1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን የንግድ መርከቦች ማኅበር፣ መንግሥትና ፣ የባህር ላይ ውንብድና፣

ሰኞ፣ ጥር 16 2003

የባህር ላይ ውንብድና ፤ በዓለም አቀፍ ሰፊ የመርከብ ንግድ ተጠቃሚ የሆኑትን ፣ በተለይ ጀርመንን የመሳሰሉትን ታላላቆቹን መንግሥታት እጅግ ያሳሰበ ችግር ሆኗል።

https://p.dw.com/p/Quwr
ምስል Oetker

በመሆኑም፣ መንግሥት ፣ በባህር ኃይሉ፣ ጥበቃ ያደርግለት ዘንድ ከአንድ ዓመት በላይ ሲወተውት የቆየው የጀርመን የንግድ መርከቦች ማኅበር ፣ በዛሬው ዕለት በርሊን ውስጥ ከሀገር አስተዳደር ሚንስትርና ከመከለላከያ ሚንስቴር ጋር ውይይት ያካሂዳል። ከስብሰባው ምን ይጠበቃል? በሃምበርግ ፣ የጀርመን የንግድ መርከቦች ማኅበር ቃል አቀባይ የሆኑትን ማክስ ጆንስን ተክሌ የኋላ፣ አነጋግሮ የሚከተለውን ዘገባ አጠናቅሯል።

ዓለም አቀፉ የባህር ላይ ውንብድና ተመልካች ድርጅት እንዳስታወቀው ፤ ባለፉት 20 ዓመታት ገደማ ፣ የባህር ላይ ውንብድና ፣ የ 2010 ጎርጎሪዮሳዊውን ዓመት ያክል እጅግ የተስፋፋበት ሁኔታ አልነበረም። በ 2009 ካጋጠመው ፣ በ8,5 ከመቶ በመላቅ ፤ በአጠቃላይ 445 የባህር ላይ ውንብድና መፈጸሙና 1,181 የመርከብ ሠራተኞች መታገታቸው ነው የተመዘገበው። የዓለም አቀፉ የንግድ መርከቦች ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፖቴንጋል ሙኩንዳን እንደገለጹት ከሶማልያ ጠረፍ ፈንጠር ብሎ በህንድ ውቅያኖስ ያለው የንግድ መርከቦች መስመር ፣ በዓለም ውስጥ ለአደጋ በመጋለጥ የመሪነቱን ሥፍራ ይዟል። ችግሩ፣ የንግድ መርከቦች ማኅበራትንም ፣ መንግሥታትንም ያሳሰበ እንደመሆኑ መጠን፣ የጀርመን መንግሥት ፤ በዛሬው ዕለት በርሊን ውስጥ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ይመክራል። ዋና ጽ/ቤቱ በሃምበርግ የሚገኘው የጀርመን የንግድ መርከቦች ማኅበር ምን ዓይነት ውጤት ይሆን የሚጠብቀው? የማኅበሩ ቃል አቀባይ ሄር ማክስ ጆንስ-

«እኛ የምንጠብቀው በመጨረሻ፣ የንግድ መርከቦች ጠንከር ያለ የጥበቃ ክብካቤ እንዲያገኙ ነው። የባህር ላይ ወንበዴዎች አሥጊ ድርጊቶችን ጽመዋል። በአደን ባህረ ሰላጤ ብቻ ሳይሆን፣ ገባ ብሎ በህንድ ውቅያኖስ የወሰዱት እርምጃ የሚያሥፈራ ነው።»

በአደን ባህረ ሰላጤ ከአውሮፓው፣ ኅብረት የተውጣጣ «አታላንታ» የሚል ሥያሜ የተሰጠው የተባበረ የባህር ኃይል ተሠማርቶ ተግባሩን እስካሁን በማከናወን ላይ ነው። የኅብረቱን ኃይል እንደማጠናከር በተናጠል የየመንግሥታቱን ባህር ኃይል ማሠማራቱ ይሻላል ማለት ነው--የአታላንታ ተልእኮ አልሰመረም ማለት ነው?

«የአታላንታ ተልእኮ ፣ በተሳካ ሁኔታ ነው የተካሄደው በመጀመሪያ የባህር ላይ ውንብድና ብርቱ ሥጋት እንዳጋጠመን አታላንታ በሚያስደንቅ ፍጥነት እየደረሰ ታድጎናል። ይሁን እንጂ የባህር ላይ ወንበዴዎቹ፤ ሥምሪታቸውን በማስፋት «አታላንታ» እርምጃ እንዲወስድ ሥልጣን ባላገኘበት ፈንጠር ባለው የህንድ ውቅያኖስ መንቀሳቀስ ቀጥለዋል።

ውቅያኖሱ እጅግ ሰፊ በመሆኑ ከሞላ ጎደል በዛ ያሉ የባህር ኃይል መርከቦች በሚፈለገው ፍጥነት ግዳጃቸውን መፈጸም አይችሉም።»

እስከምን ድረስ ነው የችግሩን ስፋትና መፍትኄውንም በተመለከተ ለጀርመን መንግሥት ያስረዳችሁ?

MV Longchamps
ምስል AP

«ለጀርመን ፖሊስና ለባህር ኃይሉ በሰፊው አስረድተናል ሁለቱም፤ በአሁኑ ጊዜ፣ የባህር ላይ ወንበዴዎቹ የሚጠበቁበትን የማጥቃት ስልት በማጤን አንድ ተጨማሪ የሆነ አሥፈላጊ የፀጥታ አጠባበቅ እርምጃ ፣ ማለትም፣ በንግድ መርከቦቻችን ውስጥ የጦር ኃይል አባላት እንዲሠማሩ ማድረግ እንደሚበጅ ግንዛቤ ሳይጨብጡ አልቀሩም። ይህ አዲስ ያቀድነው የፀጥታ አጠባበቅ ስልት ነው። ይህ በሰፊው ፣ የዓለምን የምግብ መርኀ-ግብር መርከቦች ለመጠበቅ ፣ በሚገባ ሥራ ላይ የዋለና አመርቂ ውጤትም የተገኘበት አቅድ ነው።

ተጨማሪ፣ በዛ ያሉ የጦር መርከቦች አያስፈልጉንም፤ የሚያስፈልጉን ተጨማሪ ጸጥታ የሚያስከብር የሰው ኃይል ነው። ተጨማሪ የባህር ኃይል ወታደሮች፣ ለተወሰኑ ሥጋት ላየለባቸው የንግድ መርከቦች ያስፈልጉናል። ይህን ማሟላት የሚከብድ አይመስልኝም። እናም ዛሬ በርሊን ልይ ከሚካሄደው ስብሰባ ተጨባጭ የሆነ ውጤት ይገኛል ብለን እንጠብቃለን። »

ከሶማልያ ጠረፍ ባሻገር በየጊዜው ለሚከሠተው የባህር ላይ ውንብድና መንስዔው በሶማልያ ሥርዓት- አልበኛነት በመንገሡ፣ ሥራ- አጥ ወጣቶችና ምናልባትም የሚያደርጉትን ያጡ የቀድሞ ወታደሮች መበራከት ሳይሆን አልቀረም። ታዲያ፣ ለሶማልያ የፖለቲካ መፍትኄ በመሻት ፣ ማናልባትም የልማት እርዳታ በማቅረብ እንደማገዝ፤ ሰፊ ወጪ የሚጠይቅ የባህር ኃይል ማሠማራት ነው የሚሻለው?

«በመሠረተ-ሓሳብ የምትለው ፍጹም ትክክል ነው። እኛ ማድረግ የምንችለው፣ የባህር ላይ ውንብድናን መከላከል ነው። ለችግሩ መሠረታዊውን መፍትኄ አይደለም የምንሻው። የችግሩን ዋና መሠረት ለማስወገድ፣ ሶማልያ እንድትረጋጋ ማድረግ ተገቢ ይሆናል። ይሁንና ይህ ባለፉት 2 ዐሠርተ-ዓመታት አልተሣካም። ስለዚህ ፤ መጬና እንዴት መፍትኄው ይገኛል፣ በጥንቃቄ መከታተል ይኖርብናል ማለት ነው። በተባበሩት መንግሥታትም በኩል፣ መላ ለመሻት ጥረት ተደርጎ ነበር። አልሠመረም እንጂ---!ለአኛ ለንግድ መርከብ ባለቤቶች ፣ ችግሩ የዕለት-ተዕለት ሆኖብናል። ችግሩ ከ 2 ዓመት በላይ የዘለቀ ነው። መርከበኞቻችን ፣ እጅግ ብርቱ ሥጋት ይደቀንባቸዋል። ይህ በአፋጣኝ ሊሠማራ በሚችል የባህር ኃይል ወታደሮች ፣ በተቻለ መጠን እንዲቆም መደረግ አለበት፤ ወይም ከሞላ ጎደል አደጋው መገታት ይኖርበታል።»

ይህ እንዲሣካ፤ የጀርመን የንግድ መርከቦች ባለቤቶች ማኅበርና የጀርመን ፖሊስ እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊት ተጠሪዎች ፤ ዛሬ ፣ በርሊን ውስጥ በሚያደርጉት ስብሰባ፤ የንግድ መርከቦችን የገጠማቸው ችግር ከሚያስወግድ ውሳኔ ላይ እንደሚደረስ ጽኑ ተስፋ ያላቸው መሆኑን ፣ ማክስ ጆንስ አያይዘው ነው የገለጹት።

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ