1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጁባላንድ ምርጫና የህገ-መንግስቱ ተቃርኖ

Eshete Bekeleሰኞ፣ ነሐሴ 11 2007

በሶማሊያ የጁባላንድ ራስ-ገዝ አስተዳደር ምክር ቤት ባለፈው ቅዳሜ አህመድ ማዶቤ ኢስላንን በፕሬዝዳንትነት መርጧል። የጌዶ፤ መካከለኛውና ታችኛው ጁባ አካባቢዎችን በማጣመር የተመሰረተው የጁባላንድ ራስ ገዝ አስተዳደር ከማዕከላዊ ሶማሊያ ጋር ያለው ግንኙነት የሻከረ ነው።

https://p.dw.com/p/1GGtE
12.06.2013 DW Online Karten Basis SOMALIA Englisch

[No title]

በሶማሊያ ከሚገኙ ጠንካራ ታጣቂ ቡድኖች መካከል የራስ ኮምባኒ መሪ የሆኑት አህመድ ማዶቤ የጁባላንድ ግዛት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል። የጌዶ፤መካከለኛውና ታችኛው ጁባ አካባቢዎችን በማጣመር የተመሰረተውን የጁባላንድ በጊዜያዊነት ሲያስተዳድሩ የቆዩት ማዶቤ ለምርጫ የቀረቡት ከሌሎች ሶስት ተፎካካሪዎች ጋር ነበር። የቀድሞው የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች አጋር ተፎካካሪዎቻቸውን በከፍተኛ የድምጽ ብልጫ ማሸነፋቸውን በሞቅዲሹ የዶይቼ ቨሌ ተባባሪ ዘጋቢ የሆነው መሐመድ ኦማር ሁሴን ይናገራል።

«የቀድሞው ፕሬዝዳንት አህመድ ማዶቤ ከሰባ አራቱ የፓርላማ አባላት መካከል የስልሳ ስምንቱን ድምጽ አግኝተዋል። ከሶማሊያ መንግስት የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩና ጥቂት የፓርላማ አባላት ምርጫውን ታዝበዋል። የኢጋድ ተወካዮችም ተገኝተዋል።»

የጁባላንድ ጊዜያዊ አስተዳደር እንደ ጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር በ2013 ዓ.ም. የተመሰረተ ሲሆን አካባቢው ባለው ከፍተኛ የተፈጥሮ ሐብትና ስልታዊ አቀማመጥ ላለፉት 20 አመታት ግጭት አልተለየውም። የሶማሊያ ህገ-መንግስት በፌደራል ግዛቶች አመሰራረትና ከማዕከላዊ መንግስቱ ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ላይ በግልጽ የሚለው ነገር ባይኖርም የጁባላንድ ግዛት አስተዳደር ግን ራሱን ራስ-ገዝ አድርጎ ይቆጥራል። ከመሐመድ ዚያድ ባሬ ውድቀት ጀምሮ በአገሪቱ የተፈጠሩ ታጣቂ ቡድኖች እርስ በርስ የሚጋጩባት የኪስማዩ ከተማና ወደብ በዚሁ ግዛት ይገኛል። በከሰል ንግድና ቀረጥ ከፍተኛ ገቢ የምታስገኘው ኪስማዩ ከስድስት አመታት በላይ በአሸባብ ጠንካራ መዳፍ ስር ቆይታለች። ከጁባላንድአካባቢዎች የተወሰኑት አሁንም የአሸባብ ታጣቂ ቡድን ይዞታ ናቸው።

Somalia - Hassan Sheikh Mohamud
ምስል picture-alliance/dpa

በሶማሊያ ማዕከላዊ መንግስትና በጁባላንድ አስተዳደር መካከል ያለው ግንኙነትም የሻከረ ነው። በግዛቲቱ ምስረታ ላይ እንኳ ከፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድ መንግስት ይልቅ የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስት ባለሥልጣን -ኢጋድ፤ኬንያ እና ኢትዮጵያ ከፍ ያለ ሚና ተጫውተዋል። በቻተምሃውስየሶማሊያፖለቲካተንታኝአህመድሱሌይማን የጁባላንድ አመሰራረት ለሶማሊያ ፌዴራላዊ የመንግስት አወቃቀር ፈተና እንደሆነ ይናገራሉ።

«በቀጣናው አገራት፤ዓለም አቀፉ ማህበረሰብና በሶማሊያ ጥቅማቸውን ማስከበር በሚፈልጉ አካላት ግፊት የጁባላንድ አመሰራረት የሶማሊያ ፌዴራላዊ መንግስት በተግባርና በወረቀት ላይ ያለውን ልዩነት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። ለህገ-መንግስቱ ጠንካራ ድጋፍ ያስፈልጋል። በግዛቶች አመሰራረትም ህገ-መንግስታዊ ህዝበ -ውሳኔ ሊኖር ይገባ ነበር። አስፈላጊ ከሆነም በግዛቶች አመሰራረትና አስተዳዳሪዎች ምርጫ ላይ ህገ-መንግስታዊ ማሻሻያ ማድረግ ይቻል ነበር።»

መሐመድ ኦማር ሁሴን አሁን ፕሬዝዳንት የመረጠው የጁባላንድ ምክር ቤት በሶማሊያ መንግስት ዘንድ ያለው ተቀባይነት ጥያቄ ውስጥ መሆኑን ይናገራል።

«ባለፉት ጥቂት ወራት በሶማሊያ መንግስትና በጁባላንድ አስተዳደር መካከል ያለው ግንኙነት በጥሩ ሁኔታ ውስጥ አልነበረም። ቅርብ ጊዜ የሶማሊያ ምክር ቤት የጁባላንድ ምክር ቤት ህጋዊ አይደለም ሲል ድምጽ ሰጥቷል። የምክር ቤቱ አባላት በጁባላንድ ነዋሪዎች የተመረጡ ባለመሆናቸው ህጋዊነትም ይሁን ተቀባይነት የላቸውም ብሏል።»

Somalia Mogadischu Sicherheitskräfte
ምስል Getty Images/AFP/M. Abdiwahab

የጸጥታ ተንታኞች የሶማሊያ የግዛት አስተዳደር አመሰራረት የፈጠረው አለመግባባት መፍትሄ ካልተበጀለት አገሪቱን ለማረጋጋት የተጀመረው ጥረት ችግር እንደሚገጥመው ይወተውታሉ። አሁን በጁባላንድ ላይ የተፈጠረው ልዩነት ማዕከላዊ መንግስቱን ከጎሳ መሪዎች ብቻ ሳይሆን ኬንያና ኢትዮጵያን ከመሳሰሉ ጎረቤት አገሮች ጋር ሊያቃቅር ይችላል የሚል ስጋት አለ። አህመድ ሱሌይማን «አሁን በሶማሊያ ህገ-መንግስት አስገራሚ ሁነት እየተመለከትን ነው። አገሪቱ አንዳንዶች እንደሚሉት ጎሳን ባማከለ ግዛት እየተከፋፈለች ነው።እንደ ጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር ከ2012 ወይም2013 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎች ፍላጎት የህገ-መንግስቱ የተወሰኑ ክፍሎች እየተጣሱ ነው።» ሲሉ የሶማሊያ ህገ-መንግስት ህልውና አደጋ ውስጥ መውደቁን ይናገራሉ።

አሁን የጁባላንድ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት አህመድ ማዶቤ የአሸባብ ታጣቂ ቡድንን ከይዞታዎቹ ለማስለቀቅ ቃል ገብተዋል። የግዛቲቱ አስተዳደር ከማዕከላዊ መንግስት ጋር የገባበት አለመግባባት የሚፈታበት መንገድ ግን እስካሁን አልታወቀም።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ