1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሚና

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 19 2006

ተጣማሪ መንግሥት ለመመስረት ከአንድ ሳምንት በፊት መደራደር የጀመሩት የጀርመን ትላላቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤የክርስቲያን ዲሞክራቶች እና የክርስቲያን ሶሻል ህብረት ፓርቲዎች እንዲሁም የሶሻል ዲሞክራቶች ህብረት ፓርቲ ወደ መግባባት መቃረባቸው እየተነገረ ነው።

https://p.dw.com/p/1A8Xf
Bundestagምስል picture-alliance/dpa

ይሁንና የሚጠበቀው የጥምር መንግሥት ትላልቆቹን ፓርቲዎች የሚያካትት ስለሚሆን ምሥረታ በጀርመን ምክር ቤት በተቃዋሚ ጎራ የሚካተቱትን 2 ፓርቲዎች አቅም የሚያሳጣ መሆኑ እያነጋገረ ነው ። ባለፈው ሳምንት የመጀመሪያ ስብሰባውን ያካሄደው 18 ተኛው የጀርመን ምክር ቤት በሴት ፣የውጭ ዝርያ ባላቸው የህዝብ እንደራሴዎች ብዛት እንዲሁም ከሌላ ዘር ያልተከለሱ የመጀመሪያውንአፍሪቃዊ ተወካይ በማካተት ከቀደሙት ምክር ቤቶች በዓይነቱ የተለየ ተብሏል ። ከአዲሱ ምክር ቤት መቀመጫዎች 36.3 በመቶው በሴቶች ተይዟል ። ከ 4 ዓመት በፊት በተመረጠው ምክር ቤት የሴቶች ብዛት 32.8 በመቶ ነበር ። የዛሬ 4 ዓመት ምክር ቤት የገቡት የውጭ ዝርያ ያላቸው የጀርመን ህግ አውጭዎች ቁጥር በመቶኛ ሲሰላ 3.4 ነበር ። ባለፈው ወር ምርጫ ግን ወደ 5.4 ከፍ ብሏል።እነዚህ በበጎ ከታዩት ለውጦች ውስጥ በዋነኛነት የሚጠቀሱት ናቸው ። በሌላ በኩል ደግሞ ባለፈው መስከረም የተካሄደውን የምክር ቤት ምርጫ ያሸነፉት እህትማቾቹ የክርስቲያን ዲሞክራቶች ህብረት በምህፃሩ CDU እና የክርስቲያን ሶሻል ህብረት በምህፃሩ CSU ፓርቲዎች ከሶሻል ዲሞክራቶች ፓርቲ በምህፃሩ SPD ጋር እንደሚጠበቀው ጥምር መንግሥት ከመሰረቱ የተቃዋሚውን ቦታ የሚይዙት የግራዎቹ ና የአረንጓዴዎቹ ፓርቲዎች በጀርመን ምክር ቤት ሃሳባቸውን ማንሸራሸር የሚችሉበት አቅም አናሳ ሊሆን መቻሉ እንደ አንድ ችግር ተወስዷል ።

Bundestag konstituierende Sitzung Plenarsaal 22.10.2013 Merkel
ሜርክል በፓርላማው የCDU ና የCSU ተወካዮች ቡድን መሪዎች መካከል ተቀምጠውምስል Odd Andersen/AFP/Getty Images

ከጀርመን ምክር ቤት ቡንደስታግ 631 መቀመጫዎች 504ቱ ጥምር መንግሥት ይመሰርታሉ ተብለው በሚጠበቁት በእህትማማቾቹ በክርስቲያን ዲሞክራቶችና በክርስቲያን ሶሻል ህብረት እንዲሁም በሶሻል ዲሞክራቶች ፓርቲዎች ሲወሰድ በተቃዋሚዎቹ በግራዎቹና በአረንጓዴዎቹና የሚያዘው መቀመጫ 127 ብቻ ይሆናል ። በቀደመው ምክር ቤት ግን ተቃዋሚዎች በምክር ቤቱ የነበራቸው መቀመጫ ከዚህ ከእጥፍ በላይ ነበር ። ቁጥራቸው ከፍ ያለ ስለነበረም አቅማቸውም የዚያኑ ያህል የተሻለ ነበር ። በአዲሱ ምክር ቤት ቁጥራቸው አናሳ እንደሚሆን የሚጠበቀው ተቃዋሚዎች ግን እንደ ከዚህ ቀደሙ አንዳንድ ጉዳዮችን የሚያጣሩ ኮሚቴዎች እንዲቋቋሙ ሃሳብ የማቅረብም ሆነ በመንግሥት ላይ የመታመኛ ድምፅ እንዲሰጥ የማድረግ አቅም ሊኖራቸው እንደማይችል የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ ። በዚህም ምክንያትም በምክር ቤቱ የተቃዋሚነት ሚናቸውን በአግባቡ መወጣት አይችሉም እንደ ተንታኞች ። ይህ ሊሆን የቻለበትን ምክንያት ፍራንክፈርት ጀርመን ነዋሪ የሆኑት የህግ ባለሞያና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዶክተር ለማ ይፍራ ሸዋ ያብራራልናል ።

የዛሬ ሳምንት በተካሄደው የጀመን ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ይህ ችግር ተነስቶ መፍትሄ እንዲፈለግ ሃሳብ ቀርቧል ።

ያም ሆኖ የትላልቅ ፓርቲዎች መጣመር በምክር ቤት ውስጥ ተቃዋሚዎችን ከመዳከም ሌላ በመራጩ ህዝብ ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖ ና ይህም የሚያስከትለው ችግር ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም እንደ ዶክተር ለማ ።

Bundestagspräsident Norbert Lammert
የጀርመን ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኖርቤርት ላሜርትምስል picture-alliance/dpa

በጀርመን የትላላቆቹ ፓርቲዎች ጥምረት የዲሞክራሲውን ሜዳ ያጠበዋል ቢባልም በዶክተር ለማ አስተያየት የተለያየ አቋም ያላቸው ፓርቲዎች ጭርሱኑ መጣመር የለባቸውም ማለት አይደለም ።

የክርስቲያን ዲሞክራትና የክርስቲያን ሶሻል ህብረት እንዲሁም የሶሻል ዲሞክራቶች ፓርቲዎች ባለፈው ሳምንት የጀመሩት የመንግሥት ምሥረታ ድርድር እስከ ታህሳስ አጋማሽ ድረስ ሊቀጥል እንደሚችል ተገምቷል ። ሶሻል ዲሞክራቶች የሠራተኖች ዝቅተኛ ክፍያ በሰዓት 8:50 እዲንዲሆን ፣ ከፍተኛ ገቢ ባላቸው ላይ ግብር ከፍ እንዲል ፣ መንታ ዜግነት እንዲፈቀድ እንዲሁም በአውሮፓ የገንዘብ ዝውውር ላይ ቀረጥ እንዲጣል ይፈልጋሉ ። ክርስቲያን ዲሞክራቶች ደግሞ ዝቅተኛ የደሞዝ መጠን በመሰወኑ አይስማሙም ።ይህ ለአሰሪዎችና ለየክፍለ ሐገር መስተዳድሮች ይተው የሚል አቋም ነው ያላቸው ። ቀረጥ መጨመሩንም አይቀበሉም ። በነዚህና በሌሎችም ልዩነቶች ላይ የተጀመረው ድርድር ተሳክቶ ጥምር መንግሥት ከተመሠረተ ጀርመን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ለ3ተኛ ጊዜ ታላላቆቹ ፓርቲዎች በተጣመሩበት መንግሥት ትመራለች ። ይህ ከተሳካ ዶክተር ለማ እንደሚሉት ለሶስተኛ የሥልጣን ዘመን ለተመረጡት ለጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ትልቅ ጥቅም አለው SPD ጥምር መንግሥት ለመመስረት ከመስማማቱ በፊት ግን የ470 ሺህ አባላቱ ህዝበ ውሳኔ ይጠበቃል ።

ሂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ