1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን-አንጎላ የኤኮኖሚ ግንኙነት

ረቡዕ፣ ሰኔ 5 2005

በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም በተፈጥሮ ጸጋ ከታደሉት ቀደምት ሃገራት መካከል አንዷ የሆነችው አንጎላ ጀርመንን በመሳሰሉ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉ መንግሥታት ዘንድ የተለየ ትኩረት አግኝታ መቆየቷ ይታወቃል።

https://p.dw.com/p/18nte
ምስል DW/A. Cascais

የጀርመኗ ቻንስለር ወሮ/አንጌላ ሜርክል ከሁለት ዓመታት በፊት አገሪቱን ሲጎበኙ ከፕሬዚደንት ዶሽ ሣንቶሽ ጋር «የስልታዊ ሽርክና» ውል ተፈራርመው መመለሳቸውም የሚታወስ ነው። ይሁንና ትብብሩ ከዚያን ወዲህ የታሰበውን ያህል ስር እየሰደደ አልመጣም። በአንጻሩ ተጎታች ሆኖ ነው የሚገኘው።

በቀድሞይቱ የፖርቱጋል ቅኝ ግዛት ብራዚልንና ቻይናን የመሳሰሉት መንግሥታት ረዘም ያለና ሰፊ የትብብር ትስስር ሲኖራቸው የጀርመን ሚና እንግዲህ ዛሬም መለስተኛ ነው። በአትላንቲክ ጠረፍ ላይ የምትገኘው አንጎላ የምዕራባውያኑን ኩባንያዎች ትኩረት እየሳበች መምጣቷ ያለምክንያት አይደለም። በተለይም በአልማዝና በነዳጅ ዘይት የካበተች ሰፊ በሆነ ጥሬ ሃብት የታደለች አገር ናት።

አንጎላ ባለፉት አሥር ዓመታት ከፍተኛ የኤኮኖሚ ዕድገት ስታደርግ በጎርጎሮሳውያኑ 2012 ዓ-ም ብቻ አጠቃላይ ብሄራዊ ምርቷ በ 8,4 ከመቶ ጨምሮ እንደነበር የውጭ ንግድና የገበያ ይዞታ ታዛቢ የሆነው የጀርመን የንግድና መዋዕለ ነዋይ ተቋም GTAI ያቀረበው መረጃ ያመለክታል። ይህም አገሪቱ የፖለቲካው ነገር ይቅርና በኤኮኖሚ ረገድ ፈጣንና ከፍተኛ ዕድገት በማድረግ ላይ ለመሆኗ ጥሩ ምልክት ነው።

በፈላጭ ቆረጭ አገዛዝ የምትተዳደረው አንጎላ በዚሁ ዕርምጃዋ በዓለም ዙሪያ ፈጣን የኤኮኖሚ ዕድገት በማሣየት ላይ ከሚገኙት ሃገራት አንዷ መሆኗ ነው። የሆነው ሆኖ የጀርመንና የአንጎላ የጥቅም ግንኙነት ከተመሠረ ከሁለት ዓመታት በኋላም የተፈለገውን ያህል ጠንክሮ አይገኝም። ይህ ደግሞ ባለፈው ሣምንት ሉዋንዳ ላይ ተካሂዶ በነበረው አራት ቀናት የፈጀ የጀርመን-አንጎላ የኤኮኖሚ መድረክ ስብሰባ ላይ በግልጽ መታየቱ አልቀረም።

Angola Ricardo Gerigk Delegation der Deutschen Wirtschaft in Angola
ምስል DW/A. Cascais

ስብሰባው በዓይነቱ አምሥተኛው ሲሆን የተዘጋጀውም በጀርመን ኤኮኖሚ ዘርፍ የአፍሪቃ ማሕበርና በጀርመን ኤኮኖሚ ልዑካን ቢሮ ትብብር ነበር። መድረኩ ራሱን የጀርመንና የአንጎላ የንግድና የመዋዕለ ነዋይ ግንኙነነት አራማጅ ድልድይ አድርጎ ይመለከታል። በወቅቱ በዚህ መድረክ አማካይነት 50 የጀርመን ኩባንያዎችና 200 ገደማ የሚጠጉ በከፊል ከፍተኛ የሆኑ የአንጎላ ባለሥልጣናት በመድረኩ አማካይነት በግንቢያ፣ በመዋቅራዊ ልማት፣ በዕርሻ ልማትና በኤነርጂ አቅርቦት ዘርፎች ወቅታዊ በሆኑ ፕሮዤዎችና የመዋዕለ ነዋይ አቅርቦት ጉዳይ በጋራ ይሰራሉ።

እርግጥ በአንጎላም እንደ ብዙዎች የአፍሪቃ ሃገራት ሁሉ የውጭ መዋዕለ-ነዋይን በስራ ላይ ማዋል ቀላል ነገር አይደለም። ቢሮክራሲ፣ ሙስናና የንብረት ዋስትና እጦት ተስፋፍተው የቀጠሉ ነገሮች ናቸው። ግን ይህም ሆኖ የጀርመን ኩባንያዎች ተሥፋ ቆርጠው ጨርሰው ወደ ኋላ አላሉም። ዛሬ ጀርመን ከአፍሪቃ ሃገራት ጋር በምታደርገው የንግድ ልውውጥ አንጎላ ከደቡብ አፍሪቃና ከናይጄሪያ ቀጥሎ ሶሥተኛውን ቦታ ይዛ እንደምትገኝ የጀርመን ኤኮኖሚ ዘርፍ የደቡባዊው አፍሪቃ አካባቢ ተመልካች ተቋም ባልደረባ አንድሬያስ ቬንስል ያስረዳሉ።

«በወቅቱ በጀርመንና በአንጎላ መካከል ያለው ልውውጥ በያመቱ 800 ሚሊዮን ኤውሮ ገደማ ይጠጋል። ያለፉትን ስድሥት ዓመታት ሂደት ከተመለከትን የአንጎላው ልውውጥ የአሥር ዕጅ ዕድገት የታየበት መሆኑ ነው። እርግጥ በዓለምአቀፉ የንግድ ልውውጥ ረገድ ጀርመን አሁንም በአንጎላ ያላት ድርሻ ዝቅተኛ ይሆናል። ግን ከሣሃራ በስተደቡብ አፍሪቃ በሚደረገው የንግድ ልውውጥ አንጎላ በወቅቱ ሶሥተኛውን ቦታ ትይዛለች። ከደቡብ አፍሪቃና ከናይጄሪያ ቀጥላ ማለት ነው»

Santos Gourgel
ምስል António Cascais

ለንጽጽር ያህል የጀርመንና የአልጄሪያ የንግድ ልውውጥ ከአንጎላው ባለፈው ዓመት በእጥፍ ከፍ ያለ ነበር። ለትብብሩ መስፋፋት አንዱ መሰናክል የአንጎላ መንግሥት በውጭ የመዋይለ ነዋይ ባለቤቶች ላይ የጣለው ደምብ ነው። በዚሁ መሠረት የውጭ ባለሃብቶች አንጎላ ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በታች መዋዕለ ነዋይ ማድረግ አይፈቀድላቸውም።

«የውጭ ኩባንያዎች በአንድ ሚሊዮን ዶላር ይጀምሩ መባሉን አልስማማበትም። እኛ መለስተኛ ኩባንያዎች ነኝ። ሌላው ነገር የጉዞ ማቃለያ ዕርምጃም በጣሙን አስፈላጊ ነው።የቪዛ ፈቃድ ጥበቃው ሊያበቃ ይገባዋል። በዚሁ መጓተት የተነሣ ቀጠሮን አክብሮ በአገሪቱ የመገኘት ችግር አለ። በተቀረ ሰዉ ግሩም ነው። ዋና ከተማይቱ ውስጥ ተዘዋውሬያለሁ። ምንም ችግር የለም»

ይህን የሚሉት የኩባንያው ተጠሪ ጉንተር-ፔተር-ስቶርቤክ ናቸው። በሌላ በኩል የአንጎላ መንግሥት የግል መዋዕለ ነዋይ ተቋም ሃላፊ ሆሴ ቺኛምባ እንደሚሉት እስከ አሥር ሚሊዮን ዶላር ለሚደረግ መዋዕለ ነዋይ ያለ ብዙ ቢሮክራሲ ፈቃድ ማግኘት ይቻላል።

ከዚያ በላይ ያለው ግን የአንጎላን የምጣኔ ሐብት ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ተጨማሪ ፈቃድ የሚጠይቅ ነው። ይህ ደግሞ 50 ከሚሆኑት የጀርመን-አንጎላ የጋራ መድረክ ተሳታፊዎች አንዱ ጉንተር-ፔተር-ስቶርቤክ እንደሚናገሩት ቀላል ነገር አይደለም።

መካከለኛቹ የጀርመን ኩባንያዎች ሊቋቋሙት አይችሉም። ስቶርቤክ የሚወክሉት የሃምቡርጉ GFA ኩባንያ እስካሁን ለደቡብ አፍሪቃ፣ ለዚምባብዌና ለቦትሱዋና የግንቢያ መኪናዎችን በማቅረብ የታወቀ ሲሆን አሁን በአንጎላ ላይ ማተኮሩ ተግባሩን አዲስና አጋዲ ወደሆነው ገበያ ለማስፋፋት በማሰቡ ነው። በጥቅሉ የጀርመኑ ኩባንያ ተጠሪ አንጎላ ውስጥ ምንም እንኳ ችግር ቢኖርም ዕርምጃውን ተሥፋ ሰጭ አድርገው መመልከታቸው አልቀረም።

«አንጎላ በጣም በተፋጠነ ሁኔታ በማደግ ላይ ያለች ሃገር መሆኗን ታዝበናል። ዕርምጃው በየቦታው ጎልቶ የሚታይ ነገር ነው። በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም በንጽጽር ሲታይ በአንጎላ ጥሩ መዋቅራዊ ይዞታ አለ። ከዚህ ባሻገር ደግሞ በአገሪቱ ሰፊ ጥሬ ሃብት ሲኖር የኤኮኖሚው ዕድገት ባለፉት አሥር ዓመታት እጅግ ከፍተኛ ሆኖ ነው የቆየው። በጥቅሉ አገሪቱ ችግር አይጣት እንጂ ለኩባንያዎች ማራኪ ናት»

Infografik Afrikas Rohstoffe Angola Deutsch

አንጎላ እንግዲህ በተፋጠነ ዕድገቷ የውጭ ኩባንያዎችን በጣሙን የምትስብ ስትሆን በሌላ በኩል ግልጽነት ቢኖር የሚመኙት ብዙዎች ናቸው። አገሪቱ ወደፊት ለመራመድ ያላት ፍላጎት እጅግ ከፍተኛ ነው። አገሪቱን ለመጀመሪያ የጎበኙት የጀርመን ኤኮኖሚ ዘርፍ የአፍሪቃ ማሕበር ባልደረባ ክሪስቶፍ ካነንጊሰርም ችግር ያለባት ሃገር ሆኖም ለኩባንያዎች የተፈጠረች ብለዋታል።

አንጎላ ውስጥ ባለፈው ሣምንት ተካሂዶ በነበረው የጀርመን-አንጎላ የኤኮኖሚ መድርክ ስብሰባ ላይ የተንጸባረቀው አብዛኞቹ የንግድ ሰዎች ከአጭር ጊዜ ጥቅም ባሻገር ረጅምና ዘላቂ መዋዕለ ነዋይ ለማድረግ እንደሚፈልጉ ነው። ይህም የአካባቢ ተፈጥሮንና ማሕበራዊ ልምዶችን ማክበርን፣ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ማድረግንና ሲቪሉን ሕብረተሰብ ማገዝን ይጠቀልላል። ግን ይህ ፈላጭ ቆራጭ የሆነ አገዛዝ ባለበት አገር ውስጥ ቀላል ነገር አይሆንም።

የቀድሞይቱ የፖርቱጋል ቅን ግዛት በፖለቲካ ረገድ ከዴሞክራሲ የራቀች ናት። ፕሬዚደንት ሆሴ-ኤዱዋርዶ-ዶሽ-ሣንቶሽ በሥልጣን ላይ 34 ዓመታት አሳልፈዋል። ዛሬም አልበቃቸውም። በዚህ ከሶሥት አሠርተ-ዓመታት በላይ በዘለቀው የአገዛዝ ዘመናቸው ደግሞ አስተዳደራቸው ከሙስናና ከጭቆና ጽዱ የሆነበት ጊዜ አይታወቅም። የጀርመን ኤኮኖሚ ዘርፍ የደቡባዊው አፍሪቃ ተቋም ባልደረባ አንድሬያስ ቬንስልም ይህንኑ ነው የሚያረጋግጡት።

«አንጎላ በብዙ ዘርፎች እኛ የምንሻውን ያህል ገና ግልጽነት አይታይባትም። ይህ ትብብር የጀርመን ኩባንያዎች በጣሙን የሚፈልጉት ነው»

ግልጽነት ከተነሣ ቻንስለር አንጌላ ሜርክል ከሁለት ዓመታት በፊት አንጎላን በይፋ ሲጎበኙ የጦር መሣሪያ ንግድ በጊዜው ብዙ አነጋግሮ ነበር። አንጌላ ሜርክል ከፕሬዚደንት ዶሽ ሣንቶሽ ከተገናኙ በኋላም ነገሩን ለማለዘብ የተሸጡት ጠረፍን ለመጠበቅ የሚያገለግሉ መርከቦች መሆናቸውን ማስታወቃቸው ይታወሳል። ዛሬ ከሁለት ዓመታት በኋላ የአንጎላው የምጣኔ-ሐብት ሚኒስትር አብራሄዎ-ዶሽ-ሳንቶሽ-ጉርጌል ስለ ጦር መሣሪያ ሽያጭ ምንም ነገር አለማስታወሱን ነው የመረጡት።

«ዕውነቱን ለመናገር ስለ መሣሪያው ግዢ የማውቀው አንዳች ነገር የለም። ይልቁንም በሌሎች የኤኮኖሚ ትብብር ዘርፎች ላይ ብናተኩር ጥሩ ይመስለኛል»

ይሁንና የኤኮኖሚው ትብብር ፍሬያማና ዘላቂ ሆኖ እንዲስፋፋ ከተፈለገ ተገቢው መስፈርት ማሟላቱ ግድ ነው።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ