1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ተልዕኮ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 7 2006

የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ግጭት ተባብሶ እንደቀጠለ ነው ። የርስ በርስ ግጭቱን ለማስቆም እዚያ የሚገኘውን የፈረንሳይና የአፍሪቃ ህብረት ኃይል ለማገዝ የአውሮፓ ህብረት ወታደሮችን ለመላክ በዝግጅት ላይ ነው ። በዚሁ ዘመቻ ጀርመን ተካፋይ ብትሆንም ተሳትፎዋ መገደቡ ግን አስተችቷታል።

https://p.dw.com/p/1BjCt
Zentralafrikanische Republik Bangui
ምስል Miguel Medina/AFP/Getty Images

ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ስምዋ እንደሚያመለክተው በአፍሪቃ እምብርት የምትገኝ ሃገር ናት በሰሜን ከቻድ በሰሜን ምሥራቅ ከሱዳን በምሥራቅ ከደቡብ ሱዳን በደቡብ ከኮንጎ ሪፐብሊክ በምዕራብ ደግሞ ከካሜሩን ጋር ትዋሰናለች ።ሃገሪቱ ወደ 620 ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያላት ሲሆን ከ4.4 ሚሊዮን በላይ ህዝብ መኖሪያም ናት ። የቀድሞዋ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ በጎርጎሮሳውያኑ 1960 ማለትም የዛሬ 54 ዓመት ነው ከፈረንሳይ ነፃ የወጣችው ።ከነፃነት በኋላ ሃገሪቱ ከ3 አሥርት ዓመታት በላይ ህዝብ ባልመረጣቸው ወይም ደግሞ በኃይል ሥልጣን በያዙ መሪዎች ስትተዳደር ቆይታ የመጀመሪያውን ምርጫ በጎርጎሮሳውያኑ 1993 ለማካሄድ በቃች ከዚያን ጊዜ አንስቶም እስከ 2011 ድረስ ምርጫዎች ሲካሄዱ ቆይተዋል ። በነዚህ ዓመታትም ሃገሪቱ ከግጭቶች ነ|ፃ አልነበረችም ። በምርጫ ሥልጣን የያዙት የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ቦዚዜ እጎአ መጋቢት 2013 በመፈንቅለ መንግሥት ከተወገዱ ወዲህ የሃገሪቱ ሰላም በእጅጉ ተናግቷል ። መፈንቅለ መንግሥቱን በተከተለውና በቀድሞዎቹ የሴሌካ አማፅያንና በአክራሪ ቡድኖች መካከል በቀጠለው ግጭት ብዙዎች ተገድለዋል ፣ ከሃገራቸውም ተፈናቅለዋል ። ግጭቱ እንደተከሰተ ብዙም ሳይቆይ የቀድሞዋ ቅኝ ገዥ ፈረንሳይ ወደ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ወታደሮችዋን ብታዘምትም ችግሩ እየተባባሰ ሄደ እንጂ አልቀነሰም ። ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ በመሄድ ላይ ያለው የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ቀውስ ለመታደግ የአፍሪቃ ህብረት 6 ሺህ ፈረንሳይ ደግሞ 2 ሺህ ወታደሮች አስፍረዋል ። ይህ ግን በቂ ሆኖ አልተገኘም ። ፈረንሳይ ባቀረበችው ጥያቄ መሠረት የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት 12 ሺህ ሰላም አስከባሪዎች እንዲዘምቱ ባለፈው ሳምንት ተስማምቷል ። ይህ ሠራዊት ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ የሚሰፍረው በመጪው መስከረም ነው ። እስከዚያው ድረስ ግጭቱን ለማብረድ የተሰማራውን የፈረንሳይና የአፍሪቃ ህብረት ኃይል ለማገዝ የአውሮፓ ህብረት ወደ 1 ሺህ የሚደርሱ ወታደሮችን ለመላክ በገባው ቃል መሰረት ወታደሮቹን ማዝመት ጀምሯል ። በዚሁ ሠራዊት ውስጥ ጀርመንም ወታደሮችን ለማዝመት ተስማምታለች ። ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የተሰበሰበው የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የጀርመን ወታደሮች ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ በሚዘምቱበት ሁኔታ ላይ መክሮ በቀረበው ሃሳብ ተስማምቷል ። በዚሁ መሠረት ጀርመን ለአውሮፓ ህብረት የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ተልዕኮ 80 ወታደሮችን ታዘምታለች ። ጀርመን ወታደሮቿን ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ልታዘምት ማቀዷን የጀርመን የግራዎቹ ፓርቲ ተቃውሟል ። የፓርቲው የመከላከያ ጉዳዮች ተጠሪ ክርስቲን ቡህሆልዝ ምክንያታቸውን ያብራራሉ ።

Anti-Balaka Kämpfer Bangui
ምስል DW/Scholz/Kriesch

«የፈረንሳይ ጣልቃ ገብነት ምን አምጥቷል ? ግድያው ቀጥሏል የተቀየረ ነገር ቢኖር የኃይል ሚዛን ለውጥ ብቻ ነው ። ፀረ ባላካ ክርስቲያኖች የፈረንሳዮች ጣልቃ ገብነት ሲጀመር የበላይነቱን ይዘዋል ። እነርሱ ደግሞ በበኩላቸው ሙስሊሞችን እያደኑ ነው ። በአሁኑ ጊዜ ሙስሊሞች በሙሉ በስደት ላይ ናቸው። በርካቶች ተገድለዋል ። የፈረንሳይ ጦር ይህን ማስቆም አልቻለም ወይም አልፈለገም ።በዚህ ጉዳይ ላይ እዚህ መነጋገር አለባችሁ ።»

ከተቃዋሚዎች በኩል ለቀረበው ለዚህ ትችት መጥፎ ልምድ አለ ተብሎ በመፍትሄው ከመሳተፍ ራስን ማራቅ እንደማይገባ ነው የጀርመን ሶሻል ክርስቲያን ህብረት ተጠሪ ራይንሃርድ ብራንድል የተናገሩት

« በሌላ በኩል ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ አንዲት ሃገር ቀስ በቀስ ወደ ዘር ማጥፋት ስትሸጋገር ዝም ብሎ መመልከት አይችልም ። ጉዳዩም በሃገሪቱ ማን ምን ዓይነት ጥቅም አለው ወይም ደግሞ ማን ምን ዓይነት ልምድ አለው አይደለም ። ከዚያ ይልቅ በተለይ የሃገሪውን ሰው ከግድያ ከዝርፊያ ና ከአስገድዶ መድፈር የመጠበቅ ጉዳዩ ነው ። »

Entwicklungsminister Gerd Müller Bangui Zentralafrika
ምስል picture-alliance/dpa

ቡህሆልዝ በአማራጭነት ሃገሪቱ ለዚህ ተልዕኮ የምታወጣውን ገንዘብ በሌላ መንገድ እንድታበረክት ሃሳብ አቅርበውም ነበር ።

«12 ሚሊዮን ዩሮ የሚስወጣውን የጀርመን የመከላከያ ሚኒስቴር ተልዕኮ አስቀርተን ገንዘቡን ለአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ማዋሉ ይሻላል ።»

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን UNHCR እንዳስታወቀው ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ውስጥ ቁጥራቸው ከ 19 ሺህ በላይ የሚሆን ሙስሊሞች ከክርስቲያን ተዋጊዎች ሊደርስባቸው በሚችል ጥቃት አደጋ ላይ ናቸው ። ድርጅቱ እንደሚለው የፈረንሳይ ወታደሮች በሃገሪቱ ባይኖሩ ምናልባትም እነዚህ ሰዎች በህይወት ላይገኙ ይችሉ ነበር ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው ግጭት ምክንያት አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ከሃገሪቱ መሰደዳቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል ። ቁጥሩ ወደ 1.3 የተገመተ ህዝብ ደግሞ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልገዋል ። የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ወታደሮች ለመላክ የተስማሙት ጥር አጋማሽ ግድም ቢሆንም አባል ሃገራት የሚያዋጡትን ወታደርና የሚያቀርቡትን መጓጓዣ መጠን ወዲያውኑ ከማሳወቅ ተቆጥበው ነበር ። ህብረቱ ወደ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ አዘምታለሁ ሲል ቃል የገባውን ቁጥር ከአባላቱ ብቻ ማሟላት አልቻለም ። የህብረቱ አባል ያልሆነችው ጆርጂያ 150 ወታደሮችን ለመላክ ፈቃደኛ ባትሆን ኖሮ ሊላክ የታቀደውን 1 ሺህ ወታደር ማግኘት መቻሉም አጠራጣሪ ነበር ። የተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ውሳኔ ተልዕኮው ለሠላማዊ ሰዎች ጥበቃ እንዲያደርግ የሚፈቅድ ቢሆንም ከአውሮፓ ወደ ሃገሪቱ የሚዘምቱት ወታደሮችም በተቻለ መጠን ደህንነታቸው አስተማማኝ በሆኑ በዋና ከተማይቱ በባንጊ አውሮፕላን ማረፊያና በሌሎች የተወሰኑ አካባቢዎች ነው የሚሰማሩት ። በዚህ ላይ ደግሞ በዚህ ዘመቻ የጀርመን ተሳትፎ በዋነኝነት የአየር ትራንስፖርት ማቅረብ ነው ። ሁለት እቃ ጫኝ አንቶኖቭ አውሮፕላኖችን አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ ቁስለኞችን የሚያጓጉዝ ሆስፒታል ያለው ወታደራዊ አውሮፕላን ታቀርባለች ።

ከዚህ በተጨማሪ የጀርመን ወታደሮች በግሪክ ከተማ በላሪሳ ና በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ዋና ከተማ ባንጊ ዋና ፅህፈት ቤቶች ውስጥ ከመስራት ውጭ በውጊያ መካፈላቸውን የጀርመን መንግስት አልፈቀደም ።ይህ ደግሞ መንግስትን እያስተቻቸው ነው ። የቀድሞ የጀርመን ጦር ኃይል ኢንስፔክተር ጀነራል ሃራልድ ኩያት ከተችዎቹ አንዱ ናቸው ። በርሳቸው አስተያየት ጀርመን ወታደሮቼን ለውጊያ አላሳልፍም ማለቷ ለአውሮፓ አጋሮቿ መጥፎ ምልክት ነው የሚያስተላልፈው ።

Zentralafrikanische Republik - Französische Soldaten an einem Checkpoint in Bangui
ምስል DW/S. Schlindwein

« ያ ማለት ኃይል ማሰባሰቢያ ተብሎ በሚጠራው ሂደት ውስጥ ከመጀመሪያው አንስቶ በእቅዱም ጭምር መሳተፍ ያስፈልጋል ነው ። ሆኖም ገና እቅዱ ሳይጠናቀቅ ከመነሻው ማፈግፈግ ወይም ደግሞ በይፋ ማሳወቅ አይገባም ። ምክንያቱም ያ ወደ ታወቁት አዳጋች ሁኔታዎች ነው የሚያመራው »

ጀነራል ኩያት ጀርመን አሁን የያዘችው አቋም በሂደት በአጋሮቿ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩ አይቀርም ባይ ናቸው ።

« ሃላፊነትን መውሰድ ከተፈለገ ወታደሮችን መውሰድ ወይም ቁስለኞች እንደ ማጓጓዝን በመሳሰሉ ቀላል በማይባሉ ጉዳዮች ላይ ሃላፊነትን መወጣት ይገባል ። አጋሮቻችንን ወታደሮቻውን እያጓጓዝን ቁስለኞችን ወደ ሃገራቸው እየመለስን እኛ ግን ራሳችን በዘመቻው በቀጥታ ተሳታፊ አለመሆናችን በሂደት አይቀበሉትም ። በኔ አስተያየት ይሄ ተቀባይነት የለውም ። »

በዚህ ጉዳይ ላይ ለዶቼቬለ አስተያየታቸውን የሰጡት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና የጀርመን የውጭ ግንኙነቶች ምክር ቤት ባልደረባ ኢቮን ቫን ዲፐን ጀርመን ይበልጥ ላገለግል እችላለሁ በምትልበት ዘርፍ ለመሳተፍ ፈቃደኝነቷን መግለጿ ተገቢ ነው ሲሉ ይከራከራሉ ።

«እንደሚመስለኝ የጀርመን የወታደሮች መዋጮ የተገደበ ቢሆንም ሃገሪቱ በአውሮፓ የደህንነት መርህ ውስጥ ሃላፊነቷን በሚገባ እየተወጣች መሆንዋን የሚያሳይ ግልፅ ምልክት ነው ። ጀርመን አሁን ያተኮረችው በዋነኛ አቅሟ ላይ ነው ይህም ስልታዊ በሆነው የአየር ትራንስፖርት እንጂ በውጊያ የሚሳተፉ ወታደሮችን በማሰለፍ አይደለም »

Zentralafrikanische Republik Bangui Alltagsleben
ምስል F.Daufour/AFP/GettyImages

ጀርመን ለአፍሪቃ ህብረት የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ተልዕኮ የገንዘብ ድጋፍ ታደርጋለች ። የአፍሪቃ ህብረት የሰላም ተልዕኮዎችን በገንዘብ የሚደግፈውን የአውሮፓ የልማት ድርጅትም የገንዘብ ድጋፍ ሰጭ ናት ።የጀርመን የልማት ሚኒስትር ጌርድ ሙለር ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ ባንጊን በመጎብኘት የመጀመሪያው የጀርመን መንግሥት ተወካይ ናቸው ።በርሳቸው አስተያየት አውሮፓውያን አጋሮች ከጀርመን ብዙ ይጠብቃሉ ።

«የአውሮፓ ህብረት ተልዕኮ ን በሚመለከት ብዙዎቹ አጋሮቻችን እኛ ቢያንስ ለአውሮፓ ህብረት በምናዋጣው ገንዘብ መጠን በዘመቻውም እንድንሳተፍ ይጠብቃሉ »

ከሙለር ጉብኝት በኋላ ጀርመን ለማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ የምታደርገው የልማት ትብብር እንደገና ተነሳስቷል ።ጀርመ ለሃገሪቱ አስቸኳይ እርዳታ 11።8 ሚሊዮንዩሮ ለመስጠት ቃል ገብታለች ። በተጨማሪም ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚገኙ የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ስደተኞች መርጃ የሚውል 1,5 ሚሊዮን ዩሮም ለግሳለች ። የጀርመን መከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው እስከነገ ድረስ የጀርመን ወታደሮች ባንጊ ይገባሉ ። ተልዕኮው በመጋቢት ወር እንዲጀመር ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በፀጥታ ችግር መባባስ ምክንያት መዘግየቱ ታውቋል ።

ሂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ