1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 27 2011

አሁን በSPD ውስጥ የደረሰው ቀውስ ጥምሩን መንግሥትም መጎሸሙ አልቀረም።መጎሸም ብቻ አይደለም ምናልባትም አዲስ ምርጫ ሊያስጠራም ይችላል የሚሉ ግምቶች ይሰነዘራሉ። የህዝብ ድጋፍ የሸሸው SPD አሁን የሚገንበት ሁኔታ ብዙ የሚያስተላልፈው መልዕክት እና የሚሰጠውም ትምህርት አለው።

https://p.dw.com/p/3JqQC
Berlin SPD SItzung Nahles
ምስል picture-alliance/dpa/W. Kumm

የጀርመን ሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ወዴት እየተጓዘ ይሆን?

 

አንጋፋው የጀርመን ሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ በቅርቡ በተካሄደው የአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት ምርጫ እጅግ አነስተኛ ድምጽ ካገኘ በኋላ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ይገኛል። የፓርቲው መሪ ከሥልጣናቸው ወርደው አዲስ መሪ እስኪመረጥ ድረስ ሦስት ጊዜያዊ መሪዎች ተሰይመዋል ። በSPD ውስጥ የተፈጠረው ቀውስ አባል በሆነበት በጥምሩ መንግሥት ዘላቂነት ላይ ጥያቄ አስነስቷል። የመሀል ግራው የጀርመን ሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ በጀርመንኛው ምህጻር SPD ህዝባዊ ከሚባሉት የሀገሪቱ ፓርቲዎች እድሜ ጠገቡ ፓርቲ ነው። 150 ዓመት ያስቆጠረው ይህ ፓርቲ የሠራተኞችን መብቶች ለሚያስጠብቁ ፖሊሲዎች፣ ለህዝባዊ አገልግሎቶች፣ እንዲሁም በሀገሪቱ ለተመጣጠነ የኑሮ ደረጃ ዋስትና መቆም የተመሰረተበት ዓላማ ነው። ይሁን እና ፓርቲው በተለይ ከዛሬ 20 ዓመት ወዲህ በተካሄዱ ምርጫዎች የሚያገኘው ድምጽ እየቀነሰ መሄድ ህልውናውን እከመፈታተን የደረሰ ይመስላል። የኋለኞቹን ትተን በጎርጎሮሳዊው 1998 በተካሄደውሀገር አቀፍ ምርጫ 40.9 በመቶ ድምጽ ያሸነፈው ይህ ፓርቲ በዚህ ሳምንት ምርጫ ቢካሄድ ሊያገኝ የሚችለው ድምጽ 12 በመቶ ብቻ እንደሆነ ፎርሳ የተባለው ምስለ ምርጫ የሚያካሂድ ድርጅት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ይፋ አድርጓል።

SPD Krise Andrea Nahles Rücktritt Symbolbild
ምስል picture-alliance/dpa/A. Prautzsch

ፓርቲው የሚያገኘው ድምጽ እየቀነሰ መሄዱ አዲስ አይደለም። ሆኖም በዛሬ ሁለት ሳምንቱ የአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት ምርጫ ያሸነፈው 15.8 በመቶ ድምጽ የዛሬ አምስት ዓመት ከተሰጠው ጋር ሲነጻጸር በ11.4 በመቶ ዝቅ ማለቱ ግን አባላቱን እና ደጋፊዎቹን አስደንግጧል። ፓርቲው እስከዛሬ ካገኘው ድምጽ እጅግ ዝቅተኛ በተባለው በዚህ ውጤት ሰበብ መሪው አንድሪያ ናለስ ሥልጣናቸውን እንዲለቁ አስገድዷል። «እንደምን ዋላችሁ! የSPD መሪነት ሃላፊነቴን ለቅቄያለሁ። ባለፉት ዓመታት ለነበረን ጥሩ ትብብር ላመሰግናችሁ እወዳለሁ።በቪሊ ብራንት ቤት ብዙ ሰዓታትን አብረን አሳልፈናል። ለዚህም አመሰግናችኋለሁ። መልካሙን ሁሉ እመኝላችኋለሁ»

የመጀመሪያዋ ሴት የSPD ሊቀ መንበር ናለስ ከፓርቲው መሪነት መሰናበታቸውን ለጋዜጠኞች በአጭሩ ያሳወቁበት መግለጫ ነበር። አንድ ዓመት ከ1 ወራት ከ11 ቀናት በፓርቲው ሊቀመንበርነት እንዲሁም 1 ዓመት ከ8 ወራት በጀርመን ምክር ቤት የፓርቲው ምክር ቤት አባላት መሪ ሆነው ያገለገሉት ኔልስ በፈቃዳቸው ከነዚህ ሁለት ኃላፊነቶች መነሳታቸው ለጀርመን ፖለቲካ እንደ ድንገተኛ የልብ ድካም ተደርጎ ነው የተወሰደው። ስንብታቸው ለዓመታት ፓርቲውን ሲመዘምዝ የቆየው በሽታ የመጨረሻው ምልክትም ተብሏል።አንዳንዶች ደግሞ መራጮቹን በሌሎች ፓርቲዎች የተነጠቀው SPD  ራሱን ገድሏል።አብቅቶለታል ሲሉ ይደመጣሉ። የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር እና የሕግ ባለሞያ ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ ግን ይህን ከማይቀበሉት ውስጥ ናቸው። በርሳቸው አስተያየት ከልምድ እንደታየው ህዝባዊ መሠረት ያለው ይህ ፓርቲ እንዲህ በቀላሉ የሚከስም አይሆንም። 

Manuela Schwesig, Malu Dreyer und Thorsten Schäfer-Gümbel
ምስል picture-alliance/dpa/S. Stein


ሶሻል ዴሞክራቶች ለሽንፈት የመዳረጋቸው ምክንያቱ የዓመታት ድምር ውጤት መሆኑን ይናገራሉ ዶክተር ለማ። አንዱ ችግር በተለይ የሠራተኛውን መካከለኛ ገቢ ያለውን ህዝብ እና የእጅ ሞያተኛውን ፍላጎት ከዓለም አቀፉ የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ ጋር አጣጥሞ የመራጮችን ፍላጎት ሊመልስ የሚችል ፍኖተ ካርታ አለመኖሩ ነው ይላሉ።ፓርቲው ባለፉት 20 ዓመታት መራጮቹ ለመነጠቃቸው  ዋና ዋና ያሏቸውን ሌሎች ምክንያቶችንም እንዲህ ዘርዝረዋል። የጀርመን ሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ አዲስ መሪ እስከሚመርጥ ድረስ ሦስት ጊዜያዊ መሪዎችን ሰይሟል። እነዚህ ጊዜያዊ መሪዎችም በኃላፊነት ላይ የሚቆዩት እስከ ጎርጎሮሳዊው ሰኔ 24 ድረስ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ  የመሪ አመራረጥን ጨምሮ ሌሎች ሊስተካከሉ ይገባቸዋል በሚባሉ አሠራሮች ላይ ፓርቲው ይመክራል ተብሎ ይገመታል። ዶክተር ለማ እንደሚሉት በተለያዩ የአውሮጳ ሀገራት ትርጉም አልባ እየሆነ የመጣው የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ በጀርመንም ተመሳሳይ እጣ እንዳይደርስበት የመራጩን ህዝብ እና የአባላቱን ፍላጎት ለሟማላት እርምጃዎችን መውሰድ ይጠበቅበታል።

የSPD ህመም ከብዙ ክርክር እና ንግግር በኋላ እውን ሊሆን በበቃው የጀርመን ታላቁ ጥምር መንግሥት ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ አልቀረም። ጥምር መንግሥቱ የዛሬ ዓመት ከመስረቱ በፊት ፓርቲው ተቃዋሚ እንደሚሆን ነበር ያሳወቀው። ሆኖም ባለፈው ምርጫ አብላጫ ድምጽ ያገኙት የክርስቲያን ዴሞክራት እና የክርስቲያን ሶሻል ህብረት ፓርቲዎች ከአረንጓዴዎቹ እና ከነጻ ዴሞክራቶች ፓርቲዎች ጋር ያካሄዱት የመንግሥት ምሥረታ ንግግር ከከሸፈ በኋላ ሌላ ምርጫ በመታጣቱ SPD ከእህትማማቾቹ ፓርቲዎች ጋር ተስማምቶ የጥምር መንግሥቱ አካል ሆኗል።እናም አሁን በSPD ውስጥ የደረሰው ቀውስ ጥምሩን መንግሥትም መጎሸሙ አልቀረም።መጎሸም ብቻ አይደለም ምናልባትም አዲስ ምርጫ ሊያስጠራም ይችላል የሚሉ ግምቶች ይሰነዘራሉ። የህዝብ ድጋፍ የሸሸው SPD አሁን የሚገንበት ሁኔታ ብዙ የሚያስተላልፈው መልዕክት እና የሚሰጠውም ትምህርት አለው እንደ ዶክተር ለማ። ከሥስት ሳምንት በኋላ ናለስን የሚተካው የSPD መሪ ማን እንደሚሆን ከወዲሁ ለመገመት አስቸጋሪ ሆኗል። ፓርቲው እንዲያንሰራራም ምናልባት ጥምሩን መንግሥት ለቆ የመውጣት ውሳኔ ላይ መድረስ አለመድረሱም እንዲሁ።ሁሉንም በጊዜው አብረን የምናየው እና የምንሰማው ይሆናል። 

Angela Merkel und Andrea Nahles
ምስል picture-alliance/dpa/K. Nietfeld

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ