1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ፓርቲዎች መንግሥት ለመመስረት ተፈራረሙ 

ሰኞ፣ መጋቢት 3 2010

ጀርመኖቹ የክርስቲያን ዲሞክራቲክ አንድነት (CDU) የባየርኑ ክርስቲያን ሶሻሊስት ኅብረት (CSU) እና የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ በዛሬው ዕለት ጥምር መንግሥት የሚመሰርቱበትን ሥምምነት ተፈራርመዋል።

https://p.dw.com/p/2uCBq
Deutschland Unterzeichnung Koalitionsvertrag
ምስል picture-alliance/dpa/AA/E. Basay

የጀርመን ፓርቲዎች ስምምነት ተፈራረሙ

በጀርመን ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ያላቸው ሦስት ፓርቲዎች አዲስ ጥምር መንግሥት ለመመስረት የደረሱበትን ስምምነት ዛሬ በፊርማ አጸደቁ፡፡ ፓርቲዎቹ የተፈራረሙት ሥምምነት በሚቀጥሉት አራት አመታት ጀርመንን የሚመራው ጥምር መንግሥት የሚከተላቸውን ፖሊሲዎች የያዘ ነው።

የስምምነቱን መጽደቅ ተከትሎ የሀገሪቱ የተወካዮች ምክር ቤት አንጌላ ሜርክልን መራሂተ መንግሥት አድርጎ በመጪው ረቡዕ ይሰየማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡  ጀርመናውያን ምርጫ ያካሄዱት ባለፈው መስከረም ወር ሲሆን በምክር ቤት መቀመጫ ያገኙ ፓርቲዎች መንግሥት መመስረት ባለመቻላቸው መራሂተ መንግሥት ሜርክል ሀገሪቱን በሞግዚትነት ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል፡፡ መንግሥት ሳይመሰረት የተቆየበት የ171 ቀናት ጊዜ በጀርመን ታሪክ ረጅሙ ነው ተብሎለታል፡፡

ሜርክል የዛሬውን የጥምር መንግሥት ስምምነት ፓርቲያቸውን የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ሕብረትን (CDU) ወክለው ተፈራርመዋል፡፡ በባቫሪያ ግዛት የCDU እህት ፓርቲ የሆነው የክርስቲያን ሶሻል ሕብረትን በመወከል ሆርስት ዜሆፈር  ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡ ከሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ደግሞ በቅርቡ የገንዘብ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ኦላፍ ሾልዝ ስምምነቱን ፈጽመዋል፡፡ 

Deutschland Unterzeichnung Koalitionsvertrag
ምስል picture-alliance/dpa/AA/E. Basay

ሜርክል በስምምነት ስነስርዓቱ ላይ ሲናገሩ፡-“የጀርመን ምክር ቤት ምርጫ ከተካሄደ ከስድስት ወር ሆኗል፡፡ በወቅቱ መራጮች ድምጻቸውን ለፓርቲዎች ሲሰጡ የሀገራችንን ኃላፊነት መሸከም የሚያስችላቸው ጽኑ የሆነ አብላጫ መቀመጫ ያለው መንግሥት እንዲመሰርቱ አደራ ሰጥተዋቸዋል፡፡ ይህን አደራ የማስተዳደር ኃላፊነት ለማሟላት የነበረው መንገድ ብዙ ቢሆንም ቀላል አልነበረም ብለዋል፡፡ ነገር ግን ዛሬ ይህን አደራ አሳክተናል ማለት እንችላለን” ብለዋል።  

በጀርመን አብላጫ መቀመጫ ያላቸው ፓርቲዎች አዲሱን የጥምር መንግሥት የመሰረቱት ሜርክል አነስተኛ ድምጽ ካላቸው ሁለት ፓርቲዎች ጋር መንግሥት ለመመስረት ያደረጉት ጥረት ከከሸፈባቸው በኋላ እንደነበር ይታወሳል፡፡ የአሁኑ ስምምነት ለሜርክል ከፍ ያለ ድል ነው ተብሏል።

ስምምነቱን ከበርሊኑ ወኪላችን ይልማ ኃይለሚካኤል ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።   

ይልማ ኃይለሚካኤል

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ