1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ንግድና መዋዕለ-ነዋይ በኢትዮጵያ

ረቡዕ፣ ሰኔ 3 2001

ጀርመንና ኢትዮጵያ በአፍሪቃ አቻ የማይገኝለት የረጅም ጊዜ የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ታሪክ አላቸው። በሌላ በኩል በኤኮኖሚና በንግድ ረገድ ግን ዕድገቱ ከመቶ ዓመታት ከሚበልጠው የግንኙነት ዘመን አንጻር ሲታይ ያን ያህል ግዙፍ የሚባል አይደለም።

https://p.dw.com/p/I70k
ምስል picture-alliance / dpa

ለዚሁ የሁለቱ አገሮች የዕድገት ደረጃ ልዩነት፤ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚና የውጭ ንግድ አለመዳበርም ዋነኞቹ ምክንያቶች ናቸው። ሆኖም የጀርመን ኩባንያዎች መዋዕለ-ነዋይ በኢትዮጵያ ለማፍሰስ ያላቸው ፍላጎት ከጥቂት ዓመታት ወዲህ እየጨመረ መምጣቱ ነው የሚነገረው። በቅርቡም በጀርመን ኩባንያዎችና በኢትዮጵያ ሽርክና ላይ ያተኮረ የጥናት ስብሰባ በፍራንክፈርት ከተማ ተካሂዶ ነበር። የጀርመን መንግሥት ግንኙነቱን ወዳጅነት የተመላበት አድርጎ ነው የሚመለከተው። ሆኖም በኤኮኖሚው መስክ የትብብር ፍላጎት መኖሩ ባይቀርም ዕድገቱ የሚገባውን ያህል ተራምዷል ለማለት አይቻልም። በአንድ በኩል ጀርመን በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸገች፤ በውጭ ንግዷም በዓለም ላይ ቀደምት የሆነች አገር ናት።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ዓለምአቀፍ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በዜጎቿ 120 ዶላር ዓመታዊ ነፍስ-ወከፍ ገቢ መስፈርት በዓለም ላይ የድሃ-ድሃ ከሚባሉት አገሮች መካከል ነው’ የምትመደበው። በተባበሩት መንግሥታት መረጃ መሠረት በሰብዓዊ ልማት ረገድም እጅግ ኋላ ቀር ከሚባሉት መካከል አንዷ ስትሆን ትራንፓረንሢይ ኢንተርናሺናል ከሁለት ዓመታት በፊት በ 2007 ባቀረበው የሙስና ዘገባ ደግሞ ከ 179 የዓለም ሃገራት መካከል 138ኛውን ቦታ ነበር የያዘችው። ከግንቦት ምርጫ ወዲህ የአገሪቱ የሰብዓዊ መብት ይዞታም አዘውትሮ በዓለምአቀፍ ደረጃ የሚተች ጉዳይ ሆኖ ነው የቆየው።

ከፖለቲካው ባሻገር የኤኮኖሚው ሁኔታም በዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ይበልጥ በተባባሰው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ሳቢያ ዕርጋታን የሚፈታተን ከባድ ሁኔታን ማስከተሉ አልቀረም። የውጭ መዋዕለ-ነዋይን መሳቡ ደግሞ ከሁሉም በላይ የፖለቲካና የማሕበራዊ ኑሮ መረጋጋትን ይጠይቃል። ከዚሁ ሌላ ቢሮክራሲያዊ መሰናክሎች መወገድ አለባቸው፤ ለመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች ዋስትና የሚሰጡ ገቢር የሚሆኑ ጭብጥ ደምቦችና ሕግጋት መኖራቸውም በጣሙን ወሣኝ ነው። በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ ብቻ ሣይሆን በብዙዎች የአፍሪቃ አገሮች ሁኔታው በተወሰነ ደረጃ አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል።

ይሁን እንጂ በቅርቡ በፍራንክፈርት ከተማ በክፍለ-ሐገሩ የኢንዱስትሪና የንግድ ም/ቤት መቀመጫ ተካሂዶ በነበረ ስብሰባ የጀርመን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ይበልጥ በተግባር እንዲሰማሩ ሁኔታው እየተሻሻለ መምጣቱ ነው የተጠቀሰው። እርግጥ መሰናክሎች ይታጣሉ ማለት አይደለም። የኢንዱስትሪና የንግድ ም/ቤቱ የዓለምአቀፍ ጉዳይ ሥራ አስኪያጅ ዶር/ዩርገን ራትሲንገር እንደሚሉት ኩባንያዎቹ ተጨባጩን ሁኔታ አጢነው የሚበጃቸውን ማወቃቸው ምንጊዜም አስፈላጊ ነው።

“እርግጥ ነው፤ በየትናውም መዋዕለ-ነዋይን በውጭ የማፍሰስ ተግባር ለሁሉም አገር የሚሰራ ሃቅ አለ። አንድ ኩባንያ በመጀመሪያ ደረጃ ጥሩ ዝግጅት ማድረጉ አስፈላጊ ነገር ነው። ማለት ገንዘቡን በሥራ ላይ የሚያውልበትን አገር ተጨባጭ ሁኔታ በትክክል ማወቅ ያስፈልገዋል። ምን ጥቅም ላገኝ እችላለሁ፤ ገበያው ምን ያህል ሰፊ ነው፤ በዚያው ባመርትና ወደ ውጭ ለመሸጥ ብፈልግስ ብሎ ማሰብ አለበት። ከዚሁ ሌላ ተስማሚ ሽሪኮች መኖራቸውም መጤን ይገባዋል። እንግዲህ በውጭ መዋዕለ-ነዋይ ለማፍሰስ ጥሩ ዝግጅት ማድረጉ ራሱ ትልቅ ዕርምጃ ነው። እና በኢትዮጵያም ሁኔታው ከዚህ የተለየ አይሆንም”

የኢንዱስትሪና ንግድ ም/ቤቱ የዓለምአቀፍ ዘርፍ ሥራ አስኪያጅ ዶር ራትሲንገር በፍራንክፈርቱ ስብሰባ ላይ የጀርመን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተግባር ለመሰማራትና መዋዕለ-ነዋይን ለማሻገር ጥሩ ሁኔታ ሊገጥማቸው እንደሚችል አንዳንድ ምልክቶች መከሰታቸውንም አስረድተዋል።

“ከሁለት ሣምንታት በፊት በኢንዱስትሪና ንግድ ም/ቤቱ ባደረግነው ስብሰባ ለጀርመን ኩባንዮች ማራኪ ሁኔታ እንዳለ በአንዳንድ ምሳሌዎች ለመታዘብ ችለናል። በመጀመሪያ ደረጃ በዚያው እያመረቱ ወደ ውጭ ለመሸጥ! ከኢትዮጵያ ጋር ጥሩ የአየር ግንኙነት አለ። ከጀርመን ወይም ከአውሮፓ ገበዮች ርቀቱ ያን ያህል ብዙ አይደለም። በኢትዮጵያ ገበያ ላይ ለመጠቀምም እንዲሁ ለምሳሌ በኤነርጂው ዘርፍ የነፋስ፤ የውሃ ኤነርጂ መስክ ጥሩ ዕድል ነው ያለው። ኢትዮጵያ በመዋቅራዊው ዘርፍ የጎደላትን ለማሟላት ትፈልጋለች። ስለዚህም ለጀርመን ኩባንያዎች በዚህ ረገድ ለመሳተፍ በሚቀጥሉት ዓመታት ጥሩ ዕድል ነው የሚኖረው”

ለማንኛውም ባለፉት ዓመታት ጀርመን ወደ ኢትዮጵያ የምታደርገው የውጭ ንግድ ቀጣይ ዕድገት እንደታየበት የአገሪቱ ፌደራል የሰንጠረዥ ቢሮ ያወጣው መረጃ ያመለክታል። ጀርመን ባለፈው 2008 ዓ.ም. 108,3 ሚሊዮን ኤውሮ የሚያወጣ ምርት ለኢትዮጵያ ስትሸጥ ይህም ቀደም ካለው ዓመት ሲነጻጸር ወደ 16 ሚሊዮን ገደማ የላቀ መሆኑ ነው። በተመሳሳይ ጊዜ ጀርመን ከኢትዮጵያ ያስገባችው ምርት ዋጋ ደግሞ 107,4 ሚሊዮን ኤውሮ የሚጠጋ ነበር። ድርሻው ከሞላ ጎደል ተመጣጣኝ ነው። በነገራችን ላይ ጀርመን ባለፈው 2008 ዋነኛዋ የኢትዮጵያ ምርት ገዢም ነበረች።

በተለይ ወደ አገር የምታስገባው ቡና ከዚህ ምርት የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ ከሰላሣ በመቶ በላይ የሚሆነውን ድርሻ ይይዛል። ኢትዮጵያ በአንጻሩ ከጀርመን የምትገዛው የምርት መኪናዎች፣ ሞተሮች፣ ተሽከርካሪዎች፣ ንጥረ-ነገሮችና መድሃኒቶች ናቸው። አሁን ደግሞ የጀርመን ኩባንያዎች በተለይ በአበባና በቆዳ ምርት ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ። የምርት ተግባራቸውን ወደ ኢትዮጵያ ለማሻገር የተቃረቡ ኩባንያዎች መኖራቸውም ነው የሚነገረው። ለጀርመን ኩባንያዎች ይበልጥ በኢትዮጵያ ማተኮር ዶር/ ራትሲንገር እንደሚሉት ሌላም ምክንያት አልታጣም።

“ኢትዮጵያ ውስጥ ለኩባንያዎቹ ተስማሚ የሆነ ጥሩ ሁኔታ አለ። ጠቅላላው የአየር ሁኔታ ለምግብ ምርትና ለተክል አመቺ ነው። ኢትዮጵያ ለጀርመን በተለይ በቡናው ንግድ መስክ ትልቅ ሽሪክ ናት። እንግዲህ በአጠቃላይ በእርሻ ልማቱ ዘርፍ የአየሩ ሁኔታ ተስማሚ ነው። ከወጪም አንጻር እንዲሁ! አገሪቱ ከሌሎች የአፍሪቃ አገሮች ሲነጻጸር ለጀርመንና ለአውሮፓ ገበዮች መልክዓ-ምድራዊ ቅርበትም አላት። ይህን በሚገባ መጠቀም ይቻላል። ከዚሁ ሌላ በኢትዮጵያ የተሰማሩ ብዙ ኩባንያዎች በዚህና በሠራተኛው ምርታማነትም በጣም ደስተኞች ናቸው”

ከሁለት ዓመታት ገደማ በፊት ቢሮክራሲና ጭብጥ ዋስትና የሚሰጡ ደምቦች ይጎላሉ ሲሉ ገንዘባቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ በሥራ ከማዋል መቆጠብ የሚመርጡ የጀርመን ባለሃብቶች አዘውትረው ቅሬታ ያሰሙ ነበር። ይህ ስጋት እርግጥ ዛሬም ጨርሶ አልተወገደም። ይሁንና የመሻሻል ሂደት ወይም ቢቀር ፍላጎት ይታያል ነው የሚባለው።

“በአጠቃላይ በስብሰባችን ላይ ግልጽ የሆነው የኢትዮጵያ መንግሥት ለውጭ የመዋዕለ-ነዋይ አቅራቢዎች አስፈላጊውን ሁኔታ ለማመቻቸት በጣም እንደሚጥር ነው። ቢሮክራሲያዊ ጉዳዮች፤ ቢሮክራሲያዊ መሰናክሎች በእርግጥም አሉ። ግን ይህ በሌሎች ብዙ የአካባቢው አገሮችም ያለና የሚጠበቅም ነው። በአካባቢው የሚሰሩ ኩባንያዎች እርግጥ የራሳቸውን ልምድ ማድረግ አለባቸው። መሰናክሎቹን ለመወጣት መጣር ይኖርባቸዋል። ወሣኙ ነገር ሁልጊዜም መንግሥቱ ራሱ ችግሩን ለይቶ ማወቁና ሁኔታውን ለመለወጥ መሻቱ ነው”

የአንድ አገር የተረጋጋ ሁኔታም በረጅም ጊዜ ለሚፈለገው ትብብሩም ሆነ ዕድገት ታላቅ ጠቀሜታ አለው። ኩባንያዎችም ቢሆን በቅድሚያ የሚያስቡበት ጉዳይ ነው።

“ለአንድ ኩባንያ የተረጋጋ ሁኔታ፤ ማለት የተረጋጋ የፖለቲካና የሕብረተሰብ ማሕበራዊ ይዞታ ጠቃሚ እንደሆነ ግልጽ ነው። በሌሎች ብዙ አገሮችም በዚህ ረገድ ጉድለት እናያለን። እርግጥ ነው ሁኔታው በጀርመን ካለው ጋር የሚነጻጸር አይደለም። ግን ወሣኙ ነገር የመሻሻል ዕርምጃ መታየቱ ላይ ነው። ንግድን ማጠናከር፤ ለብልጽግና መሠረታዊ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት መጣሩ ነው። እና እነዚህ ጥረቶች አገሪቱ በአጠቃላይ በተረጋጋ ሁኔታ እንድታድግ ሊያደርጉ ይችላሉ። እንግዲህ አዎን፤ ችግሩ አለ። ሊተኮርባቸው የሚገቡ ሁኔታዎች አሉ። ሁኔታው እንደሌሎች አገሮች ቀላል አይደለም። ግን በሌላ በኩልም ገንቢ አዝማሚያ ሲኖር እያንዳንዱ ኩባንያ ይህን መመዘን ይኖርበታል”

በፍራንክፈርት-አም-ማይን በኢንዱስትሪንና ንግድ ም/ቤቱ የተካሄደውን ስብሰባ የጀርመን መንግሥታዊ የቴክኒካዊ ትብብር ድርጅት GTZ እና የጀርመን የአፍሪቃ ማሕበር አብረው ሲያዘጋጁ የሁለቱ መንግሥታት አምባሣደሮችና የኩባንያዎች ወኪሎችም ተሳትፈው ነበር። የኩባንያዎቹ ወኪል የሆነው ም/ቤት በያመቱ መላውን የዓለም አካባቢ የሚመለከቱ ዝግጅቶችን የሚያስተናግድ ሲሆን በአፍሪቃም ላይ በተከታታይ ያተኩራል። ኢትዮጵያን በተመለከተ ዓላማው በተጠቀሱት የስብሰባው አዘጋጆችና ተሳታፊዎች መካከል የግንኙነት መረቡን በማጠናከር በጀርመን ኩባንያዎችና በኢትዮጵያ መካከል ሽርክናውን ማሳደግ ነው።

MM/IHK/SL