1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን የውጭ ንግድና የኤኮኖሚው ቀውስ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 13 2001

ጀርመን የኤኮኖሚ ዕድገታቸው በውጭ ንግድ ላይ ጥገኛ ሆኖ ከሚገኝባቸው የበለጸጉ መንግሥታት መካከል አንዷ ናት። በዚሁ የተነሣም አገሪቱ ምርቶቿን በውጭ ገበዮች ላይ በሚገባ መሸጥ እስከቻለች ድረስ ይሄው የብልጽግናዋ ሞተር ሆኖ ይቀጥላል።

https://p.dw.com/p/JEEz
የጀርመን ኢንዱስትሪና ንግድ ም/ቤት መለያ
የጀርመን ኢንዱስትሪና ንግድ ም/ቤት መለያምስል DW

የውጩ ንግድ መዳበር ለብሄራዊው ኤኮኖሚ ማደግና ለሥራ አጦች ቁጥር መቀነስ ሲበዛ ወሣኝነት አለው። ለዚህም ነው ጀርመን ዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስ በዓለም ንግድ ላይ ባስከተለው ችግር የተነሣ በጣሙን ተጎጂ ሆና የቆየችው። የጀርመን የውጭ ንግድ ገቢ በዚህ ዓመትም 17 ከመቶ በሆነ መጠን ዝቅ እንደሚል ይጠበቃል። ሆኖም የዓለምአቀፉ ቀውስ ከባድ ተጽዕኖ እየለዘበና የማቆልቆሉ ሂደት እያከተመ ዕድገት ስር መስደድ መያዙ በሚነገርበት በአሁኑ ወቅት የጀርመን ኢንዱስትሪና ንግድ ም/ቤት እንደሚተነብየው ቢቀር ተከታዩ 2010 ዓ.ም. የተሥፋ ጭላንጭል የሚታይበት ነው።

በብዙ ጠበብት ዘንድ ሳይቀር ሳይታሰብና ሳይታለም ከሰባ ዓመታት ወዲህ ዓለምን ክፉኛ የመታው የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ የበለጸገ ታዳጊ ሳይል ሁሉንም ነው ያንገዳገደው። በበለጸጉት ሃገራት እስከዚያው ለዚያውም ውሱን የነበረው የኤኮኖሚ ዕድገት እንኳ የሚደረስበት አልሆነም። ይሁንና ጠበብት በወቅቱ እንደሚናገሩት የዓለም ኤኮኖሚ ቀውስ ካለፉት ዓመታት ውድቀት ወዲህ በተለይም በበለጸጉት ሃገራት እየተገታ በወቅቱ የዕድገት አዝማሚያ መታየት ጀምሯል። እርግጥ ሂደቱን ቀጣይ ወይም አስተማማኝ አድርጎ መያዙ ገና አስተማማኝ አይደለም። ለማንኛውም አዝማሚያው የማገገም መሆኑን የሚጠቁሙ መረጃዎች ከያቅጣጫው ይቀርባሉ።

በዚህ በጀርመንም የኢንዱስትሪና ንግድ ም/ቤቱ የሚገምተው ከመጪው 2010 ዓ.ም. ጀምሮ የአገሪቱ ምርቶች በውጭ ገበዮች ሰፊ ተቀባይነት እያገኙ እንደሚሄዱ ነው። በወቅቱም ከያዝነው 2009 ዓ.ም. የመጀመሪያ ሩብ ችግር ወዲህ የጀርመን ኩባንያዎች የውጭ ንግድ እንደገና እየጨመረ መሄዱን መረጃዎች ይጠቁማሉ። እርግጥ የውጩ ንግድ ማገገም በወቅቱ ቀስተኛ ዝግመት የሚታይበት ነው። በመሆኑም የጀርመን ኢንዱስትሪና ንግድ ም/ቤት በተከታዩ ዓመት የሚጠብቀው ዕድገት ከአራት በመቶ አይበልጥም።

አነሰም በዛ ይህ በጎው አዝማሚያ ሲሆን በሌላ በኩል አስከፊው ዜና የውጩ ንግድ በያዝነው ዓመት ሂደት 17 ከመቶ የሚያቆለቁል መሆኑ ነው። በሌላ አነጋገር ይህ የ 170 ሚሊያርድ ኤውሮ ማቆልቆል ማለት ይሆናል። የጀርመንን ኤኮኖሚ እንግዲህ የአገሪቱ የኢንዱስትሪና ንግድ ም/ቤት የውጭ ኤኮኖሚ ዘርፍ ሃላፊ አክሰል ኒሽከ እንደሚሉት በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት ኮረኮንች የበዛው መንገድ ነው የሚጠብቀው።

“የዓመቱ ሁለተኛ ሩብ አንዱን ወይም ሌላውን ያልተጠበቀ አበረታች ዕርምጃ ነው ያስከተለው። ከቀውሱ አዘቅት ዳዴ እያሉ መውጣቱ በአጠቃላይና ከኛም አኳያ ከተጠበቀው ይልቅ የተፋጠነ ዕርምጃ የሚታይበት ይመስላል። እና ለሚቀጥለው ዓመት ግምታችንን ጥንቃቄ በተመላው መንፈስ በአራት ከመቶ ስንወስን ላለማጋነን እንበል ዛፎች ሰማይ ላይ እንደማይበቅሉ ግልጽ ለማድረግ ነው”

የጀርመን ኢንዱስትሪና ንግድ ም/ቤት ትንበያውን የመሠረተው ከ 80 በሚበልጡ ሃገራት ከሚገኙ የንግድ ም/ቤቶች ጋር ባደረገው መጠይቅ ነው። በተለይ በአውሮፓ ሕብረትና በኤውሮው ምንዛሪ ክልል ሃገራት ውስጥ የሚገኙት ም/ቤቶች የሰጡት ግምት በተለይ ተሥፋ የተመላበት ሆኖ ተገኝቷል። በዓመቱ መጀመሪያ ከባድ ውድቀት በተከሰተባት በዚህ በጀርመን በሚቀጥለው ዓመት ንግዱ ጥሩ ዕርምጃ እንደሚያደርግ ነው የሚታመነው። ይህ ደግሞ በአገሪቱ ኩባንያዎቹ ዘንድ አስደሳች ጉዳይ ነው። ምክንያቱም 65 በመቶ የሚደርሰው የጀርመን የውጭ ንግድ ምርት የሚሄደው ወደ አውሮፓ ሕብረት ዓባል ሃገራት ነው። አሜራሪካና ቻይናም የጀርመንን ምርቶች በሰፊው ይነሳሉ።

‘በአሜሪካም የቀውሱ አደጋ ገና ጨርሶ የተሰወረ ባይሆንም የጀርመን የውጭ ንግድ እንደሚዳብር የመጀመሪያው ቁጥብ ተሥፋ መታየቱ አልቀረም። አሜሪካ የቀውሱ ዋና መነሻ ብትሆንም ለጀርመን የውጭ ንግድ ከስጋት ይልቅ የተሥፋ ምንጭ እየሆነች ነው የምትሄደው። የጀርመን የውጭ ንግድ በቻይና ጠንካራ ፍጆትም ይደገፋል። የቻይና ኤኮኖሚ በቀውሱ ወቅት እንኳ በዚህና በሚቀጥለው ዓመት ሰባት በመቶ ገደማ ዕድገት የሚታይበት ነው የሚሆነው”

በዚህ ሂደት ከሁሉም በላይ የጀርመን የምርት መኪናዎችና የፋብሪካ መሣሪያዎች አምራች ዘርፍ ተጠቃሚ ይሆናል። ጀርመን ወደ ቻይና የምትልከው ከጠቅላላ የውጭ ንግዷ 25 በመቶው ምርት፤ ማለት ሩቡ የሚመነጨው ከዚህ ዘርፍ ነው። የኢንዱስትሪና ንግድ ም/ቤቱ ባልደረባ ኒሽከ እንደሚሉት በአንጻሩ የጀርመንና የሩሢያ ንግድ የቻይናን ያህል ሲዳብር አይታይም።

“ሩሢያ እንደ አንድ የምሥራቃዊው አውሮፓ የሃይል ማዕከል በኤኮኖሚው ቀውስ በተለይ ተጎድታለች። ከጥሬ ዕቃዎች ንግድ የሚገኘው ገቢ መቀነስ፣ የሥራ አጦች ቁጥር መጨመርና ወደ አገር ምርቶችን ለማስገባት ለሚፈልጉ ወገኖች የብድር አሰጣጡ ሁኔታ መጥበቡ ከጀርመን ጋር የሚደረገውን የውጭ ንግድ ክፉኛ ነው ያከበደው። በመሆኑም በዚህ ዓመት ከሲሶ በላይ ማቆልቆል እንደሚታይ እንገምታለን። በሌላ በኩል በሩሢያ የውጭ ንግድ ሸንጎ አባባል ላይ በመመሥረት ጀርመን ለሩሢያ የምትሸጠው ምርት መልሶ በአሥር ከመቶ እንደሚያገግምም ግምታችን ነው”

ከዚህ ሲነጻጸር ጀርመን ከብራዚል፣ ከቅርብና መካከለኛ ምሥራቅ፤ እንዲሁም ከአፍሪቃ ጋር የምታካሂደው ንግድ በመልካምነት የሚጠቀስ ነው። በነዚህ አካባቢዎችም የኤኮኖሚው ቀውስ ከባድ ችግርን ያስከትል እንጂ የጀርመን የውጭ ንግድ መጠን ከአማካዩ መስፈርት በላይ ሆኖ ነው የሚገኘው። በአጠቃላይ የጀርመን የውጭ ንግድ ኩባንያዎች ዕርምጃ በዓለም ኤኮኖሚ ሂደት ላይ ጥገኛ ሆኖ ይቀጥላል። የኤውሮ ምንዛሪ ይበልጥ ከጠነከረ ለጀርመን የውጭ ንግድ ጎጂ ሊሆን ይችላል። ለዚሁም ምክንያቱ የጀርመን ምርት ከኤውሮው ምንዛሪ ውጭ በሆኑ አገሮች ውድ ሊሆንና ተፈላጊነቱንም ሊቀንስ መቻሉ ነው።

በታዳጊ አገሮች የሚገኙ አነስተኛ ገበሬዎችን ለማገዝና የሕጻናት የሥራ ጉልበት ብዝበዛንም ለመከላከል ፌየር-ትሬድ ማለት ፍትሃዊ ንግድ በሚል ምርቶችን በተሻላ ዋጋ እየገዙ በዚህ በምዕራቡ ዓለም ገበዮች ማቅረብ ከተጀመረ ቆየት ብሏል። ከነዚሁ ምርቶች መካከል ለምሳሌ ቡናን፣ ሻይን፣ ሩዝንና ኮኮን የመሳሰሉት የእርሻ ውጤቶች ይገኙበታል። በፌየር-ትሬድ መለያ ገበያ ላይ የሚቀርቡት ምርቶች አብዛኛውን ጊዜ በሌሎች ከሚቀርቡት ተመሳሳይ የእርሻ ውጤቶች ወደድ ያሉ ናቸው። ዓላማውም አምራቹ የተሻለ ወይም መርሁ እንደሚለው ፍትሃዊ ዋጋ እንዲያገኝ ማድረግ ነው።

ምናልባት በዛሬው የኤኮኖሚ ቀውስ ወቅት ይህም ዘርፍ ከባድ ፈተና የተጋረጠበት መስሎ ሊታሰብ ይችላል። ሆኖም በዚህ በጀርመን አንድ የዘርፉ ጥናት ውጤት እንደሚያሳየው ንግዱ ባለፈው ዓመት እንዲያውም አርባ ከመቶ ነው ያደገው። የጀርመን ፍጆተኛ ምም እንኳ የኤኮኖሚው ቀውስ ቢጫነውም በየመደብሩ ሰማያዊና አረንጓዴ መለያ ማሕተም የሰፈረባቸውን ምርቶች ማንሳቱን ለዚያውም ካለፈው ዓመት በበለጠ መጠን ቀጥሎበታል። በንግዱ የሚያተኩር አንድ መድረክ ያካሄደው ጥናት እንዳመለከተው ለምሳሌ በፌየር-ትሬድ መስፈርት የሚሸጠው የቡና ምርት ባለፈው ዓመት በ 13 ከመቶ መጠን ሲያድግ የፍራፍሬ ጭማቂዎች ዋጋ እንዲያውም 80 በመቶ ነው የጨመረው።

“የጥናቱን ውጤት አስደሳች የሚያደርገው የፍትሃዊው ንግድ መልዕክት በመላው የሕበተሰብ ቡድኖች ዘንድ ስር እንዲሰድ ለማድረግ መቻላችን ነው። ከዚሁ ሌላ ፍትሃዊውን ንግድ የሚደግፍ፤ ሆኖም ለጊዜው ገና ምርቱን የማይገዛ ሰፊ የሕብረተሰብ ክፍል መኖሩም ተደርሶበታል። እንግዲህ ለዕድገት የሚሆን ሰፊ ምንጭ አለ ማለት ነው”

ይህን የሚሉት የፍትሃዊው ንግድ ማሕበር ሊቀ-መንበር ሃንስ-ክሪስቲያን ቢል ናቸው። ጥናቱ ጨምሮ እንዳመለከተው እስካሁን 44 በመቶው ጀርመናውያን ቢቀር አንዴ ምርቱን ገዝተዋል። ፍጆተኛው በዚህ መልክ የሚገዛው ምርት ጠቀሜታ ምን እንደሆነም ጠንቅቆ የሚያውቅ ነው።

“ጥቂትም ቢሆን የታዳጊውን ዓለም ሕዝብ ለመደገፍ፤ በሕጻናት ጉልበት የሚመረት ነገርን ላለመገዛት፤ አነስተኛ ገበሬዎችን ለመደገፍ መሻት!”

እርግጥ የኤኮኖሚው ቀውስ እስካሁን በሰሜኑ የዓለም ክፍል ግብይት ላይ ተጽዕኖ ባያሳድርም በደቡቡ ታዳጊ ዓለም አምራቾች ዘንድ ግን አሻራው ጎልቶ የሚታይ ነው።

“ገና ከቀውሱ በፉት ከሁለት አንዱ የዓለም ረሃብተኛ የታዳጊ አገር አነስተኛ ገበሬ ነበር። የንግድ ሸሪኮቻችን የምግብ ምርቶች፣ የነዳጅና የማዳበሪያ ዋጋ በጣም በመጨመሩ፤ ለምርት የሚሆን ብድር ማግኘትም ስለሚከብዳቸው በቀውሱ በጣሙን ነው የሚሰቃዩት። በተመሳሳይ ጊዜ ለገጠር ልማት የሚደረገው ድጎማም በተከታታይ እየቀነሰ ነው የመጣው”

በዚሁ የተነሣ ለደቡቡ ዓለም አነስተኛ ገበሬ የምርቱም ዋጋ እያቆለቆለ እንዳይሄድ ማድረጉ እጅግ አስፈላጊ ነው። በወቅቱ ጊዜው የቀውስ ቢሆንም ዋጋው በኢንዱስትሪው ዓለም ፍላጎት ማደግ የተነሣ የተረጋጋ ነው። ግን በበለጸገው ዓለምም ገበያውን ለማሳደግ ያለውን ሰፊ ዕድል መጠቀም ያስፈልጋል።

MM/AA/DW