1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ኤኮኖሚ በአዲሱ ዓመት

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 24 2005

የአዲሱ 2013 ዓ-ም የጀርመን የኤኮኖሚ ሂደት ምን ሊሆን ይችላል? የኤኮኖሚ ጠበብት እንደሚሉት ከሆነ ጀርመን ዘንድሮ እንዳለፉት ዓመታት በዓለምአቀፍ ደረጃ ከሚታየው ድክመት ተጽዕኖ የምታመልጥ አትሆንም።

https://p.dw.com/p/17CXC
ምስል dapd

የአዲሱ 2013 ዓ-ም የጀርመን የኤኮኖሚ ሂደት ምን ሊሆን ይችላል? የኤኮኖሚ ጠበብት እንደሚሉት ከሆነ ጀርመን ዘንድሮ እንዳለፉት ዓመታት በዓለምአቀፍ ደረጃ ከሚታየው ድክመት ተጽዕኖ የምታመልጥ አትሆንም። እርግጥ የተወሰኑ የዕድገት ተሥፋ የሚታያቸው ባለሙያዎችም አልጠፉም። በነዚህ ዕምነት ጀርመን በአዲሱ ዓመት ካለፈው አነስ ባለ መጠን ቢሆንም መልሳ ዕድገት ማሳየቷ የሚጠበቅ ነው። በአብዛኞቹ የጀርመን ኩባንያዎች ዘንድ ያለው የተሥፋ ስሜትም ከሞላ ጎደል ባለበት ነው የቀጠለው ለማለት ይቻላል።

ይሁንና የጀርመን የምጣኔ ሃብት ኢንስቲቲዩት በዘርፉ ያካሄደው አዲስ መጠይቅ ውጤት እንደሚያመለክተው አጠቃላይ የተሥፋ ስሜት ይኑር እንጂ ኩባንያዎች የአዲሱን ዓመት ሂደት የሚያስቡት በስጋት መንፈስ ነው። ለዚሁ ምክንያቱም ከሁሉም በላይ ማሰሪያ ያጣው የኤውሮ አካባቢ የዕዳ ቀውስ ሆኖ ይገኛል። የጀርመን ኤኮኖሚ ዘርፍ ለነገሩ በጋራ ጥቅምን በማስጠበቁ ረገድ በሚገባ የተደራጀ ነው። ይህም የጥንካሬው መለያ ሆኖ ይታያል።

እያንዳንዱ ቅርንጫፍ የራሱ ማሕበር ሲኖረው ለምሳሌ የጀርመን ኢንዱስትሪን ፌደራል ማሕበር የመሰለ ጣራ ድርጅትም አለው። ማሕበራቱ ዓባል ኩባንያዎችን የሚያማክሩ ሲሆን የጋራ መርህን በማስፈንና ድጋፍን በማሰባሰብም የሚረዱ ናቸው። ማሕበራቱና ኩባንያዎቹ የጀርመን ምጣኔ-ሃብት ኢንስቲቲዩት በመባል የሚታወቅ ለዘብተኛና ለአሠሪዎች የቀረበ የምርምር ተቋምም በገንዘብ ያግዛሉ። እንግዲህ ግምትም ሆነ ውጥናቸው በጥናት ላይ የተመሠረተ፤ የተሰላ መሆኑ ነው።

Bildergalerie Deutsche Maschinenbauer
ምስል SICK AG

የጀርመን ምጣኔ-ሃብት ምርምር ኢንስቲቲዩት በዓመት አንዴ በማሕበራቱና በዓባል ኩባንዮቻቸው ሁኔታ ላይ መጠይቅ ያደርጋል። አሁን በቅርቡም እንዲሁ! የዚሁ ውጤቱ ደግሞ ብዙም አበረታች ሆኖ አልተወሰደም። እንደሚባለው ሁኔታው በአዲሱ ዓመት ቢብስ ወይም ባለበት ቢቀጥል ነው። የኢንስቲቲዩቱ ሃላፊ ሚሻኤል ሁርተር እንደሚያስረዱት ከሆነ እመርታን የሚጠብቅ ማንም የለም።

«ከ 2009 ዓ-ም ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድም ዘርፍ ከተገባደደው ዓመት የተሻለ ሁኔታ ከማይጠብቅበት ውጤት ላይ ደርሰናል»

ለጀርመን ኩባንያዎች ትልቅ የራስ ምታት የሆነው በተለይም የኤውሮ ዞን የበጀት ቀውስ ነው። የሆነው ሆኖ ሁኔታው ሊከፋ እንደሚችል የሚያምኑት ከ 46 መጠይቅ ከተደረገላቸው ኩባንያዎች መካከል 11 የሚሆኑት ናቸው። በሌላ በኩል ሃያ የሚሆኑት ከአዲሱ ዓመት የተሻለ ዕርምጃ ነው የሚጠብቁት። እንግዲህ ስጋቱ ከሁኔታው ይልቅ የተጋነነ ነው የሚመስለው።

«በኩባንያዎቹ ዘንድ ያለው ሰሜት ካለፈው ዓመት ሲነጻጸር በከፊል ገደብ ያለ ሆኖ ነው የሚገኘው። ሌላው ጠቃሚው ነገር፤ የምርቱ ግምት፣ የሚጠበቀው መዋዕለ-ነዋይና የሥራ መስኩ ሁኔታ ግን ጥንካሬ የሚታይበት ነው»

የጀርመን ምጣኔ-ሃብት ምርምር ኢንስቲቲዩት ሃላፊ ሚሻኤል ሁርተር ገደብ ባለው ሰሜትና ጠንካራ ሆኖ በሚገኘው አንጻራዊ የንግድ ይዞታ መካከል የሚታየውን ቅራኔ በዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ልምዶች ላይ በመመርኮዝ ለማብራራት ይሞክራሉ።

«ኩባንያዎቹ በጣሙን ጥንቁቅ ወይም ቁጥብ ሲሆኑ እንዳይደርስ የሚፈልጉት አንድ ነገር አለ። ሁሉም ነገር ከዕጅ እየሾለከ የሄደበት፤ የዓለም ኤኮኖሚ ዕርምጃ ቀጥ ያለበት የ 2008 መገባደጃና የ 2009 መጀመሪያ ሁኔታ እንዲደገም አይፈልጉም። ይህ ገና የሩቅ ታሪክ አይደለም። እናም ኩባንያዎቹ ከቀድሞው ይልቅ ቁጥቦች ናቸው። ይህም ከሁኔታው አንጻር አግባብ የለሽ ሆኖ ሊታይ አይችልም። በአጠቃላይ ካለፈው የመማርና የመጠንቀቅ ሁኔታ ነው ሰፍኖ የሚገኘው»

Bildergalerie Deutsche Maschinenbauer Best of German Engineering
ምስል SEW-EURODRIVE GmbH & Co KG, Bruchsal

በዓባል ኩባንያዎች ውስጥ የሥራ ቦታዎች እየቀነሱ እንደሚሄዱ ከሚያምኑት ማሕበርት መካከል ማዕድን፣ የሕትመት ኢንዱስትሪ፣ ባንኮችና የኤነርጂው መስክ ይገኙባቸዋል። በተለይ በኤነርጂ ኩባንያዎች ዘንድ ለተከሰተው የተሥፋ እጦት ሁኔታ ሁርተር የፖለቲካውን ዘርፍም ተጠያቂ ያደርጋሉ።

«የኤነርጂ ለውጥ ለማካሄድ መወሰኑንና ነገር ግን መንግሥት የራሱን ውጥን ገቢር ሊያደርግ አለመቻሉ ሲታሰብ መዋዕለ-ነዋይ አቅራቢዎች ምን ያልተጠበቀ ችግር ሊግጥመን ይችላል ብለው መስጋታቸው የሚያስደንቅ አይሆንም። የፖለቲካው ዘርፍ ሚና አሁን በዘመነ ግሎባላይዜሽንም ከፍተኛ መሆኑ መዘንጋት የለበትም። የፖለቲካው ዘርፍ በጀርመን የምርት ቦታዎች ጸንተው በመቆየታቸው፤ በአገር ውስጥ የሥራ ቦታዎችን ለመፍጠር በዓለምአቀፍ ደረጃ ለፉክክር በመብቃታችን ላይም ወሣኝ ነው»

በሌላ በኩል የአውቶሞቢል፣ የኤሌክትሮኒክና የምርት መኪና ኢንዱስትሪዎች የወደፊቱን የሚመለከቱት በታላቅ ተሥፋ ነው።

«በጥቅሉ ሲታይ የጀርመን ኤኮኖሚ መንኮራኩር የሆነው የኢንዱስትሪው ዘርፍ ጠንካራና በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ነው። በተለይም በምርት መኪናው ኢንዱስትሪ ዘርፍ ምርቱ እንደሚያድግና መዋዕለ-ነዋይም እንደሚጨምር እንጠብቃለን። እንግዲህ ወደ ላይ ከፍ አድርገን ነው የምንመለከተው። በሥራ ቦታዎች ሁኔታም እዚህ ሁኔታው የጠነከረ ነው»

ባለፈው 2012 ዓ-ም የጀርመን ኤኮኖሚ ጠንከር ብሎ ከጀመረ በኋላ ወደመጨረሻው ለዘብ ሲል ዘንድሮ ደግሞ ሂደቱ የተገላቢጦሽ እንደሚሆን ነው የሚታመነው። የጀርመን ምጣኔ-ሃብት ምርምር ኢንስቲቲዩት የዚህ ዓመት ዕድገት በሁለተኛው አጋማሽ ላይ ጎልቶ እንደሚታይ ይገምታል። የሚጠበቀው ካለፈው ያነሰ 0,7 ከመቶ የኤኮኖሚ ዕደገት ነው።

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ለጀርመን ኩባንያዎች የዕድገት ተሥፋ መለዘብና ስጋት ምክንያት የሆነው በተለይም የኤውሮ ምንዛሪ ሃገራት መንግሥታዊ የዕዳ ቀውስ ማለቂያ ማጣት ነው። ጉዳዩ አከራካሪ ሲሆን በዘመን መለወጫው ዋዜማም ጎላ ባለ መልክ የኤኮኖሚ ጠበብትን ለሁለት ከፍሎ ታይቷል። አንዳንዶች የኤውሮው ቀውስ በአብዛኛው ተወግዷል የሚሉ ሲሆን ሌሎች ደግሞ የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ የመንግሥታት ዕዳን በመሸከም የያዘው መፍትሄ ፍለጋ ዘግየት ብሎ ብርቱ ችግርን ሊያስከትል እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ።

Bundesbankpräsident Jens Weidmann
ምስል DW

ይህን ማስጠንቀቂያ ከሚሰነዝሩት መካከል አንዱ የዶቼ ባንክ አስተዳዳሪ የንስ ቫይድማን ናቸው። እንደርሳቸው ከሆነ የቀውሱ መንስዔ ገና አልተወገደም። እርጋታ አይጠበቅም ማለት ነው። ታዲያ የኤውሮ ዞን ሁኔታ እንዴት ሊቀጥል ይችላል? የኤውሮ ዋጋ የመውደቅ አደጋስ እስከምን ድረስ ነው? ይህም የሃሣብ ልዩነት የበዛበት ጉዳይ ሆኖ ነው በወቅቱ የሚታየው።

ያለፈው 2012 ዓ-ም በአውሮፓ ሕብረት ላይ መሪር ልምድ ጥሎ ያለፈ ነበር ለማለት ይቻላል። የዕዳ ቀውስ ለተጫናቸው ግሪክን ለመሳሰሉት ሃገራት መዓት ገንዘብ ቢፈስም የምንዛሪው ሕብረት መሠረታዊ ችግር፤ ማለትም የዓባል ሃገራቱ የኤኮኖሚ አቅም ልዩነት እየሰፋ መሄድ መፍትሄ አላገኘም። እስካሁን እንደታየው ሃቁ ይህን ይመስላል። ደካሞቹ ሃገራት ጠንከር ካሉት ዕርዳታ ይፈልጋሉ። ግን የኋለኞቹ ገንዘብ ለመስጠት ዝግጁ የሚሆኑት በተረጂዎቹ ላይ የቁጠባ ደምብ መጫን እስከቻሉ ድረስ ብቻ ነው።

ዕርዳታ ተቀባዮቹ ደግሞ ይህን ፍትሃዊ አድርገው አይመለከቱም። ግፊቱን በውስጣዊ የበጀት ጉዳይ ጣልቃ እንደመግባትና መብትን እንደመግፈፍ አድርገው ነው የሚቆጥሩት። ታዲያ በወግ አጥባቂው የብሪታኒያ የአውሮፓ ፓርላማ ዓባል በማርቲን ካላናን አመለካከት ሕብረቱን ጠምዶ የሚገኘው ዋናው መሰናክልም ይሄው ነው።

«አንዱ ወገን ሉዓላዊነቱን ሌላው ደግሞ ገንዘቡን አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ ባልሆነበት ሁኔታ ከተፈጠረው መሰናክል መውጣት አልቻልንም»

እርግጥ ካላናን አገራቸው የኤውሮ ምንዛሪ ሕብረት ዓባል ባለመሆኗ ጉዳዩን ለዘብ ባለ ገለልተኛ መንፈስ ነው የሚመለከቱት። በሌላ በኩል ለጀርመን ችግሩ መፍትሄ ማግኘቱ ማዕከላዊ ጉዳይ ነው። በመሆኑም ቻንስለር አንጌላ ሜርክል የምንዛሪው ሕብረት ምሥረታ ወቅት ስህተቶች መታረም እንዳባቸው ነበር በቅርቡ ያስገነዘቡት።

«ኤውሮን እንደ ጋራ ምንዛሪ ማቆየት ብቻ ሣይሆን መሠረቱን ማጠናከር በማሰፈለጉ ረገድ የጋራ ፍላጎት መኖሩን ባለፉት ወራት በግልጽ ለማየት የቻልን ይመስለኛል። ይህ በግሪክና በሌሎች በርከት ባሉ ምሳሌዎች ያየነው ጉዳይ ነው። በሁለተኛ ደረጃም ዓባል ሃገራቱና ሕብረቱ በጥቅሉ ስር ነቀል ለውጥ ለማካሄድ ዝግጁ እንደሆኑ አምናለሁ»

ያም ሆነ ይህ የኤውሮ የዕዳ ቀውስ መቼ መፍትሄ እንደሚያገኝ እንዲህ ብሎ ጭብጥ ጊዜ መጥቀስ ያዳግታል። ምናልባትም ገና ጊዜ የሚፈጅ መሆኑን ነው መናገሩ የሚቀለው። ይህ እስከሆነ ድረስ፤ ማለትም ቀውሱ ባለበት እስከቀጠለ ድረስ የአውሮፓ የዕድገት መንኮራኩር ሆና በቆየችው በጀርመን የኤኮኖሚው ዘርፍ ስጋት እየጠነከረ የሚሄድ ነው የሚመስለው። በሌላ በኩል የአገሪቱ የምጣኔ-ሃብት ምርምር ኢንስቲቲዩት እንደሚገምተው በአዲሱ ዓመት ከአንድ በመቶ ያነሰም ቢሆን ዕድገት ከታየ የኤኮኖሚው ጥንካሬ ባለበት እንደቀጠለ የሚያረጋግጥ ምልክት ነው የሚሆነው።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ