1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

አፍሪቃ-አዉሮጳ-እስያ ይገናኛሉ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 5 2010

የተመረቀዉ በ240 ሔክታር መሬት ላይ የተንጣለለ ነዉ።በ10 ዓመት ደግሞ 4800 ሄክታር መሬት ያካልላል።የአፍሪቃ-አዉሮጳ-እስያ ሸቀጥ ይናኸሕርበታል።ወጪዉም ዋዛ አይደለም።3.5 ቢሊዮን ዶላር ፈጅቷል።60 በመቶዉን የጅቡቲ የወደብ አስተዳደር፤ የተቀረዉን 3 የቻይና ኩባንዮች ይከፍላሉ።

https://p.dw.com/p/31MIv
Dschibuti Einweihung Internationale Freihandelszone
ምስል Getty Images/AFP/Y. Chiba

Dschibuti-Afrikas größte Freihandelzone - MP3-Stereo

 ጅቡቲ ባለፈዉ ሳምንት ያስመረቀችዉ ነፃ የንግድ ቀጠና ከራስዋ ከጅቡቲ አልፎ ለአካባቢዉ ሐገራት እና ከአካባቢዉ ሐገራት ጋር ለሚነግዱ የሌላ አካባቢ ሐገራት ሰፊ ጥቅም እንደሚሰጥ እየተነገረ ነዉ።የምጣኔ ሐብት አዋቂዎች እንደሚሉት የንግድ ቀጠናዉን የገነባችዉ ቻይናም እስካሁን የነበረዉን የምዕራባዉያን ሐገራትን ተፅዕኖ አዳክማ  ምጣኔ ሐብታዊ እና ፖለቲካዊ ጥቅሟን ለማስከበር ይረዳታል።የዚያኑ ያክል ለግንባታ የወጣዉ ገንዘብ እና ለአገልግሎቱ የሚያስፈልገዉ የሰለጠነ የሰዉ ኃይል ትንሺቱን ምሥራቅ አፍሪቃዊት ሐገር ዕዳ ዉስጥ እንዳይከት ማሳሰቡ አልቀረም።ዳንኤል ፔልስ የዘገበዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

ለትንሺቱ ሐገር ታላቅ ድል ነዉ።ለትልቅ መሪዋ ከፍተኛ ኩራት።«የዓለም የዉጪ ንግድ ማዕከል መሆን እንሻለን» አሉ ፕሬዝደንት ኢስማኢል ዑመር ጉሌሕ ማዕከሉ ሲመረቅ፤ ባለፈዉ ሐሙስ።«የአፍሪቃ መግቢያ በር እንሆናለን።» አከሉ።ቢኮሩ አይበዛባቸዉም።
ያስገነቡት የነፃ ንግድ ቀጠና ወይም ማዕከል ከአፍሪቃ ትልቁ ነዉ።የተመረቀዉ በ240 ሔክታር መሬት ላይ የተንጣለለ ነዉ።በ10 ዓመት ደግሞ 4800 ሄክታር መሬት ያካልላል።የአፍሪቃ-አዉሮጳ-እስያ ሸቀጥ ይናኸሕርበታል።ወጪዉም ዋዛ አይደለም።3.5 ቢሊዮን ዶላር ፈጅቷል።60 በመቶዉን የጅቡቲ የወደብ አስተዳደር፤ የተቀረዉን 3 የቻይና ኩባንዮች ይከፍላሉ።
የጅቡቲ የወደብ አስተዳደር ገንዘቡን የሚከፍለዉ ከቻይና ተበድሮ ነዉ።ቻይና የምታገኘዉ ጥቅም ብዙ ነዉ-ይላሉ ኢትዮጵያዊዉ የምጣኔ ሐብት አዋቂ ጌድዮን ጃለታ።
                            
«የንግድ ቀጠናዉን ለሚገነቡ እና በንግድ ቀጠናዉ ለሚሰሩ የቻይና ኩባንዮች የሥራ እና የገበያ ዕድል ይከፍታል።በቻይና እና በኢትዮጵያ፤በቻይ እና በጅቡቲ መካከል የዳበረ የንግድ ግንኙነት አለ።ሥለዚሕ እነዚሕ ሐገራት የምዕራባዉያን ጥገኛ መሆናቸዉ ይቀነሳል።»
በቀጠናዉ ዉስጥ የሚሠፍሩ ኩባንዮች የሽያጭም ሆነ የገቢ ግብር አይከፍሉም። ኩባንዮች ወደ ቀጠናዉ እንዲገቡ ግብዣ፤ ማባበያ፤ ማስታወቂያዉ ተጧጡፏል። የጀርመን የአፍሪቃ ንግድ ምክር ቤት ሊቀመንበር ሽቴፋን ሊቢንግ እንደሚሉት  ቻይና ባካባቢዉ ተፅዕኖ ታሳርፋለች መባሉ አያስፈራቸዉም።
                                         
«ቻይና ንቁ ተሳትፎ ማድረጓ የሚደገፍ ነዉ።የጀርመን ኩባንዮችንም የሚስብ ነዉ።ምክንያቱም በወደብ መሠረተ ልማት ጅቡቲ በጣም ጠቃሚ ሐገር ናት።ወደ ኢትዮጵያ የሚገባዉ ሸቀጥ በሙሉ እና ወደ ሌሎች የሚገባዉ በጀቡቲ በኩል ነዉ።»
ወደብ አልባዋ ትልቅ ሐገር ኢትዮጵያ የዉጪ ንግድ ሕልቅቷ ጅቡቲ ነዉ።ሁለቱን ሐገራት የሚያገናኝ አዲስ የባቡር መስመር ካለፈዉ ጥር ጀምሮ እያገለገለ ነዉ። በዓመት አራት ሚሊዮን ቶን ሸቀጥ ይጓጓዝበታል።
የጅቡቲዉ የንግድ ቀጠና 350ሺሕ ሠራተኞች ይኖሩታል።ከነዚሕ ዉስጥ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ሰባ ከመቶ የሚሆኑት የዉጪ ዜጎች ናቸዉ።የጅቡቲ ዜጎች ስራዉን እየተለመመዱት ሲመጡ ግን የዉጪዉ ሠራተኛ ከ30 ከመቶ አይበልጥም ነዉ የተባለዉ።የምጣኔ ሐብት ባለሙያ ገዲዮን ገለታ እንደሚሉት የዕዉቀት ሽግግሩ ፈጣን እንዲሆን የአፍሪቃ ሐገራት መደራደር አለባቸዉ።
                            
«የአፍሪቃ ሐገራት ለሐገሬዉ ኩባንዮች እና ለሠራተኞች የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር፤ በጋራ ተጣምረዉ እንዲሰሩ፤ የእኩል ድል ሁኔታን ለመፍጠር የአፍሪቃ ሐገራት መደራደር አለባቸዉ።ምክንያቱም የቻይና ኩባንዮች ወደ አፍሪቃ ሲገቡ የሐገሬዉን ኩባንዮች በቀላሉ ያሸንፏቸዋል።ጥቅምም ጉዳትም አለዉ።»
ሌላዉ ጉዳት ጅቡቲን በዕዳ ማጥለቅለቁ ነዉ።የዓለም የገንዘብ ድርጅት በቅርቡ እንዳስታወቀዉ ጅቡቲ ከሁለት ዓመት በፊት የነበረባት የዉጪ ዕዳ ካጠቃላይ ዓመታዊ የሐገር ዉስጥ ገቢዋ 50 በመቶ ነበር።አሁን 85 በመቶ ደርሷል።«ዕዳዉ አያሳስበንም» ይላሉ የጅቡቲ የወደብ አስተዳደር ኃላፊ አቡበከር ዑመር ሐዲ ምክንያቱም ዕዳዉን የጂቡቲ ሕዝብ አይከፍልም።የሚከፍሉት በነፃ ቀጠናዉ የሚጠቀሙ ነጋዴዎች፤ኩባንዮች፤የመርከብ ድርጅቶች---እያሉ ይዘረዝራሉ።ግን ማን ተበድሮ-ማን ከፋይ ይሆናል?

Dschibuti Einweihung Internationale Freihandelszone
ምስል Getty Images/AFP/Y. Chiba
Dschibuti Einweihung Internationale Freihandelszone
ምስል Getty Images/AFP/Y. Chiba

ዳንኤል ፔልስ

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ