1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ኤኮኖሚ ወቅታዊ ይዞታ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 10 2003

በዓለምአቀፉ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ ባለፈው ዓመት አቆልቁሎ የነበረው የጀርመን ኤኮኖሚ መንኮራኩር የሆነው የውጭ ንግድ በዚህ ዓመት መልሶ ከፍተኛ ዕድገት እየታየበት ነው።

https://p.dw.com/p/PjFV
ምስል picture-alliance/ dpa

በዚሁ በውጭ ንግድ ላይ ጥገኛ የሆነው የጀርመን ኤኮኖሚም ዘንድሮ ከሌሎች ከበለጸጉ መንግሥታት አንጻር እጅግ በላቀ ሁኔታ ከሶሥት በመቶ በላይ ዕድገት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። እርግጥ ሂደቱ በተለይ በአሜሪካ ኤኮኖሚ መልሶ ቀውስ ላይ መውደቅ መቻል የተነሣ ጨርሶ ከአደጋ የተላቀቀ አይደለም። በሌላ በኩልም የሠለጠነ የሥራ ሃይል እጥረት ፈታኝ ደረጃ መድረስ በተለይም ለአምራቹ የኢንዱስትሪ ዘርፍ የራስ ምታት እየሆነ ነው የሄደው። ይህ ሰሞኑን አጣዳፊ መፍትሄን የሚሻ የበርሊኑ መንግሥት መወያያ ጉዳይ ሆኖም ይገኛል።

ባለፈው 2009 ዓ.ም. የጀርመን ኤኮኖሚ መንኮራኩር፤ ማለት የአገሪቱ የውጭ ንግድ ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ባስከተለው መዘዝ ሳቢያ በአግባብ ከማይንቀሳቀስበት ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። በዚህ ዓመት ግን የዘርፉ አዋቂዎች እንደሚሉት ሁኔታው ወደ በጎው ተለውጧል ወይም ቢቀር እየተለወጠ ነው። የጀርመን የውጭ ንግድ መልሶ ማበብ ሲይዝ ሂደቱ የዘርፉ ፌደራላዊ ማሕበርም የወደፊቱን በተሥፋ እንዲመለከት አድርጓል። የማሕበሩ ፕሬዚደንት አንቶን በርነር እንደገለጹት የያዝነው 2010 ዓ.ም. ዕድገት በ 16 ከመቶ አዲስ ክብረ-ወሰን ላይ ሊደርስ መቻል ዘርፉን በጣሙን እያስፈነደቀ ነው።

“ለስኬቱ ዋናው ምክንያት በተፋጠነ ዕርምጃ ላይ የሚገኙት ሃገራት ጠንካራ የኤኮኖሚ ዕድገት ነው። በነዚህ ሃገራት፤ በቻይና፣ በደቡብ ምሥራቅ እሢያ፣ በሕንድ፣ በብራዚል ጥሩ ንግድ ነው የምናካሂደው። በተጠቀሱት አካባቢዎች የጀርመን መዋዕለ-ነዋይ ተፈላጊነት አልተዳከመም። ይልቁንም በጣሙን የተረጋጋ ሲሆን በዚሁ መቀጠሉም እርግጠኛ ነገር ነው”

ጀርመን በዚህ ሊገባደድ በተቃረበው ዓመት ከአውሮፓ ሕብረት ክልል ውጭ የምታካሂደው ንግድ 16 በመቶ ይደርሳል ተብሎ ነው የሚጠበቀው። እንደ አንቶን በርነር ትንበያ ከሆነ የውጩ ንግድ በቀጣዩ አዲስ ዓመት 2011 የመጀመሪያ አጋማሽ እንዲያውም ከዓለምአቀፉ ቀውስ በፊት ወደነበረበት ጥንካሬ ሊመለስ ይችላል። ለዚህም በተለይ ቀውሱን ተከትሎ መንግሥታት በብዙ ሚሊያርድ የሚቆጠር ገንዘብ በማፍሰስ ገቢር ያደረጉት የኤኮኖሚ ማነቃቂያ ዕቅድ የጀርመኑ የውጭ ንግድ ፌደራል ማሕበር ፕሬዚደንት አያይዘው እንደሚሉት ታላቅ አስተዋጽኦ ነበረው።

“እንግዲህ በሚቀጥለው ዓመት በውጭ ንግድ ታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ ቢሊዮን ኤውሮ በላይ የማስገባት ጥሩ ዕድል ነው ያለን። እንደሚታወሰው ይህ ዕድል ከቀውሱ በፊት በነበረው በጥሩው የኤኮኖሚ ዓመት 2008 ለጥቂት ነበር ያመለጠን”
ይሁንና በርነር እንደሚሉት ሂደቱ በውጩ ንግድ ላይ በጣሙን ጥገኛ ለሆነው የጀርመን ኤኮኖሚ አደጋን ሊያስከትልም የሚችል ነው። ለምሳሌ የአሜሪካ ኤኮኖሚ እንደገና ቀውስ ላይ ሊወድቅ መቻልና መልሶ መቀዝቀዝ ጎጂ ነገር ነው የሚሆነው።

“የዩ.ኤስ.አሜሪካ ኤኮኖሚ መቀዝቀዝ በቀጥታም ሀነ በተዘዋዋሪ በጀርመን ምርቶች ተፈላጊነት ላይ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል። በቻይናም የፊናንስ ገበያ ለውጥ አይኖርም አይባልም። ከዚሁ ሌላ በኤውሮ ክልል ውስጥ በሚገኙ አንዳንድ አገሮች የተከሰተው የዕዳና የዓመኔታ ችግር ገና እንዳልተወገደ መታሰብ አለበት”

የጀርመኑ የውጭ ንግድ ማሕበር ፕሬዚደንት ጎረቤት አገሮች ጀርመን ብዙ ወደ ውጭ በመነገድና በአንጻሩ ግን ጥቂት ወደ አገር በማስገባት የአውሮፓን ኤኮኖሚ ጉዳት ላይ እየጣለች ነው ሲሉ በቅርቡ የሰነዘሩትን ወቀሣ አግባብ የለሽ ሲሉ እንደገና አስተባብለዋል። በርነር በፌዝ መልክ የውጭ ንግድ እኮ ሃጢአት አይደለም ነው ያሉት።

“ጀርመን የአውሮፓ ሕብረት አጋሮቿ የውጭ ንግድ መንኮራኩር ናት። ከነዚሁ አገራት የምታስገባው ምርትም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ወደዚያ ከምትልከው ይልቅ በጣሙን ነው የጠነከረው። ከዚሁ ሌላ በዓለም ዙሪያ ተሰማርተው የሚገኙት የጀርመን ኩባንያዎች በአዳጊዎቹ ገበዮች ለሕብረቱ ጎረቤት ሃገራት ምርት አቅራቢዎች በር ከፋች መሆናቸው መዘንጋት የለበትም። እና ያለ ጀር,መን የውጭ ንግድ ጥንካሬ የአውሮፓ ኤኮኖሚ ይዞታ የባሰ የከፋ በሆነ ነበር። በተለይ ደግሞ አንዳንዶቹ አገሮች ከቀውሱ በመውጣቱ ረገድ አዝጋሚ መሆናቸው ሲታይ”

Ausländer und Deutsche in der Wirtschaft
ምስል dpa Zentralbild

እርግጥ ነው የጀርመንን የውስጥ ፍጆታም መዋዕለ-ነዋይን በማፍሰስ ማጠናከሩ አስፈላጊ በመሆኑ ሃሣብ በርካታ የኤኮኖሚ ጠበብት ይስማማሉ። በበርነርም ዕምነት በወጪውና በገቢው ንግድ መካከል ሚዛን ለመጠበቅ የሚቻለው እንዲህ ነው። አንቶን በርነር በጀርመን የሥራ ገበያ ላይ የተደቀነውን የሠለጠነ ሃይል እጥረት አደጋ በማንሣትም አገሪቱ ከዛሬው የበለጠ በሰፊው መጤዎችን ማስገባት እንዳለባት አስገንዝበዋል።
ጀርመን እስካሁን በቢሮክራሲና ባሕላዊ መሰናክሎች የተነሣ ከፍተኛ ዕውቀት ያላቸውን ሙያተኞች በመሻማቱ በኩል በዓለምአቀፍ ንጽጽር ደካማ ሆና ነው የቆየችው። በዚህ በኩል የተሻለ ለውጥ ካልተደረገ የሥራ ሃይሉ እጥረት የአገሪቱን የኤኮኖሚ ዕድገት የሚያሰናክል ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም። የጀርመን የንግድና ኢንዱስትሪ ም/ቤት በቅርቡ ባካሄደው መጠይቅ እንዳረጋገጠው ከአገሪቱ ኩባንያዎች ሰባ በመቶው ከአሁኑ በአጠቃላይ ወይም በከፊል ተስማሚ ባለሙያዎችን ለመቅጠር ችግር አለባቸው። ይሄው ችግር ከኤኮኖሚው ዕድገት ጋር እየጨመረ መቀጠሉም የማይቀር ነገር ነው።
የኢንዱስትሪው ዘርፍ ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ ጉዳዩን በማንሣት መወትወቱ ባይቀርም ከፖለቲካው አንጻር ግን ችግሩን የሚያቃልል ቁርጠኛ ዕርምጃ ተወስዷል ለማለት አይቻልም። አሁን በአንጻሩ የጀርመን መንግሥት ለመጤዎች በአገሪቱ የሥራ ገበያ ላይ ያለውን ሁኔታ ለማቃለል መነሣቱ እየተነገረ ነው። በተለይም መጤዎች በአገራቸው ያፈሩት የሙያ ሥልጠና ወይም ከፍተኛ ትምሕርት በዚህ በጀርመን ዕውቅና አለማግኘቱ ከሩብ ሚሊዮን ለሚበልጡ ሰዎች መሰናክል ሆኖ ሲቆይ አሁን ይሄ የሚለወጥበት አዲስ ሕግ እንዲሰፍን ጭብጥ ጥረት ይደረጋል እየተባለ ነው።

ከነዚህ መጤዎች ብዙዎቹ አንዴ ሃኪሞች፣ ኢንጂነሮች ወይም መምሕራን ነበሩ። ሆኖም በዚህ በጀርመን የትምሕርት ደረጃቸው ዕውቅና በማጣቱ የተወሰኑት በታክሲ ነጂነት ወይም በምግብ ቤት አስተናጋጅነት ይሰራሉ፤ ያላንዳች ሥራ በመንግሥት ድጎማ የሚተዳደሩትም ብዙዎች ናቸው። በተማሩት ሙያ ሊሰሩበት አልቻሉም ማለት ነው። የመጤዎች ይዞታና ከሕብረተሰብ መዋሃድ ጉዳይ አጥኚ ም/ቤት በጉዳዩ ባቀረበው ዓመታዊ ዘገባ ሁኔታውን “ከንቱ የዕውቀት ብክነት” ብሎታል። በሌላ በኩል የበርሊኑ ጥምር መንግሥት በአዲሱ ዓመት በሚሰፍን አዲስ ሕግ ሁኔታውን ለመለወጥ ቆርጦ መነሣቱን ነው ሰሞኑን ያመለከተው። እንደ ነጻ ዴሞክራቱ ፖለቲከና እንደ ሤርካን ቱረን ከሆነ ደግሞ ሕጉ የትምሕርት ደረጃን ዕውቅና የማስገኘት የመጤዎችን መብትም የሚጠቀልል ነው።

“ብዙ ባለሙያዎች፤ ኢንጂነሮችና ሌሎችም አሉን። የምስክር ወረቀታቸው ዕውቅና ባለማግኘቱ የተማሩትን በሥራ ላይ ለማዋል አይችሉም። እናም ለውጡ ቢመጣ የሙያተኛውን እጥረት ስለሚያለዝብ ለኛ ለኤኮኖሚያችንም እጅግ የሚጠቅም ነው የሚሆነው። ለመጤዎቹ ለራሳቸው ደግሞ ከማሕበራዊ ድጎማ መላቀቅ ወይም ወደ ከፍተኛ የሥራ ደረጃ መሸጋገር ማለት ነው። እንግዲህ ዕርምጃው እስካሁን የምሥክር ወረቀቶቻቸውን ሊጠቀሙ ያልቻሉትን መጤዎች ሁኔታ የሚያቃልል ይሆናል”

በወቅቱ ዕውቅና የመስጠቱን ምርመራ የማካሄዱ ተግባር በተለያዩ የመንግሥት ዘርፎችና ቢሮዎች ተከፋፍሎና ተበጣጥሶ ነው የሚገኘው። የአካዳሚ ትምሕርት ምሩቃን ከሆኑ ሃላፊነቱ የፌደሬሺኑ ነው። ሃኪሞችን በተመለከተ የሙያው ማሕበራትና ሸንጎዎች አብሮ ወሣኞች ናቸው። የእጅ ሥራ ደግሞ በአካባቢ የሙያው ም/ቤቶች ነው የሚታየው። ይህ ታዲያ ከባድ የቢሮክራሲ አሠራርን ማስከተሉ አልቀረም። በመሆኑም ወደፊት አዲሱ ሕግ ሲሰፍን በየመስተዳድሩ ለሁሉም ነገር አንድ ቢሮ እንዲኖር ለማድረግ ይታሰባል። ይህም አመልካቹ በተፋጠነ ሁኔታ ቢበዛ በግማሽ ዓመት ጊዜ ውስጥ መልስ እንዲያገኝ መብት የሚሰጥ ነው።

“ለምሳሌ አንድ ሰው የውጭ አገር የሃኪም ዲፕሎም ካለው ይህ ሙሉ በሙሉ ዕውቅና አያገኝም። ሆኖም ግን በመንከባከቢያ ወይም መሰል ዘርፎች ተቀባይነት ይሰጠዋል። እርግጥ የሚቻል ከሆነ! እንግዲህ ከፊል ዕውቅና ይኖራል ማለት ነው። ከባለሥልጣኑም በኩል መጤው የሚቀሩት ምርጫዎች ካሉ መገለጽ ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ ለዕውቅና የሚያበቃ ተጨማሪ ሥልጣና ካስፈለገ!”

ያም ሆነ ይህ ሃቁ በጀርመን በከፍተኛ ሙያ የሠለጠኑ ሠራተኞች እጥረት መኖሩና አሳሳቢም መሆኑ ነው። ኤኮኖሚው ደከም ባለበት ባለፈው 2009 ዓ.ም. 34 ሺህ የኢንጂነርና የኤሌክትሮኒክ ጠበብት የሥራ ቦታዎችን ለመሙላት አልተቻለም። ባዶዎች ነበሩ። ሕብረተሰቡ እያረጀ በሚሄድባት በጀርመን በቂ ልጆች ስለማይወለዱም የሙያተኛው እጥረት ወደፊትም እየከፋ የሚሄድ ነው የሚሆነው። ለምሳሌ የአንጋፎች እንክብካቤ ሠራተኞች እጥረት ገና ከዛሬው ብዙ ያሳስባል። በአጠቃላይ ወደ ኤኮኖሚው መለስ ብንል የአገሪቱ የምጣኔ-ሐብት ዕድገት ቀጣይነት እንዲኖረው በአስቸኳይ ጭብጥ ለውጥ መስፈኑ ግድ ነው የሚሆነው።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ